ፈልግ

የሳህል ሃገራት ወታደራዊ መሪዎች በኒያሚ በተደረገው ጉባኤ ወቅት የሳህል ሃገራት ወታደራዊ መሪዎች በኒያሚ በተደረገው ጉባኤ ወቅት  

ኒጀር፣ ማሊ እና ቡርኪናፋሶ አዲስ የ 'ሳህል ሃገራት ህብረት' አቋቋሙ

በማሊ፣ ቡርኪናፋሶ እና ኒጀር የሚገኙ ወታደራዊ አገዛዞች መሪዎች ‘የሳህል ሃገራት ኮንፈደሬሽን’ የሚባል አዲስ ህብረት መመስረታቸው ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እነዚህ ሶስቱ የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት ማለትም የቡርኪና ፋሶ፣ የማሊ እና የኒጀር ወታደራዊ መሪዎች በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ላይ የወጡ ሲሆኑ፥ “የሳህል አገራት ኮንፌዴሬሽን” የተባለ ጥምረት መመሥረታቸውን አውጀዋል።

በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ስልጣን ከያዙ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት የጋራ ጉባኤ ጥምረቱን መመስረታቸውን አስመልክተው የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የሦስቱ አገራት ወታደራዊ መሪዎች ቅዳሜ ሰኔ 29 ቀን 2016 ዓ.ም. በኒጀር መዲና ኒያሚን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ከአሁን በኋላ አዲሱ ቡድን በፀጥታ ጉዳዮች ላይ ተባብሮ እንደሚሰራ፣ የጋራ መገበያያ ገንዘብ መፍጠርን ጨምሮ ኢኮኖሚያዊ ትስስርን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

የኒጀር መሪ ጄኔራል አብዱራሃማኔ ቺያኒ፣ የማሊው ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ እና የቡርኪና ፋሶው መሪ ሻምበል ኢብራሂም ትራኦሬ የመሠረቱተ ጥምረት “በውጪ ኃይል ቁጥጥር ስር አይወድቅም” ብለዋል።

አንድ ላይ ተደምረው ከ70 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የሚሆኑት ሦስቱ ሃገራት በተደጋጋሚ በተከሰተው የታጣቂ አንጃዎች አመጽ የጸጥታ ችግር ውስጥ ገብተው እንደነበር ይታወቃል።

የቡርኪናፋሶው መሪ ካፒቴን ኢብራሂም ትራኦሬ ጉባኤው ከተካሄደባት የኒጀር ዋና ከተማ ኒያሚን በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት ጉባኤው 'ለወደፊታችን የጋራ ቦታ ወሳኝ እርምጃ' ነው ብለዋል። ትራኦሬ አክለውም እንደተናገሩት የሰላም እና የዘላቂ ልማት ዋስትና የሆነው የእውነተኛ ነፃነት መሰረት “የሳህል ሃገራት ኮንፌዴሬሽን” በመፍጠር ይጠናክራሉ ብለዋል ።

ከኤኮዋስ (ECOWAS) ስለ መውጣት

ሶስቱ በወታደራዊ መንግስት የሚመሩ ሀገራት ባወጡት መግለጫ እ.አ.አ. በ1975 ከተመሰረተው የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ወይም ኢኮዋስ እንደሚለቁ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ነበር። ሀገራቱ ባወጡት የጋራ መግለጫ ኢኮዋስ “በውጭ ሀይሎች ተጠምዝዞ ከቀደሙት የቡድኑ መስራቾች የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ተንሸራቷል” ካሉ በኋላ፥ “ኢኮዋስ የተመሰረተበትን መርህ በመካድ ለአባል ሀገራቱ እና ህዝቦቻቸው ስጋት ሆኗልም” ነው ያሉት።

የሃገራቱ ከኢኮዋስ መውጣት የደህንነት ትብብርን ሊያደናቅፍ ይችላል፥ በተለይም የስለላው መረብ መላላትን እና ከሽብርተኝነት ጋር የሚደረገውን ትግል ሊያዳክመው ይችላልም ተብሏል።

ማሊ፣ ቡርኪናፋሶ እና ኒጀር መደበኛ የቅኝ ገዥዎቻቸው የሆነችውን ፈረንሳይን በጥላቻ አይን እንደሚያይዋት እና በአሁኑ ጊዜ ከምዕራባውያን አገሮች ጋር የቀዘቀዘ ግንኙነት እንዳላቸው ይታወቃል። በቅርቡም ከቱርክ፣ ሩሲያ እና ኢራን ጋር ወዳጃዊ ግንኙነት ለመፍጠር ፍላጎት እንዳላቸው አሳይተዋል።
 

09 July 2024, 15:41