ፈልግ

የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ በኪጋሊ በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ድምጽ ሲሰጡ የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ በኪጋሊ በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ድምጽ ሲሰጡ 

በሩዋንዳ ፕረዚዳንታዊ ምርጫ ካጋሜ በድጋሚ ሊመረጡ እንደሚችሉ ፍንጮች እየታዩ ነው

እ.አ.አ. በ1994 ዓ.ም. በሩዋንዳ ከተካሄደው የጅምላ ጭፍጨፋ ከተካሄደበት ጊዜ ጀምሮ ማዕከላዊ አፍሪካዊቷን ሀገር የመሩት የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር (RPF) ፓርቲ መሪ የሆኑት ፖል ካጋሜ፥ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች “አምባገነን” ናቸው ብለው አጥብቀው ሲተቹ የነበረ ቢሆንም፥ በአሁኑ ፕረዚዳንታዊ ምርጫ ከሁሉም በላይ የአሸናፊነት ግምት ተሰጥቷቸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በሚሊዮኖች የተቆጠሩ ሩዋንዳዊያን ሃምሌ 8 ቀን 2016 ዓ.ም. ሰኞ ዕለት ፕሬዚዳንታቸውን እና የምክር ቤት ተወካዮቻቸውን ሲምርጡ ውለዋል፡፡ በምርጫው ሃገሪቱን ላለፉት በርካታ ዓመታት ሲገዙ የነበሩት ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ ስልጣናቸውን ለተጨማሪ አምስት ዓመት የሚቀጥሉ እንደሚሆን ይታመናል።

የወቅቱ ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ ለ30 ዓመታት ያልተቀየረውን የአገዛዝ ሥርዓት በኋላ ለምርጫው የቀረቡትን ሁለት ደካማ ተቃዋሚ እጩዎችን አሸንፈው በድጋሚ ይመረጣሉ ተብሎ በሚጠበቀው ምርጫ ላይ ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ሩዋንዳውያን ቀጣዩን ፕሬዝዳንት እና የፓርላማ አባላትን ለመምረጥ ሰኞ ዕለት በምርጫ ድምፅ ሲሰጡ ውለዋል።

የ66 ዓመቱ የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር መሪ እ.አ.አ. ከ1994 ጀምሮ ሥልጣን ላይ የነበሩት ሲሆን፥ ይህ በቱትሲዎች የሚመራው ፓርቲያቸው ስልጣኑን ከሁቱ መንግስት ከተረከበ በኋላ ከ800,000 እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ቱትሲዎችን እና ለዘብተኛ ሁቱዎችን ህይወት የቀጠፈውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በማስቆም ሃገሪቷን ወደ ተሻለ ዕድገት መርተዋታል ተብሎም በብዙዎች ይታመናል። እ.አ.አ. ከ1994 ጅምሮ በይፋ ፕሬዝዳንት እስከሆኑበት 2000 ዓ.ም. ጊዜ ድረስ እንደ ምክትል ፕሬዝዳንት ይቆጠሩ ነበር።

ከሩዋንዳ ሕዝብ ስድሳ አምስት ከመቶውን የሚይዙት ከሠላሳ ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች ለአራተኛ የስልጣን ዘመን ከሚወዳደሩት ከካጋሜ ሌላ የሚያውቁት ርዕሰ ብሔር የለም፡፡

ፕሬዝዳንት ካጋሜ ለተከታታይ አራተኛ የስልጣን ዘመን እጩ ሆነዋል

በአውሮፓዊያኑ 2015 ዓ.ም. ሩዋንዳውያን ሁለት ዙር ብቻ የነበረውን ሕገ መንግሥታዊ የስልጣን ዘመን ገደብ በማንሳት እና ከሰባት ወደ አምስት ዓመታት ለማሳጠር ህዝበ ውሳኔ አድርገዋል። ይህም ካጋሜ እስከ 2034 ድረስ በስልጣን ላይ እንዲቆዩ መንገዱን የከፈተ ሲሆን፥ በስልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት አሁንም ሰፊ ህዝባዊ ድጋፍ ማግኘታቸውን ቀጥለዋል።

በአፍሪካ ውስጥ በፍጥነት በማደግ ላይ ካሉ ኢኮኖሚዎች አንዱ

እ.አ.አ. ከ 2008 እስከ 2022 ዓ.ም. መካከል ባሉ ዓመታት ሃገሪቷ በአማካይ ከ 7 በመቶ በላይ እድገት እንዳስመዘገበች የዓለም ባንክ መረጃ ያሳያል። ይህ ለውጥ በነዋሪዎቿ የኑሮ ደረጃ ላይ ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል የተባለ ሲሆን፥ ከድህነት ወለል በታች የሚኖረው የሩዋንዳ ህዝብ እ.አ.አ. በ2000 ከነበረበት 75.2 በመቶ፥ በ2013 ወደ 53.5 በመቶ ዝቅ ማለቱ ተነግሯል። ከዚህም ባለፈ በሀገሪቱ ውስጥ ካሉ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ የህፃናት ሞት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱም ተመዝግቧል።

ሩዋንዳ ከፍተኛ የወጣቶች ሥራ አጥነት ተግዳሮት ቢፈትናትም በአፍሪካ ፈጣን ኢኮኖሚ እያስመዘገቡ ካሉት አንዷ ነች ተብሏል።

በሃገሪቷ የተመዘገቡ አሉታዊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና በዲሞክራሳዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያሳየችው ጣልቃ ገብነት

ሆኖም ፕረዚዳንት ካጋሜ በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በኩል በተደጋጋሚ ጊዜ “አምባገነን” ናቸው ተብለው የሚተቹ ሲሆን፥ ተቺዎቹ እንደሚሉት እኚህ የኪጋሊ ብርቱ ሰው ምንም አይነት ተቃዋሚ እንዳይኖር መንገዶቹን ሁሉ እንደዘጉ እና ከዚህም ባለፈ ድንበር ዘለል ግድያዎችን በማቀናበር የስልጣን ዘመናቸውን ያራዝማሉ በማለት ይከሷቸዋል።

የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸውም በጥንቃቄ መመርመር አለበት የሚሉት ተቺዎቻቸው፥ የሩዋንዳ መንግስት በምስራቃዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለሚንቀሳቀሱት አማፂ ቡድን እና ሬድ-ታባራ ተብሎ የሚታወቀው የቡሩንዲ ሚሊሻ ወታደራዊ ድጋፍ እንደምታደርግና፥ ይህም ድርጊቷ በነዚህ ሁለት ጎረቤት ሀገራት መካከል አለመግባባት እየፈጠረ ነው ይላሉ።

በጥር ወር የመካከለኛው አፍሪካ ጳጳሳት ጉባኤዎች ማኅበር (ACEAC) ስብሰባ ላይ የተሰባሰቡት የሦስቱ አፍሪካ አገሮች ጳጳሳት በእነዚህ ሃገራት ያለው ችግር ተባብሶ በመቀጠሉ የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸው፥ በዲሞክራሳዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንዲቆም ጠይቀዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቅርቡ ያወጣው ሪፖርት በዲሞክራሳዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ ወደ 4,000 የሚጠጉ የሩዋንዳ ወታደሮች እንዳሉ ገልጿል።

የዩኬ-ሩዋንዳ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ከሃገር የማስወጣት ስምምነት

አዲሱ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመር የቀድሞው ወግ አጥባቂ መንግስት ከሩዋንዳ ጋር የተፈራረሙት ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የማፈናቀል ውል እንደሚሻር ካስታወቁ በኋላ የካጋሜ መንግስት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል። ይህ አወዛጋቢ ስምምነት ቀድሞውኑ በአውሮፓ ህብረት የተተቸ ሲሆን፥ ከሁለት ዓመት በፊት ከተፈረመበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ተቃውሞ ሲያስተናግድ ቆይቷል። የእንግሊዝ ዳኞች የሩዋንዳ የጥገኝነት ጠያቂዎች አያያዝ ስርዓት እና የሰብአዊ መብት አጠባበቋ ደካማ ነው በሚል ምክንያት ይሄንን ስምምነት ውድቅ አድርገውም ነበር።

ፕረዚዳንት ካጋሜ በበኩላቸው እነዚህን ውንጀላዎች ውድቅ በማድረግ ሀገራቸው የፖለቲካ ነፃነትን ታከብራለች ሲሉ የሩዋንዳ የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ ሁሌም አጥብቀው ይሟገታሉ።

ሁለት ተቃዋሚ እጩዎች

በምርጫው ለመወዳደር ማመልከቻ ያስገቡት ስምንት ሰዎች ሲሆኑ የተፈቀደላቸው የዲሞክራቲክ ግሪን ፓርቲው መሪ ፍራንክ ሃቢዜና እና ፓርቲ ሳይወክሉ በግላቸው የሚወዳደሩት ፊልፔ ምፓይማና ብቻ ናቸው።

የሩዋንዳ ዴሞክራሲያዊ ግሪን ፓርቲ መሪ የሆኑት የ47 ዓመቷ ሀቢኔዛ፣ 70 በመቶው ህዝብ በግብርና በተሰማራባት ሀገር የውሃ ተደራሽነትን ለማሳደግ እና የሜካናይዝድ እርሻን ለማስፋፋት ቃል ገብቷል።

ሁለተኛው ተወዳዳሪ የሆኑት የቀድሞው ጋዜጠኛ እና ደራሲ፣ የ54 ዓመቱ ፕሮፌሰር ፓይማና በሃገሪቷ ተከስቶ የነበረውን የዘር ማጥፋት ወንጀልን ሸሽተው ለብዙ ዓመታት በውጭ ሀገር የኖሩ ሲሆን፥ የካጋሜ መንግስት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚያስቀጥሉ፥ በተለይም በግብርናው ዘርፍ እና የህዝቡን የኑሮ ደረጃን ለማሻሻል ቃል ገብተዋል። የህዝብ ቁጥር መጨመርን ለመቋቋም የሶስት ልጅ ብቻ መውለድን የሚደነግገውን ፖሊሲን ተግባራዊ ለማድረግም ቃል ገብተዋል።

በ2017 በተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ 1 በመቶ ድምጽ ያገኙት ሁለቱም ተቃዋሚ እጩዎች የማሸነፍ ዕድላቸው ጠባብ ነው ተብሏል።

የፕሬዚዳንታዊ እና የፓርላማ ተወካይ ምርጫ ውጤት መጪው ሃምሌ 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ይገለፃል ተብሎ ይጠበቃል።
 

16 July 2024, 14:27