እስራኤል በጋዛ እና ግብፅ ድንበር ላይ ያለው ጦሯ አከባቢውን ለቆ እንደማይወጣ ገለጸች
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የእስራኤል ጦር በጋዛ እና ግብጽ ድንበር ላይ የሚገኘውን እና ለሐማስ “የህይወት መስመር” ነው የተባለውን የፊላዴልፊ ኮሪደር [መተላለፊያ] ተብሎ የሚጠራውን ስትራቴጂካዊ ቀጠናን ግንቦት ወር ላይ መቆጣጠሯን ይፋ አድርጋ የነበረ ሲሆን፥ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሰሞኑን ባወጡት መግለጫ ወታደራዊ ሃይሎቻችንን ጋዛን እና ግብፅን ከሚያዋስነው ድንበር አናስወጣም ማለታቸው ተነግሯል።
ኔታንያሁ ከሃማስ ጋር እየተደረገ ባለው የተኩስ አቁም ስምምነት ምክረ ሃሳብ ላይ ወታደራዊ ሃይሎችን ከድንበር ላይ ለማስለቀቅ መስማማታቸውን ያስተባበሉ ሲሆን፥ ጉዳዩን አስመልክተው የወጡት የሚዲያ ዘገባዎች ‘ትክክል አይደሉም’ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እስራኤል አካባቢውን ለቃ ለመውጣት እንዳልተስማማች ጠቁመዋል።
በዋሽንግተን የሚደገፈው የድርድር ምክረ ሃሳብ የእስራኤል ወታደሮች በጋዛ እና በግብፅ መካከል በሚገኘው እና እጅግ አስፈላጊ የሆነውን የፊላዴልፊ ኮሪደርን ለቆ መውጣትን ያካትታል።
ኔታንያሁ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለማራመድ ከዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር ተነጋግረው የነበረ ሲሆን፥ ሆኖም ግን የውይይቱ ዝርዝር ይፋ አልተደረገም ነበር።
በሌላ ዜና የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት በጋዛ ሰርጥ፣ ራፋህ አከባቢ የሚገኘው የሃማስ ቡድን መሸነፉን እና ወታደራዊ ሃይላቸው በእስራኤል-ሊባኖስ ድንበር ላይ ከሄዝቦላህ ጋር ለመዋጋት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
ረቡእ ዕለት ማለዳ ላይ ሂዝቦላ የእስራኤል ጄቶች በሊባኖስ ድንበር ውስጥ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ በእስራኤል በተያዘው ጎላን ተራራማ አከባቢዎች ላይ በደርዘን የሚቆጠሩ ሮኬቶችን ያስወነጨፈ ሲሆን፥ የሊባኖስ ባለስልጣናት እስራኤል ጥቃት አንድ ሰው መሞቱን እና 30 ሰዎች መቁሰላቸውን ገልጸዋል።