ፈልግ

እስራኤል በሰሜን ጋዛ የፈጸመችው የአየር ድብደባ እስራኤል በሰሜን ጋዛ የፈጸመችው የአየር ድብደባ   (ANSA)

በእስራኤል የአየር ጥቃት 141 ሰዎች መገደላቸውን ሃማስ ገለጸ

የሃማስ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው የአየር ድብደባ ቢያንስ 141 ሰዎች መሞታቸውን አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ እስራኤል በፈጸመችው የአየር ድብደባ ቢያንስ 141 ሰዎች መሞታቸውን ጋዛ የሚገኝ የሃማስ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ያለፈው ቅዳሜ እስራኤል በካን ዮኒስ አቅራቢያ በፈጸመችው የአየር ጥቃት 90 ሰዎች ሲሞቱ 300 ሰዎች መቁሰላቸው የሚታወስ ሲሆን፥ እስራኤል ይህን ጥቃት የፈጸመችው ብዙ ሕዝብ ተጠልሎ በሚገኝበት በማዋሲ አካባቢ ሲሆን፥ አካባቢው ለተፈናቀሉት የጋዛ ሕዝቦች ደህንነቱ የተጠበቀ ቀጠና እንደሆነ የእስራኤል ጦር አሳውቆ ነበር።

ጋዛ ውስጥ ዕርዳታን በማስተባበር እና በማሰራጭት ሥራ የሚታወቅ የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲ (UNRWA) በአሁኑ ጊዜ ወደ 1.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች እዚያ ተጠልለው እንደሚገኙ ገምቷል። በግንቦት ወር እስራኤል በራፋህ ላይ ጥቃት ካደረሰች በኋላ ብዙ ፍልስጤማውያን በካን ዮኒስ ተጠልለው እንደሚገኙ ይታወቃል።

በካን ዮኒስ የተፈጸመውን ጥቃትን ተከትሎ ሃማስ ከእስራኤል ጋር የሚያደርገውን ቀጥተኛ ያልሆነ የተኩስ አቁም ድርድር አቋርጧል” የሚሉ ዘገባዎችን ሃማስ ያለፈው እሑድ አስተባብሏል።

ዘገባዎች እንደሚያሳዩት እስራኤል የሃማስ ወታደራዊ ክንፍ መሪ መሐመድ ዴፍን ኢላማ አድርጋለች። የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ መሪው መሐመድ ዴፍ መስከረም 26/2016 ዓ. ም. በእስራኤል ላይ ከደረሰው ጥቃት ጀርባ ካሉት መካከል አንዱ እንደሆነ ይታሰባል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጋዜጣዊ መግለጫው “ጦርነቱ የሚያበቃው እስራኤል ሁሉንም ግቦቿን ካሳካች በኋላ ነው” ማለታቸው ይታወሳል።

አሁን ባለው ሁኔታ በእስራኤል እና በሃማስ መካከል በመካሄድ ላይ በሚገኘው ጦርነት 38,345 የጋዛ ነዋሪዎች መገደላቸውን የፍልስጤም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል። በሌላ በኩልም ሃማስ መስከረም 26/2016 ዓ. ም. በእስራኤል ላይ በፈጸመው ጥቃት 1,195 ሰዎች እንደተገደሉ እና አብዛኛዎቹ ሲቪሎች እንደሆኑ ይነገራል።

የሶርያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ እስራኤል በሶርያ ምድር ላይ ያደረሰችው ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ገልጿል።

እስራኤል በደማስቆ ወስጥ ባካሄደችው ጥቃት የሶርያ ወታደሮች ለሞት መዳረጋቸው እና በታለሙባቸው አካባቢዎችም ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ታውቋል።

 

16 July 2024, 17:05