የእስራኤል ጥቃት እየጠነከረ በመምጣቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሊባኖሳዊያን መሰደዳቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ሄዝቦላህ ወደ ሰሜን እስራኤል ከ300 በላይ ሮኬቶችን በመተኮስ በሰጠው ምላሽ 6 ሰዎች ቆስለዋል ሲል ጦሩ አስታውቋል።
ጥቃቱ የተፈጸመው ሰኞ ዕለት እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ ላይ ባካሄደችው የአየር ድብደባ ወደ 500 የሚጠጉ ሰዎች ህይወት ማለፉን ተከትሎ ነው።
እስራኤል ሰኞ ዕለት በሊባኖስ ላይ የፈጸመችው ጥቃት በሃገሪቱ ላይ ካለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ ከተፈጸሙት ጥቃቶች እጅግ የከፋው እንደሆነም ጭምር ተነግሯል።
በጋዛ ጦርነት ምክንያት በእስራኤል እና በሄዝቦላህ መካከል በተቀሰቀሰው ድንበር ተሻጋሪ ጦርነት አብዛኛዎቹ የሄዝቦላህ ታጣቂዎች የሆኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሞቱ ሲሆን በሁለቱም አገራት የድንበር አካባቢዎች የሚኖሩ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል።
ዓለም አቀፍ ምላሾች
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት በሊባኖስ ያለውን ቀውስ ለማስቆም በዚህ ሳምንት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት 'ተጨባጭ የሆኑ እቅዶችን' እንደሚያቀርብ በመግለጽ፥ ዋሽንግተን ጥቂት ተጨማሪ ወታደራዊ አባላትን ወደ ክልሉ እንደምትልክ አስታውቋል።
በብራስልስ የአውሮፓ ህብረት የውጭ ፖሊሲ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል ግጭቱ ወደ ሙሉ ጦርነት እየተቀየረ መሆኑን ያስጠነቀቁ ሲሆን፥ በተመሳሳይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ በሁለቱ ሃገራት መሃከል የተከሰተው ግጭት ለሲቪሎች 'ከባድ ስጋት' ሆኗል ሲሉ ገልጸዋል ።
ሄዝቦላህ ሃማስ መስከረም 26 በእስራኤል ላይ የወሰደውን ድንገተኛ ጥቃት በመደገፍ ወደ እስራኤል በርካታ ሮኬቶችን ማስወንጨፉን ተከትሎ በሊባኖስ እና እስራኤል ድንበር ላይ ያለው ውጥረት ከባለፈው ዓመት ጀምሮ እየተባባሰ መሆኑን እና በጋዛ የተኩስ አቁም እስካልመጣ ድረስ ወደ ኋላ እንደማይልም ተናግሯል። ሁለቱ ቡድኖች በኢራን የሚደገፉ ሲሆን በእስራኤል፣ በእንግሊዝ እና በሌሎች አገራት ደግሞ በአሸባሪነት ተፈርጀዋል።