ስደተኛ ተማሪዎች የሁለተኛ ድግሪ ትምህርታቸውን ለመቀጠል ጣሊያን መግባታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የስደተኞች የዩኒቨርሲቲ ኮሪደር (UNICORE) የሚባለው የስደተኛ ምሁራን ህብረት የሁለት ዓመታት የትምህርት ወጪያቸውን ሙሉ በሙሉ በገንዘብ የደገፋቸው የተለያዩ ስደተኞች የማስተርስ ፕሮግራሞቻቸውን በ37 የጣሊያን ዩኒቨርሲቲዎች ለመጀመር የመጀመሪያው ቡድን ሮም ገብተዋል።
ይህ ህብረት በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት የስኮላርሺፕ ፕሮግራም ሲሆን፥ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ በመባልም ይታወቃል። እ.አ.አ. ከ2019 ዓ.ም. ጀምሮ ዩኒኮር በተወሰኑ የአፍሪካ ሀገራት የስደተኛ ደረጃ የተሰጣቸውን ተማሪዎች ተቀብሎ ሲያስተናግድ እንደነበረም ይታወቃል። ዘንድሮ እድሉን ያገኙት የስደተኞች ቡድን ከደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኮንጎ እና ኢትዮጵያ የተውጣጡ 65 ተጠቃሚዎችን ያካተተ ሲሆን፥ እነዚህም ሃገራት በአሁኑ ወቅት የእርስ በርስ ጦርነት እና ለረዥም ግጭት ውስጥ የሚገኙ ሀገራት ናቸው።
ከዋና የፕሮግራሙ አስተባባሪዎች ውስጥ አንዱ የሆነው ካሪታስ ኢጣሊያና ባወጣው መግለጫ፣ ምን ያህሉ ወጣት ተማሪዎች በሀገረ ስብከቱ ግብረ ሰናይ ሠራተኞች እንደሚታገዙ በዝርዝር አስቀምጧል።
ካሪታስ ማለት ዋና ቢሮውን ሮም ላይ ያደረገ የካቶሊክ የእርዳታ ድርጅቶች ስብስብ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፥ ዩኒኮር ድጋፍ ያደረገላቸው ስደተኛ ተማሪዎቹ ወደ ጣሊያን ዩኒቨርሲዎች ገብተው እንዲማሩ ከሚያስተባብሩት የሃይማኖት ድርጅቶች ውስጥ አንዱ ብቻ ነው። የዋልዲሺያን ማህበር እና የጄሱሳዊያ የስደተኞች አገልግሎት የዘንድሮውን ተነሳሽነት ለማስተባበር እና ለማቀድ ከጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ‘ካምፓስ ኤክስ’ ከሚባለው ተቋም ጋር በመሆን ለአንዳንድ የትምህርት ዕድሉ ተጠቃሚዎች መኖሪያ ቤቶችን እንዳዘጋጀ ተገልጿል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ የጣሊያን እና የቅድስት መንበር ተወካይ ቺያራ ካርዶሌቲ በ ‘ዩኒኮር 2024’ ለተሳተፉ የመንግስት፣ የቤተ ክህነት እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ምስጋና አቅርበዋል።
ካሪታስ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ “ለስድስት ተከታታይ ዓመታት እነዚህን ውጤቶች እንዲመዘገቡ ያስቻሉት ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና አጋሮች የማያቋርጥ ቁርጠኝነት ስለሆነ በእነሱ ኩራት ይሰማናል” ብሏል።
የከፍተኛ የትምህርት ዕድል ፕሮግራም ተጠቃሚዎቹ በመላው አገሪቱ ውስጥ በሚገኙ የጣሊያን ዩኒቨርሲቲዎች ለሁለት ዓመታት ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ የተገለጸ ሲሆን፥ ተማሪዎቹ የተለያዩ የሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብሮች ማለትም የቢዝነስ ኢኮኖሚክስ፣ የበረራ ምህንድስና እና የዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ውስጥ መምረጥ ይችላሉ ተብሏል።
እንደ ጽንሰ-ሃሳብ፣ የዩኒኮር ፕሮጄክት በአውሮፓ ህብረት የጥገኝነት፣ ፍልሰት እና ውህደት ፈንድ ከሚደገፈው ትልቁ የሰብአዊ ኮሪደሮች ፕሮጀክት የመነጩ ናቸው። እነዚህ ኮሪደሮች ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ህዝቦችን ወደ ኢጣሊያ ለማጓጓዝ ቅድሚያ እንደሚሰጥ እና ይህም ተግባራዊ እንዲሆን በርካታ በሃይማኖት ላይ የተመሰረቱ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተገልጿል።
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከግጭት እና ከድህነት የሚሸሹትን ስደተኞች በአስተማማኝ እና በህጋዊ መንገድ ለማጓጓዝ የሰብአዊነት ኮሪደሮችን እንደ አብነት ደጋግመው ያነሳሉ።
የከፍተኛ ትምህርት ተደራሽነት ለሃገራዊ እድገት እና ለስደተኞች የወደፊት እድሎችን ለመፍጠር ወሳኝ ነው። እንደ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ መረጃ ከሆነ ከዓለም አቀፍ ስደተኞች መካከል ሰባት በመቶው ብቻ በዩኒቨርሲቲዎች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ስደተኛ ካልሆኑት ደግሞ 42 በመቶ አካባቢ እንደሆኑ ይገልፃል።