የእምነት ሴቶች ለሰላም እና የጦርነት ቁስሎችን ለመፈወስ በህብረት እየሰሩ ነው
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
‘የእምነት ሴቶች ለሰላም’ የሚባለው ንቅናቄ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በመሆን የኢጣሊያን ግዛት በሆነው ትሬንቶ፣ ሞንታኛጋ ከተማ ተዘጋጅቶ እሁድ እለት የተጠናቀቀው ይህ ስብሰባ የሰላም፣ የተለያዩ ሃይማኖቶች መካከል የሚደረግ ጸሎት እና “የሰላም መንገድ” በሚል መሪ ሃሳብ የተለያዩ አውደ ጥናቶች ቀርበውበታል።
ከተለያዩ ትውልዶች የተውጣጡ አርባ የሚያህሉ ሰዎች ከአርብ ነሐሴ 24 ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት አብረው የቆዩ ሲሆን፥ “የሰላምን ትርጉም እና አስፈላጊነት በጥልቀት ለማሰላሰል እና “በጦርነት ውስጥ ባለው ዓለም ውስጥ የሰላም ትርጉም ምንድነው?” በሚለው ጥያቄ ዙሪያ ሲወያዩ ነበር።
የእምነት ሴቶች ለሰላም የሚለው ንቅናቄ ከ15 ዓመታት በፊት በኢየሩሳሌም የተመሰረተ፣ ያልተለመደ የሰላም ልምድን በተጨባጭ ሁኔታ ለማስፋፋት፣ የጭፍን ጥላቻን ግንቦችን ለማፍረስ እና በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ እውነተኛ ውይይት ለመፍጠር፣ በግጭት ዞኖች እንዲሁም ውጥረት ባለባቸው አገሮች እና በሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች ውስጥ አዳዲስ የሰላም መንገዶችን የመፈለግ ዓላማ ያነገበ ነው።
ካሪትሮ ፋውንዴሽን፣ ሸማ ማህበር፣ ህብረት ለትልቅ ለውጥ እና ሊድ ኢንተግሪቲ የተባሉ ተቋማት ንቅናቄው ስብሰባውን እንዲያዘጋጅ የረዱ አካላት መሆናቸውም የተገለጸ ሲሆን፥ የእምነት ሴቶች ለሰላም ንቅናቄ መስራች የሆኑት ሊያ ቤልትራሚ ከቫቲካን ዜና ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ይቀርባል፦
ጥያቄ፦ የእምነት ሴቶች ሰላምን ለማስፈን ምን ልዩ አስተዋጽዖ ሊያበረክቱ ይችላሉ?
መልስ፦ በእምነት ውስጥ የሚኖሩ ሴቶች ለእርቅ መንገድ ትልቅ አስተዋፅዖ ያደርጋሉ። የተከፋፈለ ህዝብ፣ ሁለት እርስ በርስ የሚጣሉ ህዝቦች፣ ሊለካ የማይችል ቁስሎችን ያመነጫሉ፥ ይህንንም ለማስታረቅ እና ቁስሉን ለመፈወስ ትልቅ ጥንካሬ እና የፈጠራ ሴት አቀራረብን ብቻ ይጠይቃል። ስለዚህ ሴቶች ጠንቅቀው ማወቅ እና ወደ እምነታቸው አቅጣጫ መሄድ አለባቸው እንዲሁም በተቀባይነት እና በአቃፊነት መንገድ ፈውስ ማምጣት ይቻላል።
በተለይም በአሁኑ ጊዜ ግጭቶች በጣም ተጠናክረው በቀጠሉበት እና የሰላም ተስፋው በተወሰነ ደረጃ የጠፋበት፣ እንዲሁም ለሰላም መንገድ የሚተጉ ሰዎች መነሳሳት በቀነሰበት በዚህ ወቅት ነው የእምነት ሴቶች ለሰላም ንቅናቄውን የጀመረው። በሰላም ሰራተኞች በኩል የሰላም ብርሃኑን እንደገና ለማቀጣጠል እራሳችንን የበለጠ አጠናክረን መገኘት አለብን፥ ምክንያቱም እያንዳንዱ ሰው በራሱ አካባቢ ምን ማድረግ እንዳለበት ያውቃል።
ሆኖም ግን አንድነት ሊሰማን ይገባል፣ እናም በውስጣችን ያለው ብርሃን የሚያበራና በዚህ ድርብ ጦርነት ውስጥ ማቆም የሌለበት ብርሃን መሆኑን መረዳት አለብን፥ ምክንያቱም ይህ አካላዊ እና የቃላት ጦርነት ነው፣ የግንኙነት ጦርነት ነው። ጦርነቱ ብዙ ጊዜ መስማት የተሳነን እንድንሆን እና ወደፊት የምንሄድባቸውን መንገዶች እንዳንፈልግ ያደርገናል።
ጥያቄ፡- የተለያዩ ግጭቶች እየተደረጉ ባለበት በአሁኑ ወቅት ስለ ሰላም ስትወያዩ ዓላማችሁ ምንድን ነው?
መልስ፦ እኛም በዚህ ሁኔታ ላይ ብዙ ተወያይተናል፥ እናም እያንዳንዳችን ሰላምን ሊያመጡ በሚችሉ ነገሮች ዙሪያ ላይ ሀሳባችንን አካፍለናል፥ ለእያንዳንዱ ሁኔታ ግልጽ እና ትክክለኛ መፍትሄዎች እንደሌሉ እንገነዘባለን፥
በመጀመሪያ ደረጃ በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ አንድ በሚያደርጉን ነገሮች ሃሳብ ለመካፈል እና ለመደማመጥ፣ ብሎም የእነዚህ ጦርነቶች ሰለባ ከሆኑት ጋር ከልብ በመነጨ ስሜት ለመወያየት እና ሃሳባቸውን ለማዳመጥ ፈቃደኛ መሆናችን ነው።
ጥያቄ፦ በስብሰባው ውስጥ ምን የተለመዱ ነገሮች ነበሩ?
መልስ፦ በመጀመሪያ ደረጃ ያዋሃደን እና አንድ ያደረገን ነገር ለሰላም ያለን ራዕይ ነው፥ በሃሳብ ውስጥ፣ በአገር ውስጥ እና በማኅበረሰብ ውስጥ ስምምነት ሲፈጠር፣ አብዛኞቻችን የሰላም ስሜት ብለን የምንገልጸው ይህንን ነው። ይህንን ስምምነት እንዴት ማግኘት እንደሚቻል ለማወቅ በእርግጠኝነት የበለጠ የተወሳሰበ ነው፥ ነገር ግን ከሁሉም ሰው የመጣው ነገር ቢኖር ፍትህ ፍለጋ ነው። ተሳታፊዎቹ ይዘው የመጡት ሃሳብን የመጋራት እና የማዳመጥ ችሎታ፣ ሌሎችን በማዳመጥ ውስጥ መሳተፍ እና ጭፍን ጥላቻን ለማሸነፍ መሞከርን ነው።
ጥያቄ፡- ሴቶች ዛሬ ለዓለም ሰላም ምን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ?
መልስ፦ ሴቶች ብዙ ሊሠሩ ይችላሉ። እንደ አለመታደል ሆኖ፣ አንዳንድ ጊዜ ሴቶች በእውነቱ ውሳኔ በሚደረግባቸው ቦታዎች ላይ ተሳታፊ አይደረጉም፥ እኔ ግን ካለኝ ልምድ በተለይም አፍሪካ ውስጥ ሴቶች የስልጣን ቦታ ባይኖራቸውም የለውጡ አንቀሳቃሾች ናቸው ማለት እችላለሁ።
ከትናንሽ ነገሮች፣ ከትናንሽ ተግባራት፣ ከትናንሽ ማህበረሰቦች ጀምሮ እስከ ትላልቅ የስልጣን ቦታዎች ድረስ እውነተኛ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ መሳሪያዎች ናቸው። በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ የሴቶች ሚና ሁል ጊዜ ማደግ እና ሴቶችን መደገፍ እንደሚችል ተስፋ ይደረጋል።
ሊደረግ የሚችለው አስተዋፅዖ እነርሱን መደገፍ ነው፥ በተለይም እራስን የመግለጽ መብት በተከለከሉ ቦታዎች ሁልጊዜ እንዲታዩ ማድረግ፣ ስለ እሱ ማውራት፣ አንዳንድ ሁኔታዎችን እንዲረሱ አለመፍቀድ፣ ምክንያቱም አንዳንድ ሁኔታዎች እንዳይረሱ ግንዛቤን ማሳደግ በእርግጠኝነት አስፈላጊ መሣሪያ ነው።
ጥያቄ፦ ከዚህ ስብሰባ በኋላ እንዴት ተጠናክሮ ወደፊት መሄድ ይቻላል ብለው ያስባሉ?
መልስ፦ በእርግጠኝነት በጠንካራ ቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዛለን። እነዚህ ሃሳብን የመጋራት፣ የመደማመጥ፣ አብሮ የመሆን እንዲሁም ሃሳቦችን፣ ፍርሃቶችን፣ ህልሞችን እና የወደፊት ፕሮጀክቶችን የመጋራት ጊዜዎች ጥሩ መነሳሻዎች ናቸው። ይህ ትልቅ ጠቀሜታ አለው፥ የእነዚህ ዝግጅቶች ታላቅ ጥንካሬ ነው። እያንዳንዳችን በራሳችን አውድ ውስጥ፣ በስራ ቦታም ቢሆን፣ እነዚያን መሰረታዊ የሆኑ ለውጦችን ለማምጣት በቁርጠኝነት ከዚህ ወደ ፊት መጓዝ እንደምንችል አምናለሁ።
ጥያቄ፦ እርስዎ ከአሲሲ ህዝቦች መሃከል የተገኙ እና በዚህ ዓመት የሰላም ተጓዦች ሽልማትን ‘ለእምነት ሴቶች ለሰላም ንቅናቄ’ የሸለመው የዓለም አቀፍ የሰላም ማእከል ፕሬዝዳንት ነዎት፥ ይሄንን እንዴት ልታደርጉ ቻላችሁ?
መልስ፦ በመጀመሪያ ደረጃ እነዚህን ስብሰባዎች ማደራጀት እና ከተለያዩ ሁኔታዎች የመጡ ሴቶችን ማሰባሰብ አስፈላጊ ነው፥ ይህ ቀጣይነት ያለው ውይይት የማፈላለግ ስራ ሲሆን፥ ለራሱ ሲል ውይይት ብቻ ሆኖ የማይቀር ነገር ግን በማህበረሰቡ ውስጥ በለውጥ እና በፍትህ ተግባራት ተጨባጭ ሥራ እየሰራ ይቀጥላል። ስለዚህ ይህ ተግባር ለሰላም ብለው ለሚጓዙ መንፈሳዊ ነጋዲያን ሙሉ እውቅና ሊሰጥ የሚገባው ነው ብለን እናምናለን።