ዩኒሴፍ እና የዓለም ጤና ድርጅት በጋዛ ውስጥ የፖሊዮ ክትባት መስጠት የሚያስችል ሰብዓዊ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠየቁ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የተባበሩት መንግስታት ኤጀንሲዎች እንደሚሉት የውጊያው ለቀናት መቋረጥ ህጻናት እና ቤተሰቦች በሰላም ወደ ጤና ተቋማት እንዲሄዱ እና የማህበረሰብ አገልግሎት ሰጭ ሰራተኞች ለፖሊዮ ክትባት የጤና ተቋማትን ማግኘት ወደማይችሉ ህጻናት እንዲደርሱ ያስችላቸዋል ያሉ ሲሆን፥ ሰብአዊ የተኩስ አቁም ካልተደረገ የክትባት ዘመቻው ፈጽሞ የሚቻል አይሆንም ተብሏል።
የሰብዓዊ ተኩስ አቁም ስምምነቱ ይሁንታ ካገኘ በነሃሴ እና በመስከረም ወራቶች መጨረሻ ላይ የሁለት ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በጋዛ ሰርጥ ላይ ይከፈታል ተብሎ ይጠበቃል።
በዘመቻው በእያንዳንዱ ዙር ‘ዝርያ ሁለት’ የተባለው አዲሱ የፖሊዮ ክትባት ሁለት ጠብታዎች ከአስር ዓመት በታች ለሆኑ ከ640,000 በላይ ህጻናት ይሰጣል ተብሏል።
ስለ ድንገተኛ ወረርሽኝ የተሰጡ ማስጠንቀቂያዎች
ባለፈው ወር በጋዛ ውስጥ የፖሊዮ ወረርሽኝ በቅርቡ ይከሰታል ተብሎ የተለያዩ ማስጠንቀቂያዎች ሲሰጡ ነበር። ከዚህም ባለፈ በቅርብ ጊዜ በተገኘው ግኝት በቆሻሻ ውሃ ውስጥ በተገኙ ምልክቶች ቫይረሱ ሊሰራጭ እንደሚችልም ይታመናል።
ከንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ ከቆሻሻ አወጋገድ እና ከጤና ስርዓቱ ጋር በተያያዙ በሚታዩ ትላልቅ ችግሮች የተነሳ የመስፋፋት እድሉ ከፍተኛ ነው የተባለ ሲሆን፥ በጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አንድ ሽንት ቤት የሚጋሩበት እና እያንዳንዱ ሰው በቀን ከሁለት ሊትር ያነሰ ውሃ ብቻ እንደሚደርሰው በተገለጸበት በዚህ አከባቢ ችግሩ አሳሳቢ እንደሆነም ይታመናል።
ክትባት ውጤታማ የመከላከያ ዘዴ ሊሆን ይችላል
በሳይንስ ሦስት ዓይነት የፖሊዮ ቫይረሶች ዝርያ እንዳሉ የሚታወቅ ቢሆንም ሦስቱም በሚያስከትሏቸው የሕመም ምልክቶች እንዲሁም በሚያደርሱት የጤና ጉዳት ተመሳሳይ ናቸው።
ፖሊዮ ለሕይወት አስጊ የሆነ በሽታ ሲሆን፥ በዋነኝነት የሚያጠቃው ከ 5 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን እና ጨቅላ ሕፃናትን እንደሆነ እንዲሁም ማንኛውም ያልተከተበ ሰው ሊይዝ እንደሚችል የተረጋገጠ ነው። ለፖሊዮ ምንም ዓይነት መድኃኒት የሌለ ሲሆን፥ ነገር ግን በስፋት የሚሰጥ ክትባት ውጤታማ የመከላከያ ዘዴ ሊሆን ይችላል።
ይህ በጣም ተላላፊ የሆነ በሽታ ከሰው ወደ ሰው በፍጥነት እንደሚተላለፍ እና ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው በበሽታው ከተያዘ ሰው ሰገራ ጋር ንክኪ ካደረገ እና አፉን ሲነካ፣ እንዲሁም በቫይረሱ በተበከለ ውሃ ወይም ምግብ አማካይነት ወደ ሰውነት ውስጥ ይገባል።
ፖሊዮ አብዛኛውን ጊዜ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆነ ሕፃናትን የአከርካሪ አጥንትን የሚያጠቃ ቫይረስ ነው።
የዓለም ጤና ድርጅት ከ200 የፖሊዮ ተጠቂዎች አንዱ ወደ ማይቀለበስ የጤና ቀውስ ወይም ልምሻነት እንደሚያድግ ተናግሯል። በዚህም የመተንፈሻ አካል ጡንቻ የተጎዳ ከሆነ ደግሞ ሞት ሊከሰት እንደሚችል የድርጅቱ መረጃ ያመለክታል።