ፈልግ

በኩርስክ ክልል ውስጥ የሚገኝ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰበት የመኖሪያ ሕንፃ - ፎቶ ማህደር በኩርስክ ክልል ውስጥ የሚገኝ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰበት የመኖሪያ ሕንፃ - ፎቶ ማህደር 

በሺዎች የሚቆጠሩ የዩክሬን ወታደሮች ወደ ሩሲያ ግዛት ዘልቀው መግባታቸው ተነገረ

ዩክሬን ወደ ደቡባዊ ምዕራብ ሩሲያ የኩርስክ ክልል ዘልቃ በመግባት የፈጸመችውን ድንገተኛ ወረራ ተከትሎ የኪየቭ መንግስት ባወጣው መግለጫ በሺህ የሚቆጠሩ የዩክሬን ወታደሮች በጥቃቱ መሳተፋቸውን የገለጸ ሲሆን፥ ሞስኮ ጥቃቱን ለማስቆም እየተጠቀምኩበት ነው ያለችው አወዛጋቢውን የቫኪዩም ቦምብ ጥቃት ጉዳይ የተለያዩ ዘገባዎች እያሳዩ ይገኛሉ።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ዩክሬን ወደ ደቡባዊ ምዕራብ ሩሲያ የኩርስክ ግዛት ዘልቃ በመግባት የፈጸመችውን ድንገተኛ ወረራ ተከትሎ ሁለቱ አገራት የገቡበት ከባድ ውጊያ ስድስተኛውን ቀኑን ይዟል።

በዓለማችን ትልቁ የሚባለው የኒውክሌር ጣቢያ በሚገኝበት በኩርስክ ግዛቷ ያልተጠበቀ ጥቃት የገጠማት ሩሲያ የአስቸኳይ ጊዜ ከማወጅ በተጨማሪ ተጠባባቂ ጦሯንም ጠርታለች።

ይሄን ተከትሎ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ሠራዊታቸው የሩሲያን ድንበር ተሻግሮ እያጠቃ መሆኑን ለመጀመርያ ጊዜ አምነዋል።

የሁለቱ አገራት ጦርነት ከተጀመረበት ወቅት በተለየ ሁኔታ ከፍተኛ እና ያልተጠበቀ ነው የተባለው የማክሰኞ፣ ሐምሌ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. የዩክሬን ጥቃት ወደ 1 ሺህ የሚጠጉ የዩክሬን ወታደሮች የተሳተፉበት ነው ተብሏል።
በዚህ ስድስተኛ ቀኑን በያዘው ጦርነት ሩሲያ በሶስት የድንበር ክልሎች ላይ ሰፊ የጸጥታ አስተዳደር መዘርጋቷም ተነግሯል። በተመሳሳይ ጊዜ ቤላሩስ ኪየቭ የአየር ክልሌን ጥሳለች በሚል ክስ ወደ ዩክሬን ድንበር ተጨማሪ ወታደሮቿን መላኳን ዘገባዎች እያሳዩ ይገኛሉ።

ሆኖም የሩሲያ ወታደሮች ለጥቃቱ በቂ የዝግጅት ጊዜ ባለማግኘታቸው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከስፍራው ለቀው እንዲወጡ መደረጉን የሩሲያ ባለስልጣናት አምነዋል። በመሆኑም የዩክሬን ሠራዊት ገፍቶ መምጣቱን ተከትሎ በኩርስክ ክልል ድንበር 76ሺህ የሩሲያ ነዋሪዎች ወደ ሌላ ቦታ እንዲዘዋወሩ መደረጉን የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ላለፉት 18 ወራት ጦርነቱን በበላይነት ስትመራ ለነበረችው ሩሲያ ይህ ግዛቷን ዘልቆ የገባው ጥቃት ጦሯን እንዲሁም ክሬምሊንን ያስደነገጠ ነው ተብሏል።

ሩሲያ በአሁኑ ወቅት ጥቃቱን በመመከት እና ዘልቀው የገቡ የዩክሬንን ወታደሮችን ከማስወጣት በተጨማሪ ይህንን ጥቃት ባለመከላከል ከሕዝቡ የሚቀርብን ወቀሳ ለማረጋጋት የሩሲያ መንግሥት እየጣረ ይገኛል ተብሏል።

ምዕራባውያኑ የዩክሬን አጋሮች ጦርነቱ የበለጠ እንዳይጋጋል ቢሰጉም፣ በአሁኑ ወቅት ኪዬቭ እያደረገችው ያለውን ድንበር ዘለል ጥቃት ራሷን የመከላከል መብት እንደሆነ ነው የሚያዩት።

አንዳንድ የቪዲዮ ምስሎች እንደሚያሳዩት በአካባቢው በርካታ የተቃጠሉ የሩሲያ ወታደራዊ መኪናዎችን ያሳዩ ሲሆን፥ ቪዲዮው የተቀረፀው ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ከምትዋሰነው ድንበር ከ20 ማይል (36 ኪሎ ሜትር) ርቃ በምትገኘው በሩሲያ ኦክቲያብርስኮ ከተማ በሚገኘው ኢ-38 አውራ ጎዳና ላይ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

ሞስኮ ዩክሬን በኩርስክ ግዛት ላይ ያካሄደችውን አስደንጋጭ ወረራ ለመበቀል የጸረ ሽብርተኝነት ዘመቻ አካል በሆነው በዩክሬን ሃይሎች ላይ ቴርሞባሪክ ቦምብ ወይም ቫክዩም ቦምብ መጠቀሟን ገልፃለች። የቦምቡ ፍንዳታ በሚደርስበት አከባቢ የተገኘ ማንኛውም የሚተነፍስ ነገር የልብ እና የደም ቧንቧው፣ ጨጓራው፣ ሳምባው እና የመስማት ብቃቱ እንዲሁም ማዕከላዊ የነርቭ ስርዓቱ በቅጽበት ውስጥ ከጥቅም ውጪ ይሆናሉ።

ሩሲያ የካቲት ወር 2014 ዓ.ም. ላይ ወረራውን ከጀመረች ከሳምንታት በኋላ የዩክሬን ባለስልጣናት የሩሲያ ጦር መሳሪያውን ሲጠቀሙበት እንደነበር ገልጸው የነበረ ሲሆን፥ ሞስኮ እንዲህ ዓይነት የጦር መሣሪያዎችን ማሰማራቷ ሲነገር ይህ የመጀመሪያው አይደለም ተብሏል።

ቫክዩም ቦንቦችን መጠቀም የዓለም አቀፍ ህግ መጣስ አይደለም ነገር ግን ሲቪሎችን ዒላማ ያደረገ ጥቃት ከተፈጸመ ህግ እንደመጣስ ይቆጠራል ተብሏል።

በተጨማሪም ኪየቭ ትናንት ሌሊት ጥቃት የደረሰባት ሲሆን፥ የዩክሬን ባለስልጣናት እንዳስታወቁት አንድ የ35 ዓመት ሰው እና የአራት ዓመት ወንድ ልጁ በሩስያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ሚሳኤል ጥቃት ተገድለዋል።

የዩክሬን የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ማዕከል እንደገለጸው በኪየቭ ከተማ ብሮቫሪ አውራጃ ውስጥ በሚገኝ የመኖሪያ አከባቢዎች ላይ የመሳሪያ ፍንጥርጣሪዎች እየወደቁ በነበረበት ወቅት ይህ ሁኔታ መከሰቱን የገለጸ ሲሆን፥ ሩሲያ ዩክሬን ላይ ሙሉ በሙሉ ወረራ ከጀመረችበት ጊዜ በኋላ ከተገደሉት እና ከቆሰሉት በመቶ ሺዎች ከሚቆጠሩት ሰዎች መካከል ይህ የቅርብ ጊዜ አሳዛኝ አደጋ መሆኑም ተገልጿል።
 

13 August 2024, 15:49