ፈልግ

በህንድ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የሟቾች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የፍለጋ ስራዎች ቀጥለዋል በህንድ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የሟቾች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የፍለጋ ስራዎች ቀጥለዋል  (ANSA)

በኬራላ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት አብያተ ክርስቲያናት እና መስጊዶች ወደ ጊዜያዊ ሆስፒታሎች ተቀይረዋል

በደቡባዊ ህንድ ኬራላ ግዛት የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው የመሬት መንሸራተት አደጋ ከ185 በላይ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ የተነገረ ሲሆን፥ በተከሰተው አደጋ ከ200 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ እስካሁን ሊገኙ ባለመቻሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ የነፍስ አድን ሰራተኞች ረቡዕ ዕለት በጭቃ እና ፍርስራሽ ሥር ፍለጋ ሲያደርጉ እንደነበር ተገልጿል። በዚህም ምክንያት መስጊዶች እና አብያተ ክርስቲያናት ወደ ጊዜያዊ ሆስፒታሎች እና መጠለያዎች በመቀየር አጋርነታቸውን እና አብሮነታቸውን አሳይተዋል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ማክሰኞ ረፋድ ላይ በህንድ ኬራላ ግዛት ላይ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት በደረሰው ከፍተኛ የሆነ የመሬት መንሸራተት በርካታ የመንደሩ ቤቶች በመውደማቸው ቁጥራቸው በትክክል ያልታወቁ በርካታ ሰዎች እስካሁን አልተገኙም።

በደቡብ ህንድ ክልል ዋያናድ አውራጃ ኮረብታማ አካባቢዎች ላይ የተከሰተውን የመሬት መንሸራተት ቤቶችን፣ ዛፎችን፣ እና ድልድዮችን ማውደሙን ተከትሎ ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎች እንደተጎዱ እና 187 ሰዎች ደግሞ የደረሱበት አልታወቀም።

በዚህም 45 የሚሆኑ ቤተክርስቲያንን እና መስጊድን ጨምሮ የእርዳታ ካምፖች የተቋቋሙ ሲሆን ከአደጋው የተረፉ ከ5 ሺህ በላይ ሰዎች ወደ ካምፑ እንደገቡ ተገልጿል፡፡

በአካባቢው በከባድ ሁኔታ እየጣለ ያለው ዝናብ የነብስ አድን ስራው ቀላል እንዳይሆን ማድረጉ ቢገለጽም፤ ከአደጋው እስካሁን ከ3 ሺህ በላይ ሰዎችን በህይወት መታደግ መቻሉ ተጠቅሷል፡፡ ነገር ግን የተዘጉ መንገዶች እና ያልተረጋጋ የመሬት አቀማመጥ የፍለጋ እና የነፍስ አድን ስራዎችን ያስተጓጎለ ሲሆን፥ የህንድ ጦር ከባድ ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች አንዱን የሚያገናኘው ዋናው ድልድይ በአደጋው በመፍረሱ ጊዜያዊ ድልድይ መገንባቱ ተዘግቧል።

ሜፓዲ፣ ሙንዳካኪ እና ቾራልማላን ጨምሮ በርካታ አካባቢዎች በአደጋው ምክንያት መንገዶች በመውደማቸው ተገልለው ያሉ ሲሆን፥ የአከባቢው ባለሥልጣናት “የጠፉ ሰዎችን ለማግኘት የሚደረገው ጥረት በሁሉም መስክ እንደቀጠለ ነው” ብለዋል።

ከ8,300 በላይ ሰዎች ወደ 82 የመንግስት የእርዳታ ማእከላት የተዛወሩ ሲሆን፥ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ጊዜያዊ የሆስፒታል ፋሲሊቲዎች በመስጊድ እና በማድራሳ እንደሚቋቋሙ እንዲሁም በቾራልማላ ቤተክርስቲያን እና ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ጊዜያዊ የሆስፒታል ስርዓት እንደሚዘረጋ አስታውቋል።

የኬረላ የካቶሊክ ብጹአን ጳጳሳት ያሳዩት አብሮነት
በተመሳሳይ ዜና የኬራላ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ምክር ቤት በሰጠው መግለጫ፥ ከመንግስት ኤጀንሲዎች እና ማህበራዊ ድርጅቶች ጋር በመሆን የማዳን ስራዎችን ለማፋጠን እንደሚሰሩ ገልጸዋል። ምክር ቤቱ በሰጠው መግለጫ “የኬረላ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ምክር ቤት ለተጎጂዎች ማጽናኛ ለመስጠት ከመንግስት ጥረት ጋር ሙሉ በሙሉ እንደሚተባበር” ተናግረዋል።

በተጨማሪም “ችግር በተከሰተባቸው አካባቢዎች ካሉ የሀገረ ስብከቱ ቡድኖች እና በጎ ፈቃደኞች ጋር በመሆን አካላዊ ድጋፍ፣ ማጽናኛ እና ቀውሱን ለማሸነፍ ፅናትን እንዲያገኙ ጠንክረን እንሰራለን” በማለት በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖች አጋርነቱን ገልጿል።

የሕንድ የአየር ንብረት ዲፓርትመንት “የዝናብ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተዛባ እና በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚገኘው የዝናብ መጠን እየጨመረ በመምጣቱ በተደጋጋሚ የመሬት መንሸራተት እና የጎርፍ አደጋዎችን ያስከትላሉ” በማለት አስጠንቅቋል።

አደጋውን ተከትሎ በኬራላ ግዛት የሀዘን ቀን መታወጁም ተጠቁሟል፡፡
 

01 August 2024, 17:00