ፈልግ

አፍጋኒስታን፡ ባግላን ከተማ በጣለው ከባድ ዝናብ እና ጎርፍ ባደረሰው አደጋ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲሞቱ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ቆስለዋል አፍጋኒስታን፡ ባግላን ከተማ በጣለው ከባድ ዝናብ እና ጎርፍ ባደረሰው አደጋ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲሞቱ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ቆስለዋል  (ANSA)

ከ38 ሺህ በላይ አፍጋኒስታዊያን በአስከፊ የአየር ንብረት ምክንያት ከሃገራቸው መሰደዳቸው ተነገረ

በአፍጋኒስታን የሚገኙ በርካታ ክልሎች ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች በአስከፊ የአየር ንብረት ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈናቀሉ ሲሆን፥ ዩኒሴፍ የተባለው የህፃናት አድን ድርጅት ንፁህ ውሃ ለማቅረብ እና መሰረታዊ ግብአት ለሌላቸው ማህበረሰቦች እርዳታ እንዲደረግ አስቸኳይ ጥሪ አቅርቧል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

እ.አ.አ. ከ1976 ዓ.ም. ጀምሮ ለአደጋ የተጋለጡ የአፍጋኒስታን ህፃናት ልጆችን ከአደጋ በመጠበቅ እና የተሻለ የወደፊት ሁኔታን እንዲኖራቸው ከፍተኛ ጥረት እያደረገ የሚገኘው ሴቭ ዘ ችልድረን የተባለው ግብረ-ሰናይ ድርጅት ባለፉት ሰባት ወራት በአፍጋኒስታን በርካታ አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ መፈናቀል መከሰቱን አረጋግጧል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ሀገሪቱ በተለዋዋጭ የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በአስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ውስጥ ገብታ ባለችበት እና ከፍተኛ ሰብዓዊ ዕርዳታ በሚያስፈልግበት በአሁኑ ወቅት የዓለም አቀፍ ዕርዳታ መቀነሱ ተነግሯል።

የሃገር ውስጥ ተፈናቃዮች መከታተያ ማዕከል ባወጣው ሪፖርት መሰረት በዘንድሮ ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ብቻ የተፈናቀሉት ህፃናት ቁጥር ከባለፈው ሙሉ ዓመት ጋር ሲነፃፀር ብልጫ እንዳለው የተጠቀሰ ሲሆን፥ እ.አ.አ. በ2023 ዓ.ም. አጠቃላይ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 37,076 ሲሆን፣ በዘንድሮው ግማሽ ዓመት ብቻ 38,488 ህፃናት እንደተፈናቀሉ ተዘግቧል።

የጎርፍ አደጋ፣ ድርቅ፣ ከፍተኛ የአየር ሙቀት እና አውሎ ንፋስ ጨምሮ የአየር ንብረት ጉዳዮች እጅግ በጣም ብዙ የአፍጋኒስታን ህጻናት እና ቤተሰቦቻቸው ቤታቸውን ለቀው እንዲሰደዱ ማድረጉ ተገልጿል።

በደቡብ እስያ ከሚገኙት ከየትኛውም ሀገር በተለየ ሁኔታ በአፍጋኒስታን ከሰባት ሰዎች መሃል አንድ ሰው ለረጅም ጊዜያት የሚቆይ የሃገር ውስጥ መፈናቀል አደጋ እንደተጋረጠበት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አረጋግጧል።

አፍጋኒስታን በሥነ ምድር አቀማመጥ ርዕደ-ምድር ከሚያጠቃቸው ክልላት ውስጥ የምትገኝ ሲሆን፥ በዚህም ምክንያት በሃገሪቷ ውስጥ የሚከሰተውን የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋን ከፍ ያደርገዋል ተብሏል። በተለይ ብዙ ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት አደጋ ላይ እንደሚጥል እና አስቸኳይ ሰብአዊ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር እንደሚጨምር ተረጋግጧል።

ከድርቅ ጋር የተያያዙ ችግሮች በአብዛኛው በደቡብ አፍጋኒስታን የሚገኘውን የካንዳሃርን ግዛት እንደሚያጠቃ፥ በተለይም ለተከታታይ ሳምንታት የሚከሰተው የዝናብ እጥረት እና ከፍተኛ የሙቀት መጠን ምክንያት በክልሉ በሚገኙ ማሳዎች እና የእርሻ መሬቶች ላይ የውሃ እጥረት እንዲፈጠር አድርጓል።

ሴቭ ዘ ችልድረን በአከባቢው የተከሰተውን አደጋ አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የመጠጥ ውሃ ፍለጋ ቤታቸውን ለቀው በየአከባቢው የተበታተኑት ወጣቶች እጅግ ተራርቀው የሚገኙ የውሃ ጉድጓዶችን ብቻ ስለሚያገኙ እና ይህንንም ከእንስሳቶቻቸው ጋር ስለሚጋሩ ለአደገኛ የበሽታ ወረርሽኞች እንዲሁም ለኮሌራ በሽታ መጋለጣቸውን አመልክቷል።

እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ዩኒሴፍ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅቶች ተባብረው ለተቸገሩት ክልሎች የውሃ አቅርቦት ዝርጋታዎችን እና ታንከሮችን መገንባት የጀመሩ ሲሆን፥ ይህም የንፁህ ውሀ እጥረትን ተከትሎ የሚመጡ ወረርሽኞችን ለመከላከል እገዛ ያደርጋል ተብሏል።

በሃገሪቱ እየተከሰተ ያለው ከፍተኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ በሺዎች የሚቆጠሩ አፍጋኒስታዊያንን ህይወት አደጋ ላይ እየጣለ እንደሚገኝ የተገልጸ ሲሆን፥ በሚያዚያ እና ግንቦት ወራት ውስጥ ብቻ የሀገሪቱ ሶስት አራተኛ በሚሆነው ክፍል በደረሰ የጎርፍ አደጋ በርካታ መኖሪያ ቤቶችን ጠራርጎ የወሰደ አስከፊ የጎርፍ አደጋ መከሰቱ ተመላክቷል።

የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ፌዴሬሽን እንዳስታወቀው በአደጋው በጣም በተጎዳው የባግላን ክልል ከ200 በላይ ሰዎች መሞታቸውን የገለጸ ሲሆን፥ ከዚህም በተጨማሪ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባወጣው ሌላኛው መግለጫ ከሁለት ሶስተኛው በላይ የሚሆኑት የአፍጋኒስታን ግዛቶች በተመሳሳይ ሁኔታ በአሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ አስጠንቅቋል።

የአፍጋኒስታን ህፃናት አድን ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት አርሻድ ማሊክ የአየር ንብረት ቀውሱ እና የሰብአዊ ቀውሱ እኩል በሚባል ደረጃ የአፍጋኒስታዊያንን ህይወት እየቀጠፈ ነው ካሉ በኋላ፥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው የጣልቃገብነት እና የገንዘብ እጥረት ምክንያት እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ያለው እድል እየተመናመነ መምጣቱንም አሳስበዋል።

በሀገሪቱ ከሁለት አስርት ዓመታት በቆየ ግጭትና ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ያለው ህዝብ፣ ይህ አልበቃ ብሎ በየጊዜው በሚከሰቱ የአየር ንብረት አደጋዎች እና የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል ምክንያት የመሻሻል እና የመረጋጋት ተስፋው እየተመናመነ መምጣቱም ተነግሯል።
 

08 August 2024, 13:01