ሞዛምቢካውያን ወደ ታሪካዊ ምርጫ በማምራት ላይ እንደሚገኙ ተነገረ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ምርጫው ሞዛምቢክ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1975 ከፖርቹጋል የቅኝ አገዛዝት ነፃ ከወጣች በኋላ አገሪቱን እየመራ ያለው የፍሬሊሞ ፓርቲ የስልጣን ዘመን ማብቂያ ሊሆን ይችላል ተብሏል። ከነጻነት በኋላ የተወለዱት እና ለመጀመሪያ ጊዜ የፍሬሊሞ ፕሬዚዳንታዊ እጩ ሆነው የቀረቡት የ47 ዓመቱ ዳንኤል ቻፖ የትውልድ ለውጥ እንደሚያሳዩ ተገልጿል። ቻፖ በፍሬሊሞ የ50 ዓመት የስልጣን ዘመን የተበሳጩ መራጮችን በማበረታታት የፓርቲውን ቅርስ ካበላሹ የሙስና ቅሌቶች ራሱን አግልሎ ቆይቷል። የቻፓ የምርጫ ቅስቀሳዎች የበርካታ ቀናተኛ ሰዎችን ቀልብ የሳበ ሲሆን፥ ብዙዎችም እርሱን ለአገሪቱ አዲስ ጅምር አድርገው እንዲመለከቱት አድርጓቸዋል።
ጥርጣሬን ማስወገድ
ይሁን እንጂ ቻፖ እውነተኛ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ሁሉም ሰው እርግጠኛ አይደለም። የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሚርና ቺትሱንጎ በፍሬሊሞ ውስጥ ያለውን ሥር የሰደደ ሙስናን ቻፓ መቋቋም ይችል እንደሆነ ትጠይቃለች። “የተዋረደች አገር ብትኖረን ምክንያቱ ሙስና ነው” ስትል ገልጻ፥ ቻፖ በሞዛምቢክ የፖለቲካ ሕይወት ውስጥ ለብዙ አሥርተ ዓመታት ማዕከል ሆኖ በቆየው ፓርቲ ውስጥ ማሻሻያ ማድረግ በመቻል ላይ ያላትን ጥርጣሬ ገልጻለች። እነዚህን ስጋቶች የሚያባብሱት የምርጫ ማጭበርበር ስጋቶች መኖራቸው እና በጥናት የተረጋገጠ ወደ 900,000 የሚጠጉ የ “ስዉር መራጮች” ምዝገባ በምርጫው ተዓማኒነት ላይ ጥላ ፈጥሯል ተብሏል።
ድህነትን መግታት
ከቻፖ በተጨማሪ ሌሎች ሦስት እጩዎች ለፕሬዚዳንትነት እየጣሩ እንደሆነ ሲነገር፥ እነርሱም እንደ ገለልተኛ እጩነት የቀረበው ቬናንሲዮ ሞንድላን፣ የዋና ተቃዋሚው የሬናሞ ፓርቲ እጩ ኦሱፎ ሞማዴ እና የሞዛምቢክ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ መሪ ሉቴሮ ሲማንጎ ናቸው። ሞንድላን “አገራችን ሞዛምቢክን አድን” በሚለው መፈክሩ በተለይ በወጣት መራጮች ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍ ማግኘቱ ሲነገር፥ ሥራ አጥነትን እና ድህነትን ለመቅረፍም ቃል ገብቷል።
የሞዛምቢክ ሕዝብ ድምጽ ለመስጠት ሲወጣ ምርጫው ሀገሪቱ በወሳኝ መስቀለኛ መንገድ ላይ መድረሷን የሚያመላክት እንደሆነ ታውቋል። ቻፖ እራሱን እንደ የለውጥ እና የአዲስ አመራር ፈር ቀዳጅ አድርጎ ባቀረበበት እና ሞንድላን ራሱን የወጣቶች ምኞት አሳኪ አድርጎ ባቀረበበት በዚህ ወቅት ሀገሪቱ ወሳኝ ምርጫ ይጠብቃታል ተብሏል።