የተባበሩት መንግስታት በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ በሚገኙ እስር ቤቶች የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን አውግዟል የተባበሩት መንግስታት በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ በሚገኙ እስር ቤቶች የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን አውግዟል 

በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ውስጥ በሚገኙ የተጨናነቁ እስር ቤቶች ውስጥ ያለው ስቃይ እና እንግልት

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዘገባ እንደሚያሳየው በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ እስር ቤት ውስጥ እየተስፋፋ ያለውን ብጥብጥ እና ጥቃት ተከትሎ በሚደረገው የጸጥታ ማስከበር ስራ የታዳጊ ጥፋተኞች ማረሚያ ቤት ስለሌለ ህጻናት ከአዋቂዎች ጋር ታስረው እንደሚገኙ በመጠቆም ጉዳዩ ትኩረትን እንደሚሻ አሳስቧል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ በሚገኙ የተጨናነቁ እስር ቤቶች ውስጥ ማሰቃየት፣ ትንኮሳ፣ ህገወጥ እና የዘፈቀደ እስራት የተለመደ ነገር መሆኑን ዩኒሴፍ ለአስር ዓመታት የዘለቀው ግጭት እና አለመረጋጋት በማስመልከት ካወጣው የስጋት መግለጫ ከቀናት በኋላ ይፋ የተደረገው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት ያመላከተ ሲሆን፥ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ እየተካሄደ ያለው ነገር “እያንዳንዱን ልጅ አደጋ ላይ ይጥላል” በማለት ተቋሙ ስጋቱን ገልጿል።

እነዚህ ሁለት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሪፖርቶች በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ከባድ ማኅበራዊ-ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ብቻ ሳይሆን፥ በህፃናት ላይ እየደረሰ ያለውን ስቃይ እውነታንም ያብራራሉ። በእስር ቤቶቹ ሁኔታ ላይ የተባበሩት መንግስታት ባደረገው ጥናት ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናት እንኳን በቀጥታ ተጎጂ እንደሚሆኑ ገልጿል።

የቴርሞሊ ተወላጅ የሆኑት የቅዱስ ጆአን አንቲዳ ቱሬት ገዳማዊያት ማህበር አባል ሲስተር ኤልቪራ ቱቶሎ ከላ' ኦዘርቫቶሬ ሮማኖ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ “መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ሕፃናትን ከእስር ቤት ለማስወጣት ዓለም አቀፍ ስምምነት ብትፈራረምም፥ አሁንም ድረስ የታዳጊ ወጣቶች ማቆያ ማዕከላት ስላልተዘጋጀ ጉዳዩ ትልቅ ትኩረት እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል።

ጣሊያናዊቷ መነኩሴ በካሜሩን ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው በርበራቲ ለ25 ዓመታት የሚጠጋ ሚስዮናዊ ስራ ከሰሩ በኋላ፣ አሁን ላይ “ከፍተኛ ተሰሚነት” ወደአገኙበት የሃገሪቱ ዋና ከተማ ባንጊ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፥ በአሁኑ ጊዜ ‘ኪዚቶ’ የተባለውን መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት እየመሩ ይገኛሉ። የእርስ በርስ ጦርነቱ ከፍተኛ በሆነበት ወቅት ተልእኮዋቸው የሕፃናት ወታደሮችን መልሶ በማቋቋም ላይ ያተኮረ ነበር፥ በአሁኑ ወቅት ግን አጽንዖት ሰጥተው እየሰሩ የሚገኙት በእስር ላይ የሚገኙ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናትን ወደ ማህበራዊ ህይወት መልሶ በማቋቋም ሥራ ላይ ነው።

ከአዋቂዎች ጋር በእስር ቤት ውስጥ የሚገኙ ህፃናት
“በዚህም የተናሳ በከፋ ድህነት ምክንያት ያልተለመደ እና ከትንሽ እስከ ትልቅ ወንጀል የሚፈጽሙ ህጻናት በተጨናነቁ እና ለጎልማሶች ብቻ ታስበው በተዘጋጁ እና መብቶቻቸው ወደማይጠበቅባቸው እስር ቤቶች ውስጥ ይጣላሉ” ሲሉ ሲስተር ኤልቪራ በምሬት ገልጸዋል።

ሲስተር ኤልቪራ በዚህ ጉዳይ ውስጥ የነበራቸውን ቀጥተኛ ተሳትፎ ሲገልጹ፥ ከዕለታት አንዱ ቀን ላይ በበርበራቲ በሚገኘው እስር ቤት ጥቂት ርቀቶች ላይ በነበሩበት ወቅት “ጩኸት እንደሰሙ” እና “የህግ አስከባሪዎች የ12 ዓመት ልጅ ይዘው ወደ እስርቤቱ ሲያስገቡ ባዩበት ወቅት ከፍተኛ ድንጋጤ ተሰምቷቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

ኢሰብአዊ የእስር ሁኔታዎች
በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ባንጊ ከተማ ከሚገኘው በመጥፎነቱ የሚታወቀው የንጋራግባ እስር ቤት ውስጥ ህጻናትን ጨምሮ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ኢሰብአዊ በሆነ ሁኔታ ታስረው እንደሚገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ።

ከመጠን በላይ መጨናነቅ ወደ መጠነ ሰፊ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እና የበሽታዎች መስፋፋት እንደሚያመራ እና እስረኞችን ማንኛውንም ትክክለኛ የሆነ የፍትህ እድል እንደሚያሳጣቸው ይታወቃል።

የተባበሩት መንግስታቱ ሪፖርት በ 2015 ዓ.ም. ላይ 1,749 እስረኞች ፍርድ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን በመጥቀስ፥ የመካከለኛው አፍሪካ ባለስልጣናት አስቸኳይ እና ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ካሳሰበ በኋላ፥ አንዳንዶቹ ደግሞ ለስድስት ዓመታት ያህል ትክክለኛ ፍርድ ሳያገኙ በእስር እንደቆዩ እና ሰብአዊ መብታቸውን እንደተጣሰ ይገልፃል።

የእስር ቤት ማሻሻያ
በታቀደው የእስር ቤት ማሻሻያ ስምምነት ላይ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ እድሎች እንዳሉ የጠቀሱት ሲስተር ኤልቪራ፥ “ነገር ግን ከባድ የገንዘብ እጥረት አለ” በማለት ያለውን ተግዳሮት አስጠንቅቀዋል።

እሳቸው የሚመሩት ኪዚቶ የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ከዩኒሴፍ ጋር በመተባበር የታዳጊ ወጣቶች ማቆያ ማዕከላትን እጦት ለመፍታት በሚያደርጉት ጥረት የዓለም አቀፍ ኮሚሽን አካል መሆናቸውን አስረድተዋል።

ሲስተር ኤልቪራ በበርበራቲ ከተማ ባደረጉት ጥረት በሴሌካ ታጣቂዎች የተመለመሉትን እና በእስር ላይ ያሉትን ጨምሮ 150 የሚደርሱ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናትን ማዳናቸውን ተከትሎ የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ባለ ሥልጣናት ራሳቸው ይህንን ኃላፊነት እንደሰጧቸው ተናግረዋል።

ይህንንም አስመልክተው ከሦስት ወራት በፊት በበርበራቲ ከተማ የተሰራውን አመርቂ ሥራ ለመድገም እንዲችሉ መንግሥት በባንግዊ ዳርቻ ላይ መሬት በነፃ እንደሰጣቸው በመጥቀስ፥ ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከዲፕሎማቶችና ከሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በየጊዜው እንደሚገናኙ ገልጸዋል። “ሆኖም ግን ይህን ማዕከል ለመገንባት የሚያስችል ገንዘብ አጥተናል” ሲሉም አክለዋል።

ለማገገም ተግዳሮቶች
በሃገሪቷ የእርስ በርስ ጦርነቱ በ 2004 ዓ.ም. መገባደጃ ላይ ከተቀሰቀሰ በኋላ የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ሙሉ በሙሉ አገግማ አታውቅም።

በጥቅምት 2015 ዓ.ም. ላይ ፕሬዝዳንት ፋውስቲን አርሴንጅ ቱዋዴራ ብሄራዊ ውይይትን ለማመቻቸት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ስምምነትን አውጀው የነበረ ቢሆንም፥ ነገር ግን አብዛኛው በአልማዝ፣ በዩራኒየም እና በወርቅ የበለፀገው የአገሪቱ ክፍል ከተለያዩ ሚሊሻዎች በሚደርስባቸው ጥቃቶች ስቃይ ውስጥ ገብተዋል።

በሲስተር ኤልቪራ የሚመራው ኪዚቶ የሚባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ብዙ ፈተናዎች ቢኖሩበትም ሥራውን የቀጠለ ሲሆን፥ ሲስተሯ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በ 2008 ዓ.ም. በባንጊ የምህረት ኢዮቤልዩ ቅዱስ በር ሲከፍቱ ያቀረቡትን ጥሪ በማስተጋባት፥ ማዕከላዊ አፍሪካውያን “አለመተማመንን” ፣ “አመፅን” እና “ጥፋትን” በተፈጥሮ ስጦታ በማሸነፍ “የሰብአዊ እና የመንፈሳዊ እድሳትን በጥበብ እንዲያሳኩ" አሳስበዋል።
 

01 August 2024, 15:52