ፈልግ

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን የሚያስጠነቅቅ የአውሮፓ ድንበር ማቋረጫ ማስጠንቀቂያ - የማህደር ፎቶ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን የሚያስጠነቅቅ የአውሮፓ ድንበር ማቋረጫ ማስጠንቀቂያ - የማህደር ፎቶ 

የአውሮፓ ህብረት መሪዎች ህገወጥ ዝውውርን ለመከላከል ለህግ አስከባሪ አካላት ጠንከር ያሉ መመሪያዎችን እንደሚያወጡ ቃል ገቡ

በየዓመቱ ጥቅምት 8 ቀን የሚከበረው የአውሮፓ ህብረት የፀረ-ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ቀን የህገ ወጥ ዝውውር አስከፊ እውነታ ግንዛቤን ያሳድጋል የተባለ ሲሆን፥ በአውሮፓ ህብረት ሃገራት ውስጥ በየዓመቱ ወደ 7,000 የሚጠጉ ሰዎች በዚህ ጉዳይ እንደሚጎዱ እና ከእነዚህ ውስጥ 15 በመቶ የሚሆኑት ህጻናት እንደሆኑ፣ በተለይ እንደ ዩክሬን እና መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ያሉ በጦርነት ከሚታመሱ ሀገራት የመጡ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ለዚህ አደጋ ይበልጡኑ ተጋላጭ እንደሆኑ ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም. በተከበረው 10ኛው የዓለም የጸሎት እና የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የግንዛቤ ማስጨበጫ ቀን ላይ ባስተላለፉት መልእክት በየደረጃው ያለው ህብረተሰብ ይሄንን ህገወጥ ድርጊት እንዲከላከል እንዲሁም የተጎጂዎችን ምስክርነት እና ድምጽ የሌላቸውን ሰዎች ልብ ብለው እንዲሰሙ አሳስበዋል።

ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር “በሰው ልጅ ላይ ያለ የተከፈተ ቁስል ነው” ሲሉ ደጋግመው ያወገዙት ብጹእ አባታችን ፤ ይህ ወረርሽኝ አውሮፓን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ መሆኑን ገልጸው፥ በተለይም በዩክሬን እና በመካከለኛው ምስራቅ በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት በርካታ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ለህገወጥ ዝውውር እና ለጉልበት ብዝበዛ የተጋለጡ እንደሆነ ተናግረዋል።

የአውሮፓ ምክር ቤት ዋና ፀሃፊ አላይን ቤርሴት ጥቅምት 8 የሚከበረውን ዓመታዊውን የአውሮፓ የፀረ-ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ቀንን አስመልክተው እንደተናገሩት “አሁን ባለው ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶች ምክንያት ችግሩ እየተባባሰ መምጣቱ ስለማይቀር፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ለመከላከል አፋጣኝ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ግልጽ ነው” ብለዋል።

በአውሮፓ የሰዎች ማዘዋወር ድርጊትን ለመከላከል የሚወሰደው እርምጃ አስመልክቶ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን የሚቃወመው የአውሮፓ ኤክስፐርቶች ቡድን (GRETA) ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት በአውሮፓ ውስጥ በተለይም በጦርነት ውስጥ ከሚገኙ ክልሎች ለሚመጡ ስደተኞች በቂ ጥበቃ ባለመደረጉ ከፍተኛ ውድቀት ታይቷል። እነዚህ ግለሰቦች ብዙውን ጊዜ ችላ ይባላሉ አልፎ ተርፎም ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ይቀጣሉም ተብሏል።

በያዝነው ዓመት በወጣው የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሪፖርት ላይ በአውሮፓ ብቻ 32,996 ሰዎች የዚህ ችግር ሰለባ መሆናቸውን እና 1,667 የቅጣት ውሳኔዎች መተላለፋቸውን ዘግቧል። ለዚህ አሳሳቢ ስጋት ምላሽ ለመስጠት የአውሮፓ ኤክስፐርቶች ቡድን በተገለሉ ማህበረሰቦች ውስጥ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት አዲስ የክትትል ዑደት መጀመሩን ያስታወቀ ሲሆን፥ ስደተኞችን የሚመለከቱ ፖሊሲዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እንዲቻል ከህግ ማዕቀፎች ጋር በተሻለ መልኩ ሊጣጣሙ እንደሚገባ ተጠቁሟል።

ሃምሌ 6 ቀን 2016 ዓ.ም. የአውሮፓ ፓርላማ እና የአውሮፓ ምክር ቤት ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የተሻሻሉ ህጎችን እና ደንቦችን በማካተት የተሻሻለውን የአውሮፓ ህብረት የፀረ-ህገወጥ የሰዎች ዝውውር መመሪያን ማፅደቁ ይታወሳል።

ለአደጋ የተጋለጡ ህፃናት
በተለይ ህጻናት ለህገወጥ የሰዎች ዝውውር ተግባር በጣም የተጋለጡ እንደሆኑ የተዘገበ ሲሆን፥ ለዚህ ምላሽ ከዩክሬን የመጡ ህጻናት ወሲባዊ ጥቃት እና የጉልበት ብዝበዛን ጨምሮ የሚያጋጥሟቸውን ህገወጥ የሰዎች ዝውውር አደጋዎች በተመለከተ በዩክሬን ህፃናት ጉዳይ የአውሮፓ አማካሪ ቡድን ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ከአውሮፓ ምክር ቤት ሴክሬታሪያት ጋር በመተባበር በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰውን ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተግባርን ለመከላከል መወሰድ በሚገባው እርምጃ ላይ ያተኮረ ልዩ ዘገባ አዘጋጅቷል።

የዚህ ሪፖርት ፍሬ ነገር ምንም እንኳን ፈታኝ እውነታዎች ቢኖሩም የዩክሬን ህፃናትን ከህገወጥ ዝውውር ለመጠበቅ ቁርጠኝነቱ ሊኖር እንደሚገባ ማሳየት ሲሆን፥ የመጀመሪያ ደረጃ አደጋዎችን እና እነሱን ለመቀነስ ሊወሰዱ የሚችሉ እርምጃዎችን በማጉላት፥ እነዚህን ህጻናት ለመከላከል በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደር አካላት ተባብረው እንዲሰሩ ጥሪውን አቅርቧል።

ሪፖርቱ አዳዲስ ተግዳሮቶች እየታዩ በሄዱ ቁጥር ችግሩን በብቃት ለመቅረፍ ስትራቴጂዎችን ማሻሻል እና የህግ አስከባሪ ኤጀንሲዎችን ሁለገብ ዘርፎች ትብብር ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ያበረታታል።

“በጣም የተጋለጡትን ለመጠበቅ እና ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል አንድ መሆን አለብን” ያሉት ቤርሴት፥ የሁሉንም ሰው በተለይም በጣም ተጋላጭ የሆኑትን ክብር እና መብት የሚያስከብር ማህበረሰብ መገንባት አለብን ብለዋል።

በዚህ ዓመት ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን የሚቃወመው የአውሮፓ ኤክስፐርቶች ቡድን 52ኛ ስብሰባውን ከህዳር 9 እስከ 13 ድረስ የሚያካሂድ ሲሆን፥ በዚህ ጊዜ ተከታታይ የሆኑ ጠቃሚ ውሳኔዎች ይወሰዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
 

21 October 2024, 16:16