በፓፑዋ ኒው ጊኒ የጎሳ ግጭት መቀስቀሱ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በሃገሪቱ በተደጋጋሚ በሚከሰተው አወዛጋቢው የወርቅ የማምረት ሂደት ምክንያት በተቀናቃኞቹ ጎሳዎች መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ከቀናት በፊት የጀመረ ሲሆን፥ ወደ ሌላ አከባቢዎችም በመዛመት በምዕራብ ፖርጄራ ሸለቆ ውስጥ መንሰራፋቱ ተነግሯል።
ይህ ግጭት የተከሰተው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በሃገሪቷ በተደጋጋሚ ጊዜያት በሚነሱ የጎሳ ግጭቶች ምክንያት ትልቅ ችግር ውስጥ የገባውን ሕዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመጎብኘት ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉዞ ወቅት የሰላም ጥሪ ካቀረቡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ወደ ደቡብ ምስራቅ እስያ እና ኦሽንያ አህጉራት ባደረጉት ሃዋሪያዊ ጉብኝት ጳጉሜ 1 ቀን 2016 ዓ.ም. የፓፑዋ ኒው ጊኒ ዋና ከተማ የሆነችውን ፖርት ሞርስቢን በጎበኙበት ወቅት የሀገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት ፍትሃዊ በሆነ ልማት እና ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ለመጠቀም ባለሥልጣናቱ የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ በመጠየቅ፥ “ሃገሪቷ ያላት የተፈጥሮ ሃብት ለመላው ማኅበረሰብ እኩል እንዲዳረስ ከእግዚያብሔር የተሰጠ ነው” ብለዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በማከልም “የጎሳ ግጭት ብዙ ጉዳት የሚያስከትል፣ ሰዎች በሰላም እንዳይኖሩ የሚከለክል እና ልማትን የሚያደናቅፍ በመሆኑ በአስቸኳይ እንደሚቆም ተስፋ አደርጋለሁ” ካሉ በኋላ፥ “ስለዚህ የጎሳ ግጭቱን ለማስቆም ሁሉን ሰው ኃላፊነት ወስዶ እንዲሰራ እጠይቃለሁ” በማለትም አሳስበዋል።
በኤንጋ ግዛት ውስጥ የተከሰተ ግጭት
በሀገሪቱ ውስጥ ካሉት ግዛቶች ተራራማ የተፈጥሮ አቀማመጥ ባለው የኤንጋ ግዛት ውስጥ እሁድ ዕለት በተቀሰቀሰው ግጭት ቢያንስ 20 ሰዎች መሞታቸው የተዘገበ ሲሆን፥ የፓፑዋ ኒው ጊኒ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት ማት ባጎሲ ግን የሟቾች ቁጥር 50 ሊደርስ እንደሚችል ተናግረው፥ “አሁን ላይ ተጨማሪ የጸጥታ ሃይሎች ወደ ከተማዋ መግባት ስለጀመሩ ይህ ምን አይነት ተጽእኖ እንደሚያሳድር መታየት አለበት” ብለዋል።
የብሔራዊ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ፥ ብጥብጡ ተባብሶ በመቀጠሉ ቅዳሜ እለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ እንደነበር ገልፀው፥ ፖሊስ ነዋሪዎችን እና መሰረተ ልማቶችን ለመጠበቅ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሆነ ገልጿል።
ኮሚሽኑ በሰጠው መግለጫ ሁኔታው እየተባባሰ የመጣው ህገወጥ የማዕድን አውጪዎች እና ህገወጥ ሰፋሪዎች በባህላዊ የመሬት ባለቤቶች ላይ ጥቃት በማድረስ የአካባቢውን ማህበረሰብ ለማሸበር ሁከት እንደጀመሩ በመግለጽ፥ በአካባቢው የሚገኘው የኒው ፖርጌራ የወርቅ ማዕድን ማውጫ አብዛኛውን ሥራውን ያቆመው በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል።
እየጨመረ የመጣው የደህንነት ስጋት
የጎሳ ግጭት በፓፑዋ ኒው ጊኒ እየጨመረ የመጣ የደህንነት ችግር እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ በተለይ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ 2000 የሚጠጉ ሰዎችን ከገደለው የመሬት መንሸራተት አደጋ በኋላ ማገገም ባቃታት የኤንጋ ክልል ችግሩ በከፍተኛ ሁኔታ መስፋፋቱ ተገልጿል።
ይህ በእንዲህ እያለ ፓፑዋ ኒው ጊኒ መስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም. ሰኞ ዕለት ሃገሪቱ ከጎረቤት አውስትራሊያ ነፃ የወጣችበትን 49ኛ ዓመት አክብራለች።