በደቡባዊ ኬራላ ግዛት በዋያናድ ወረዳ ሙንዳካኪ መንደር የመሬት መንሸራተት ከተከሰተ በኋላ ሰዎች የፍለጋ ስራዎች ሲከናወኑ እያዩ በደቡባዊ ኬራላ ግዛት በዋያናድ ወረዳ ሙንዳካኪ መንደር የመሬት መንሸራተት ከተከሰተ በኋላ ሰዎች የፍለጋ ስራዎች ሲከናወኑ እያዩ  (REUTERS)

የህንድ ሀገረ ስብከት በመሬት መንሸራተት ለተጎዱ ሰዎች የእርዳታ ካምፖችን መክፈቱ ተነገረ

በህንድ የካሊከት ከተማ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ቫርጌስ ቻካላካል ደብሮች እና የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች ተቋሞቻቸውን በጊዜያዊነት ወደ የእርዳታ ካምፖች በመቀየር የመሬት መንሸራተት ተጎጂዎችን እንዲያስተናግዱ መመሪያ ሰጥተዋል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የህንድ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የካሊከት ሀገረ ስብከት ምዕመናን በመሬት መንሸራተት ምክንያት ለተጎዱ ቤተሰቦች እና ተጎጂዎች ጸሎት እንዲያደርጉ ጥሪ በማቅረብ፥ “አሁን የተቸገሩትን እና አቅመ ደካሞችን የምናገለግልበት ጊዜ ነው” በማለት ሃገረስብከቱ በድረ-ገጹ ላይ ገልጿል።

ሃምሌ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. በደቡባዊ ህንድ ኬራላ ግዛት ውስጥ ባለው ዋያናድ መንደር ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቀው ከባድ ዝናብ ባስከተለው የመሬት መንሸራተት አደጋ ከ270 በላይ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉ እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ የተነገረ ሲሆን፥ እስካሁን ድረስ 378 የሚጠጉ ሰዎች እንዳልተገኙ ተነግሯል።

የፓራ ሬጅሜንታል ማሰልጠኛ ማዕከል አዛዥ እንደገለፁት ከብሄራዊ የአደጋ ጊዜ መከላከያ ግብረሃይል፣ ከጦር ሰራዊት፣ ከክልል ፖሊስ፣ ከደን ጥበቃ ሠራተኞች እና ከበጎ ፈቃደኞች የተውጣጡ ከ 500 እስከ 600 ሰራተኞች በማዳን ሥራው ላይ ተሰማርተዋል ብለዋል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ እንዳስታወቀው አደጋው በደረሰበት ወረዳ ቢያንስ 85 የእርዳታ ካምፖች ተቋቁመው 8,577 ሰዎች እንዲያርፉበት ተደርጓል። ይህ በኮራልማላ በሚገኙ በዘጠኝ ካምፖች ውስጥ ብቻ የሰፈሩትን 1,822 ግለሰቦች የሚያካትት እንደሆነም ተነግሯል።

የዋያናድ ወረዳ ባለስልጣናት እንደገለጹት የተከሰተውን ከፍተኛ አደጋን ተከትሎ የጠፉትን ሰዎች ቁጥር ለማወቅ መረጃ መሰብሰብ መጀመራቸውን ገልጸው፥ በአከባቢው ይገኛሉ ተብሎ የተጠረጠሩትን ግለሰቦችን ለማግኘት የማዳን ስራው ቀጥሏል ብለዋል።

የሕንድ የነፍስ አድን ሠራተኞች እስከ ሐሙስ ድረስ በጭቃ ውስጥ ተቀብረው የቀሩ የሻይ እርሻዎችን እና መንደሮችን ለማዳን በተከታታይ ከደረሰው ከባድ የመሬት መንሸራተት እምብዛም የሚተርፉ ሰዎችን ለማግኘት ብዙ ተስፋ ሳይኖራቸው ፍለጋቸውን ቀጥለው እንደነበር የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ አመልክቷል።

ለተከታታይ ቀናት የጣለው ከባድ ዝናብ ደቡባዊ የኬራላ ግዛት ላይ ከባድ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፥ አደጋው በደረሰባት የዋያናድ ወረዳ የሚገቡ መንገዶች የተዘጉ በመሆናቸው ከማክሰኞ ጀምሮ የሚደረጉ የእርዳታ ጥረቶችን እያወሳሰበ ይገኛል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በህንድ ውስጥ ከባድ ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት ቁጥር መጨመሩ እና የአየር ንብረት ለውጥ ችግሩን እያባባሰው መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ቀደም ሲል የተገኙ አስከሬኖችን ለማጓጓዝ የበፊቱ መሸጋገሪያ ድልድይ በአደጋው በመጎዳቱ ምክንያት የሃገሪቱ የጦር ሰራዊት ቡድን ጊዜያዊ ድልድይ ለመስራት ሌት ተቀን ሲሰሩ እንደ ነበርም ተገልጿል።

የመሬት መንሸራተት ከመከሰቱ በፊት ባሉት ሁለት ቀናት ውስጥ ቢያንስ 572 ሚሊ ሜትር (22.5 ኢንች) ዝናብ መዝነቡን የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት ፒናራዪ ቪጃያን ተናግረዋል።

የደቡብ እስያ ግድቦች፣ ወንዞች እና ህዝቦች ትሥሥር የአካባቢ ጥበቃ ኤክስፐርት የሆኑት ሂማንሹ ታካር ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደተናገሩት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የዝናብ መጠኑ በከፍተኛ ድግግሞሽ፣ መጠን እና ከፍተኛ የዝናብ ስርጭት እየተቀየረ መሆኑን ተናግረዋል።

ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ ከደረሱት የሕንድ የመሬት መንሸራተት ውስጥ እጅግ የከፋው እ.አ.አ. በ1998 ዓ.ም. የደረሰው ሲሆን፥ በወቅቱ በደረሰው ከባድ ዝናብ ምክንያት በተከሰተው የድንጋይ ናዳ በትንሹ 220 ሰዎችን ሲገድል፣ ትንሿን የሂማሊያን ማልፓ መንደርን እንደቀበረ ይታወሳል።
 

02 August 2024, 18:53