በሱዳን የተከሰተው እና ዓለም ችላ ያለው ሰብዓዊ ውድመት
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የአፍሪካ ቀውሶች በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ብዙ ጊዜ ችላ ይባላሉ። ይህ የትኩረት እጦት በሱዳን ጉዳይ ላይም በግልጽ የሚታይ ሲሆን፥ በሱዳን ጦር እና መደበኛ ባልሆነው ፈጣን ድጋፍ ሰጪ ሃይሎች (RSF) መካከል የተቀሰቀሰው ጭካኔ የተሞላበት ግጭት ወደ አስከፊ ጥፋት ተሸጋግሯል።
የሚገርሙ ምስሎች፣ አስፈሪ ውንጀላዎች
ይህ ዓለም አቀፍ ሽፋን እጦት ያስከተለውን የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዝምታ ጦርነቱ ከተጀመረ 18 ወራትን ቢያስቆጥርም አሁንም ድረስ በተጠናከረ ሁኔታ እንዲቀጥል አድርጎታል። እንደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዘገባ መሰረት በዚህ ጦርነት 9,000 የሚደርሱ ሰዎች ተገድለዋል፣ ከ5.6 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ተፈናቅለዋል፣ 25 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ከፍተኛ የሆነ ሰብአዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብሏል።
በሱዳን ጦር ላይ ከሚቀርቡት ክሶች እና ውንጀላዎች መካከል ብዙ ህዝብ በሚበዛባቸው ሲቪል አካባቢዎች ላይ የአየር ድብደባ ከማድረሱ በተጨማሪ የአስገድዶ መድፈር እና ጾታዊ ጥቃት በስፋት መዘገባችን ይታወሳል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ በያዛቸው ሰፊ ግዛቶች ላይ የዘር ማጥፋት፣ ጅምላ ጭፍጨፋ እና አረብ ባልሆኑ የማሳሊት ማህበረሰብ ላይ ጾታዊ ጥቃት በመፈጸም የሚከሰሱ ሲሆን፥ ምንም እንኳን የስቃዩ መጠን እና የክሱ ክብደት ከፍተኛ ቢሆንም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በጉዳዩ ላይ ብዙ ፍላጎት ያለው አይመስልም።
ግጭቱ
ወደ ሲቪል አገዛዝ እና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሊደረግ የነበረው ሰላማዊ ሽግግር ታስቦ በነበረበት ወቅት በጦር ኃይሉ እና በፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ መካከል በተካሄደው አረመኔያዊ የስልጣን ሽኩቻ ምክንያት በሱዳን የተቀሰቀሰው ጦርነት በዓለም ላይ ታይቶ ወደማይታወቅ ትልቁ የመፈናቀል ቀውስ ተሸጋግሯል።
በጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር ሃይሎች እና በቀድሞ ምክትላቸው በጄኔራል መሀመድ ሃምዳን ዳግሎ (ሄሜቲ) በሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ መካከል የተፈጠረው ግጭት የተቀሰቀሰው ሚያዝያ 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ነበር። ከዚህ ቀደም ሁለቱ መሪዎች በ 2011 ዓ.ም. ሃገሪቱን ለረዥም ጊዜ ሲመሩ የነበሩትን አምባገነኑን መሪ ፕረዚዳንት ኦማር አልበሽርን ከስልጣን ለማውረድ ተባብረው የነበረ ሲሆን፥ ፕረዚዳንቱ በሀገሪቱ የዳርፉር ክልል በሰብአዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች፣ በጦር ወንጀሎች እና የዘር ማጥፋት ወንጀል በዓለም አቀፉ የወንጀሎኞች ፍርድ ቤት ሲፈለጉ እንደነበር እና የእሳቸው ከስልጣን መባረር ለዲሞክራሲያዊ ሽግግር መንገድ ይጠርጋል ተብሎ ታስቦ እንደነበር አይዘነጋም።
ህፃናት
በአሁኑ ሰዓት በሃገሪቷ ያለው የሰብአዊነት ሁኔታ በእጅጉ እንደወደቀ የሚታወቅ ሲሆን፥ በሃገሪቱ የሚገኙ አብዛኞቹ ሱቆች በመዘረፋቸው ወይም በመውደማቸው ምክንያት በመሠረታዊ ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ እጥረት እንዳስከተለ መረጃዎች ያሳያሉ። በግንቦት ወር አጋማሽ እስከ መስከረም ወር አጋማሽ መካከል በነጭ አባይ ግዛት ብቻ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ከ1,200 በላይ ህጻናት በኩፍኝ በሽታ ወረርሽኝ እና በከፍተኛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት እንደሞቱ፣ እንዲሁም ከ3 ሚሊየን በላይ ህጻናት በመፈናቀላቸው ምክንያት ሱዳን በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ቁጥር ያላቸው ህጻናት የተፈናቀሉባት ሀገር ያደርጋታል ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪም 19 ሚሊዮን የሚሆኑ ህፃናት በትምህርት ገበታ ላይ እንደሌሉ መረጃዎች ያመላክታሉ። እነዚህ አስደንጋጭ አኃዞች ቢኖሩም፣ የጤና አጠባበቅ እና የመንግሥት አገልግሎቶች መውደቅ፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች እጥረት፣ እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን ትኩረት እጦት የአደጋውን አጠቃላይ ይዘት ስለሚሸፍነው በጦርነቱ የሞቱትን ትክክለኛ የሰዎች ሞት መጠን በእርግጠኝነት ማወቅ አልተቻለም ተብሏል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የሰላም ጥሪ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በሱዳን እየተካሄደ ላለው ግጭት ጥልቅ የሆነ ጭንቀታቸውን በተለያዩ ጊዜያት ገልጸው የነበረ ሲሆን፥ ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆም እና ተፋላሚ ወገኖች ሰላማዊ ውይይት እንዲያደርጉ በመጠየቅ
‘ጦርነት በሚፈጠርበት ቦታ ሁሉ ሰዎች ይዳከማሉ፥ በጦርነት ይሰላቻሉ’ በማለት በአጽንዖት በመናገር፣ የበለጠ ውድመት እና ስቃይ እንዳይከሰት የፖለቲካ መሪዎች ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጡ ሳይታክቱ ሲማፀኑ እንደነበር ይታወቃል።