ፈልግ

የኬንያ ፖሊስ በሄይቲ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ አካል ሆኖ በስፍራው ይገኛል የኬንያ ፖሊስ በሄይቲ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ አካል ሆኖ በስፍራው ይገኛል  (Ricardo Arduengo)

በትርምስ ውስጥ ባለችው ሄይቲ ታግተው የነበሩ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ካህን ተፈቱ

በእርስ በርስ ጦርነት እና ሁከት እየታመሰች ባለችው ሄይቲ ሰኔ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. የወረበሎች ቡድን ግሬሲየር ከተማ ላይ ጥቃት አድርሰው 20 ንጹሃን ሰዎችን ከገደሉ በኋላ በወሮበሎቹ ታግተው የነበሩ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ካህን የሆኑት ሄይቲያዊው አባ ኢማኑኤል ሴንትሊያት ከእስር መፈታታቸው የተረጋገጠው ሃገረስብከቱ ባወጣው መግለጫ ሲሆን፣ በስልጣን ላይ ያሉ አካላት ድርጊቱን እንዲያስቆሙና የሰውን ህይወት እንዲታደጉ ጥሪ አቅርቧል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የሄይቲ ከተማ በሆነችው ግሬሲየር በሚገኘው የቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ደብር ካህን የሆኑት አባ ኢማኑኤል ሴንትሊያት፣ በሄይቲ ዋና ከተማ ፖርት ኦ-ፕሪንስ አቅራቢያ በሚገኘው የግሪሲየር ማዘጋጃ ቤት ላይ ጥቃት በፈጸሙ የወረበላ አባላት ሰኔ 23 ታግተው ነበር።

የፖርት ኦ-ፕሪንስ ሃገረ ስብከት ካህኑ መፈታታቸውን ያረጋገጠ ሲሆን፥ አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን ምንጮች እንደገለጹት ካህኑን ለማስለቀቅ ምንም ዓይነት ክፍያ አልተከፈለም።

በቀድሞው የፖሊስ መኮንን ጂሚ ቼሪዚየር የሚመራው ‘ቪቭሬ ኤንሴምብል’ የተባለ ታጣቂ የወረበሎች ቡድን ሰኔ 23 በከተማዋ ባደረሱት ከፍተኛ ጥቃት ቢያንስ 20 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፥ በአጠቃላይ በሀገሪቱ ካለው ትርምስ ጀርባ የቡድኑ መሪ እንዳለ ይታመናል። ከዚህም በተጨማሪ የቡድኑ መሪ መጋቢት ወር ላይ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አሪኤል ሄንሪ ከስልጣን እንዲለቁ ጠይቆ እንደነበርም ይታወሳል።

በግሬሲየር ከተማ የታጠቁ ቡድኖች ከቀናት በፊት በኬንያ የሚመራውን የሰላም አስከባሪ ጦር በስፍራው መምጣቱን በመቃወም በርካታ ቤቶችን በማቃጠል በህብረተሰቡ ላይ ሽብር ፈጥረዋል። ሆኖም የሃገሪቱ ፖሊስ አሁን ላይ አካባቢውን እንደገና መቆጣጠር እንደቻለም እየተነገረ ይገኛል።

የኬንያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ

ሰኔ 24 ላይ መግለጫ ያወጣው የፖርት ኦ-ፕሪንስ ሃገረ ስብከት በሁኔታው የተሰማውን ንዴት እና ሀዘን በመግለጽ የሄይቲን ማህበረሰብ ጠፍንጎ የሚይዝ “በክፋት አዙሪት ውስጥ ያለ እስራት” አይነት ነው በማለት ገልጿል። መግለጫው በእሁዱ ጥቃት የተፈፀመውን ድርጊት በመቃወም፣ “ለመናገር የሚያዳግት እጅግ አስከፊ ጥቃት” በማለት በጽኑ አውግዟል።

ከዚህም በተጨማሪ መግለጫው “የሚያገለግሉትን ማህበረሰብ ፈጽሞ ያልተው እና ሁልጊዜ ሌሎችን ለመርዳት ዝግጁ የሆኑ” በማለት አባ ሴንቴሊያትን አወድሷል።

አባ ሴንትሊያት እንዲፈቱ የተደረገ ጥሪ

የፖርት ኦ-ፕሪንስ ሃገረ ስብከት በተጨማሪም ክስተቱ አንዳንድ የዋና ከተማዋ ፖርት-አው ፕሪንስ ክልል ውስጥ አሁንም ለሕዝቡን ደህንነት የሚያሰጉ ከቁጥጥር ውጪ የሆኑ ተግባራት መኖራቸውን በመጥቀስ፣ ሃገረስብከቱ አሁንም “ለሁሉም ተጎጂዎች እና ቤተሰቦቻቸው ቅርብ ነው” ሲል አረጋግጧል።

በመጨረሻም መግለጫው የመንግስት ባለስልጣናት በአስቸኳይ “ይህን የአመፅ ድርጊት ለማስቆም እና በሀገሪቱ ውስጥ የመኖር መብትን እንደገና ለማረጋገጥ እርምጃ የመውሰድ” አስፈላጊነትን በማስታወስ ደምድሟል።
 

04 July 2024, 15:25