ፈልግ

የሁለቱ ግዛቶች የድንበር ከተማ  የሁለቱ ግዛቶች የድንበር ከተማ  

ቆጵሮስ ለሁለት የተከፈለችበት 50ኛ ዓመት ሲታወስ፣ የተባበሩት መንግስታት የአንድነት መንገድን እየፈለገ መሆኑ ተነገረ

ሃምሌ 8 ቀን 1966 ዓ.ም. ቆጵሮስን ከግሪክ ጋር ለመቀላቀል የታለመው መፈንቅለ መንግስት የቱርክን ወረራ ቀስቅሶ ከግሪኮች ጋር በተደረገው ጦርነት ሃገሪቷ ለሁለት የተከፈለች ሲሆን፥ ይህ ክስተት በዚህ ሳምንት 50ኛ ዓመቱን ይዟል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የቱርክ ቆጵሮሳዊያን ‘የቱርክ ሰሜን ቆጵሮስ ሪፐብሊክ’ በሚል በሰሜናዊ ክፍል፣ የግሪክ ቆጵሮሳዊያን ደግሞ በደሴቲቱ ደቡባዊ ክፍል እየኖሩ ይገኛሉ።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ቆጵሮስን ከግሪክ ጋር አንድ ለማድረግ የታለመው መፈንቅለ መንግስት የቱርክን ወረራ ከቀሰቀሰ በኋላ ክስተቱ በዚህ ሳምንት 50ኛ ዓመቱን ይዟል።

በዚህም ጦርነት ምክንያት ከ 1966 ዓ.ም. ጀምሮ የቱርክ ቆጵሮሳዊያን በደሴቲቱ ሰሜናዊ ክፍል፣ እንዲሁም በደቡብ የግሪክ ቆጵሮሳዊያን ይኖራሉ።

ለአምስት አስርት ዓመታት ቆጵሮስ ውስጥ የሚከሰቱት ችግሮች ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከባድ ፈተና ሆነው ሰንብተዋል። ይህችን ከሃምሳ ዓመታት በፊት ለሁለት የተከፈለች ደሴት እንደገና አንድ ለማድረግ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሙከራዎች ተደርገዋል። ሆኖም ግን በ 2009 ዓ.ም. በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አመቻችነት የተደረገው የመጨረሻ ዙር ድርድር ከከሸፈ ወዲህ፣ የሚደረጉት ጥረቶች ለመጨረሻ ደረጃ የቆሙ ይመስላሉ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ መልዕክተኛ የሆኑት ወ/ሮ ማሪያ አንጄላ፣ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በቆጵሮስ ውስጥ ያሉ ግንኙነቶችን ለማደስ ወደ ደሴቲቷ መመላለስ ጀምረዋል።

ወ/ሮ ማሪያ አንጄላ ሆልጊን ምንም እንኳን በቆጵሮስ ያለው ሁኔታ እና ሂደቱ ከባድ ቢመስልም ድርድሩን ዳግም ለማስጀመር የሚቻሉባቸውን መንገዶች ለማሰስ ሃላፊነት የተሰጣቸው ሲሆን፥ ወደ ቆጵሮስ፣ አውሮፓ እና በአካባቢው ያሉ ሃገራት ተመላልሰው በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ሃሳብ ለማወቅ ያደረጉት ጥረት የተሳካ አይመስልም።

ወ/ሮ አንጄላ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫዊ ደብዳቤ “ባለፉት ጊዜያት ያልተሳኩ ግምቶችን ከፈጠሩ እና የበለጠ አለመግባባቶችን እንዲሁም ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎችን ከፈጠሩ የመፍትሄ ሃሳቦች መራቅ አስፈላጊ ነው” ካሉ በኋላ፥ የጋራ የሆነ የወደፊት ሕይወት ለሁሉም ቆጵሮሳውያን ታላቅ ዕድል ይፈጥራል ሲሉ ሰዎች በተለየ መንገድ እንዲያስቡ አሳስበዋል።

ረዘም ያለውና እና በአብዛኛው ስሜታዊነት በሚታይበት ደብዳቤያቸው፣ ቆጵሮሳውያን 'ያሳለፉትን የስቃይ ታሪካቸውን እንዲያሸንፉ' አሳስበዋል።

ቆጵሮስን እየተፈታተኑ ያሉ ችግሮች ውስብስብ እና በርካታ ሲሆኑ፥ ከእነዚህም መሃከል የደህንነት፣ የንብረት፣ የስደተኞች፣ የሰፋሪዎች፣ የኢኮኖሚ እና የህገ መንግስት ችግሮችን ጨምሮ የተለያዩ ወሳኝ ጉዳዮችን ያካትታል።

በሰሜናዊ ኒኮሲያ የሚገኙት የቱርክ ቆጶሮሳዊያን ሉዓላዊነታቸው እና የእኩልነት መብታቸው እስካልተረጋገጠ ድረስ በማንኛውም የድርድር ጠረጴዛ ላይ እንደማይቀመጡ ገልጸዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያለው የግሪክ-ቆጵሮስ መንግስት በበኩሉ፣ በቆጵሮስ ሪፐብሊክ ውስጥ የሚገኘውን አማካይ የድንበር መለያ መስመርን ስለማይቀበል ይህንን እንደ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ፣ የተባበሩት መንግስታት ደሴቲቱ በኒኮሲያ ከሚገኘው ማዕከላዊ መንግስት ጋር በፌዴራል ጥላ ስር እንድትዋሃድ በሚያቀርበው የድርድር ሃሳብ ላይ እንደሚስማማ ገልጿል።

ስለዚህ አሁን ባለው ሁኔታ በሁለቱም ግዛቶች በኩል ምንም ዓይነት የስምምነት አዝማሚያዎች ስለማይታዩ፥ በሁለቱ ወገኖች መካከል እንደገና ድርድር ለመጀመር የሚያስችል እቅድ የለም።

ቆጵሮስ በ 1996 ዓ.ም. የአውሮፓ ህብረትን የተቀላቀለች ሲሆን፥ ነገር ግን የአባልነት ጥቅማ ጥቅሞችን የሚያገኘው ደቡብ ቆጵሮስ ብቻ ነው።

የደሴቲቱ አንድነት ለቱርክ አስፈላጊ እንደሆነ ይቆጠር ነበር፣ ምክንያቱም የተከፋፈለችው ደሴት ቱርክ የአውሮፓ ህብረትን ለመቀላቀል ለምታደርገው ጥረት ዋና እንቅፋት ሆና ነበር። ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ወደ አውሮፓ ህብረት ለመግባት የምታደርገው ጥረት ቀዝቀዝ ብሏል።
 

18 July 2024, 14:31