ፈልግ

በሱዳን በተከሰተው ግጭትና የአየር ንብረት ጉዳይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል በሱዳን በተከሰተው ግጭትና የአየር ንብረት ጉዳይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል  (AFP or licensors)

የሱዳን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹአን ጳጳሳት ሰብአዊ ቀውሱ እንዲቆም ሰላማዊ ውይይት እንዲደረግ ጠየቁ

ሱዳን ተጠናክሮ በቀጠለው የእርስ በርስ ጦርነት እና ባስከተለው ከፍተኛ መፈናቀል ምክንያት አሳሳቢ ለሆነ የሰብአዊ ቀውስ እየተጋረጠች ባለችበት በአሁኑ ወቅት፥ የሀገሪቱ ብጹአን ጳጳሳት እነዚህን “አስከፊ” ሰብአዊ መዘዞችን ለመቅረፍ የሰላም ድርድር እንዲደረድ ጥሪ አቅርበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሱዳን በጦር ኃይሎች እና በፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ከፍተኛ ግጭት ውስጥ ትገኛለች፡፡ በግጭቱ በርካቶች ሲገደሉ፣ ከ4.6 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል፡፡

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በእሁዱ የመልአከ እግዚያብሄር ጸሎት ላይ ሀገሪቱ በሁሉም ዋና ዋና ከተሞቿ በተከሰቱት ግጭቶች ጋር እየተናነቀች ለምትገኘው ሱዳንን ጨምሮ በጦርነት እና በዓመፅ ለተጎዱትን ለሁሉም ሃገራት ህዝቦች ጸሎት አድርገዋል።

በዩናይትድ ስቴትስ አደራዳሪነት በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እና በሱዳን ጦር ሃይሎች መካከል እየተደረገ ያለው ውይይት የተወሰኑ መሻሻሎች ቢያሳይም ለሳምንታት እየተራዘመ ባለበት በአሁኑ ወቅት ሰብአዊ ቀውሱ በከፍተኛ ሁኔታ መቀጠሉ ተነግሯል።

የሱዳኑ ወታደራዊ መሪ ጄኔራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሀን ነሃሴ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ረቡዕ ዕለት ከተቃጣባቸው የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃት መትረፋቸውን የሀገሪቱ ጦር አስታውቋል። ቡርሃን የተረፉት በምስራቅ ሱዳን በተካሄደው የጦር ሠራዊት ምረቃ ስነ ስርዓት ላይ የ5 ሰዎች ህይወት ካለፈበት የድሮን ጥቃት መሆኑ ተገልጿል፡፡

ሱዳናዊው ካህን ‘አስፈሪ ሁኔታ’ ማለታቸው
የአል-ኡባይድ ሀገረ ስብከት ካህን የሆኑት አባ ባዮንግ ክዎል ዴንግ ከቫቲካን ፊደስ የዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በዋና ከተማው እና በተቀረው የሀገሪቱ ክፍል ባለው “አስፈሪ ሁኔታ” ምክንያት ከሌሎች በርካታ የቤተክርስቲያኒቱ አባላት ጋር ካርቱምን ለቀው ለመውጣት መገደዳቸውን ገልጸው፥ “ባለው አስከፊ ሁኔታ ምክንያት ወደ ጁባ (የደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ) መሸሽ ነበረብኝ” ሲሉ የሱዳን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጳጳሳት ጉባኤ ዋና ጸሃፊ የሆኑት አባ ክዎል ከገለጹ በኋላ “እንደ አብዛኛው የቤተክርስቲያኑ አባላት በሱዳን የነበርንባቸውን ቦታዎች መልቀቅ ነበረብን፣ ምክንያቱም አከባቢዎቹ በጣም አደገኛ ሆነዋል፥ ነገር ግን በየጊዜው አዳዲስ መረጃዎችን እየተቀበልኩ እገኛለሁ” ብለዋል።

በሱዳን በተከሰተው ግጭት ምክንያት እርዳታ ፍለጋ ወደ ደቡብ ሱዳን የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር መጨመሩንም ዘገባዎች እያሳዩ ይገኛል።

“በሚያሳዝን ሁኔታ” ይላሉ አባ ክዎል፣ “በአስከፊ ሁኔታ ሁሉም ነገር ተባብሷል… በሱዳን የውሃ፣ የምግብ እና የመድኃኒት እጥረት አለ፣ ይህም የሁሉንም ስደተኞች ሁኔታን ያባብሰዋል” በማለት አክለዋል።

ምንም እንኳን ፈታኝ ቢሆንም፣ በሁለቱም አገሮች የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመርዳት በአከባቢው የምትገኘው አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ጥረቷን ቀጥላለች ተብሏል።

አንዳንዶቹም ከዚህን በፊት በደቡብ ሱዳን ተከስቶ በነበረ ግጭት ምክንያት ወደ ሱዳን ተሰደው የነበሩት ሲሆኑ፥ አሁን በተመሳሳይ ሁኔታ ወደ ፈለሱበት ክልል እንዲመለሱ ተገደዋል።

አባ ባዮንግ ክዎል በካርቱም የሚኖር አንድ ዘመዳቸው “በግጭቱ ያልተጠቃ የሀገሪቱ ጥግ የለም፣ ጦርነቱ በሁሉም ቦታ እየተካሄደ ነው” ብሎ እንደነገራቸው ተናግረዋል።

በአሜሪካ አደራዳሪነት የሚደረገው የሰላም ድርድር
ነሃሴ 8 ቀን 2016 ዓ.ም. ረቡዕ ዕለት በጄኔቫ የሚካሄደው የሰላም ድርድር በዩናይትድ ስቴትስ የሚደገፍ ሲሆን፥ ሆኖም በጂዳህ ያለ ስምምነት የተጠናቀቀውን የሰላም ድርድር ተከትሎ የሱዳን መንግስት እና የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ተሳትፎ ገና አልተረጋገጠም።

ይህ ውይይት የሱዳን ህዝቦች ነፃ አውጪ ንቅናቄን የመሳሰሉ ቡድኖች ከድርድሩ መገለላቸውን ተከትሎ ውይይቱ ከአሁኑ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል ተብሏል።
 

14 August 2024, 12:41