በፓሪሱ ኦሎምፒክ የደቡብ ሱዳን የቅርጫት ኳስ ቡድን ሻምፒዮና ለመሆን እንደሚፈልጉ ገለጹ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በሳምንቱ መጨረሻ በተደረገው የፓሪስ ኦሎምፒክ የቅርጫት ኳስ ጨዋታ ፖርቶ ሪኮን 90-79 በማሸነፍ የደቡብ ሱዳን ብሄራዊ ቡድን ሃገሪቷን በዓለም ህዝብ ዘንድ አስተዋውቋል።
እነዚህ የተገኙት ነጥቦች በትላልቅ የስደተኞች ካምፕ ቀውስ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ካጋጠሟቸው የጦርነት እና የድህነት ዓመታት በላይ ሊታዩ ይችላሉ፣ ነገር ግን የእርቅ ስራዎች አሁንም ድረስ ባለመፈጸማቸው የሰላም ተስፋዎች ደብዝዘዋል።
በየካቲት 2015 ዓ.ም. ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለደቡብ ሱዳን ሕዝብ ያላቸውን ቀረቤታ ለማሳየት እና ለማበረታታት ብሎም ስለ ተስፋ እና እርቅ ለማውራት ወደ አፍሪካ ሀገር ሃዋሪያዊ ጉዞ ማድረጋቸው አይዘነጋም።
ብዙውን ጊዜ ከአከባቢው ርቀው የሚገኙትን የአመጽ እና የድህነት ታሪኮችን ለመስማት ፍላጎት የሌለው የዓለም ማህበረሰብ እሁድ ዕለት በፓሪሱ ኦሎምፒክ በኩል ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን የተባሉ ሃገራት እንዳሉ “ተገንዝቧል” ተብሏል።
ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት የደቡብ ሱዳን ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች የሀገራቸው ትክክለኛ ብሔራዊ መዝሙር ሳይሆን ለ20 ሰከንድ የተሳሳተ መዝሙር በመሰማቱ ግራ ተጋብተው ነበር። ደጋፊዎች ተቃውሟቸውን በጩኸት ገልጠዋል ። በስታዲየሙ አስተዋዋቂ በኩልም ይቅርታ ተጠይቋል። ቀደም ሲል በአወዛጋቢው በፓሪስ ኦሎምፒክ መክፈቻ ሥነስርዓት ወቅት የደቡብ ኮሪያ የኦሎምፒክ ቡድን የሰሜን በሚል ተዋውቆ ነበር። ሁለቱ ኮሪያዎች የዘመናት ቁርሾ ያለባቸው ባላንጣዎች ናቸው። የደቡብ ኮሪያ ቡድን የፓሪስ ኦሎምፒክ ላይ ቅሬታ እንደሚያቀርብ ተገልጧል።
ደቡብ ሱዳን ሃምሌ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. ከኤንቢኤ ኮከቦች ጋር ተጫውተው 103 ለ 86 በመሸነፋቸው ታሪክ ለመስራት የነበራቸው ህልም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ከሰርቢያ ጋር ሃምሌ 27 ቅዳሜ ዕለት የሚያደጉት ጫወታ በጉጉት እየተጠበቀ ይገኛል።
የደቡብ ሱዳን የኦሎምፒክ ቡድን በታሪክ ቢያንስ ሦስት “መስራች አባቶች” አሉት።
የቀድሞው የቺካጎ ቡልስ እና የሎስ አንጀለሱ ላከር ተጫዋች የነበረው፣ አሁን የደቡብ ሱዳን የቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት የሆነው ሉል ዴንግ የተባለው የመጀመሪያው “መስራች አባት” ከአሰልጣኙ ሮያል ኢቪ ጋር በመሆን ጥሩ ልምዶችን በማካፈል ላይ ይገኛሉ። ይህ 18 ዓመት እንኳን ያልሞላው እና 218 ሴ.ሜ. ቁመት ያለው ተጫዋች ከቤተሰቦቹ ጋር በኡጋንዳ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ያደገ ሲሆን፥ የቡድን አጋሮቹ ከሆኑት ከማሪያል ሻዮክ እና ካርሊክ ጆንስ እንዲሁም ካማን ማሎውች ጋር በመሆን ታሪክ ለመስራት ተስፋ አድርገዋል።
ሁለተኛው “መስራች አባት” የተባለው ደቡብ ሱዳናዊ 231 ሴ.ሜ. ቁመት ያለው ማኑቴ ቦል ለታዋቂው የአሜሪካ ኤን ቢ ኤ ቡድን የሚጫወት ሲሆን፥ ለሀገሩ ወጣቶች ተስፋ ለመስጠት ጥረት አድርጓል። ማኑቴ በ 47 ዓመቱ በ 2002 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም ድካም ተለይቷል።
ሦስተኛው “መሥራች አባት” የጣሊያን ኮምቦኒ ማህበር ሚስዮናዊ ካህን የሆኑት አባ ዳንኤል ሞሼቲ ሲሆኑ፥ ከማራቶን እስከ እግር ኳስ ያላቸውን የህይወት ተመኩሮ ለሃገሬው ወጣት ያበረከቱ፥ “ወደ ሰላም፣ ፍትህ እና ክብር የሚያደርሰውን ረጅሙን ጎዳና” ያሳለፉ አባት ነበሩ።
በፓሪስ ኦሎምፒክ ደቡብ ሱዳን ከቅርጫት ኳስ በተጨማሪ በሉሲያ ሞሪስ የ100 ሜትር እና በአብርሃም ጉም የ800 ሜትር ሩጫ ውድድር እየተሳተፈች ሲሆን፥ በፓሪስ ኦሊምፒክ የስደተኞችን ቡድን እንዲወክሉ ከተመረጡት 36 አትሌቶች መካከል በስደተኛ ካምፖች ውስጥ ከእይታ ውጪ በሚደረጉ ውድድሮች የሚሳተፉ አትሌቶች ይወክላሉ።
ከእነዚህም ሌላ ታዋቂው ኬንያዊው የሰላም የስፖርት አምባሳደር እና የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆነውን የማራቶን ሯጭ ቴግላ ሎሮፕን፣ እንዲሁም ዶሚኒክ ሎባሉ የተባለ የ5000 ሜትር እና ፔሪና ሎኩሬ የተባለ የ800 ሜትር የሩጫ ውድድር አትሌቶችን በስደተኞች ቡድን ውስጥ ተካተዋል።
ከኢትዮጵያ፣ ትግራይ ክልል የመጣችው እየሩ ገብሩ በዘንድሮው የፓሪስ ኦሊምፒክ የስደተኞች ቡድንን ወክለው ከሚወዳደሩት ውስጥ አንዷ ናት። የብስክሌት ተወዳዳሪ የሆነችው እየሩ በህልሟ ላይ ማተኮሯ “ያንን የመከራ ወቅት እንዳሳልፍ ረድቶኛል” ብላለች።
በሰሜን ኬንያ በሚገኘው ካኩማ የስደተኞች ካምፕ የመጣው እና ያለ ቤተሰብ ያደገው ዪች ፑር ቤልም ከደቡብ ሱዳን ኦሊምፒክ ተወካዮች ውስጥ አንዱ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል። ዪች በ 2008 ዓ.ም. በተደረገው ኦሊምፒክ ከስደተኞች ቡድን ጋር ከተሳተፈ በኋላ በአሁኑ ወቅት የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
ለሁለት ሳምንታት የሚካሄደው እና በፈረንሳይ ፓሪስ እየተካሄደ ባለው የኦሊምፒክ ውድድር ከ200 በላይ አገራትን የሚወክሉ አትሌቶች፣ በ32 የስፖርት ዓይነቶች፣ ለ329 ሜዳሊያዎች እየተፎካከሩ ይገኛሉ።