ፈልግ

ጥቅምት 2 በዛፖሪዢያ ውስጥ የሩሲያ የአየር ጥቃት ከደረሰ በኋላ ጥቅምት 2 በዛፖሪዢያ ውስጥ የሩሲያ የአየር ጥቃት ከደረሰ በኋላ 

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ጦርነቱ እንደሚያበቃ ያላቸውን ተስፋ ገለፁ

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በቫቲካን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን ሲደርሱ በሰጡት አስተያየት ከሩሲያ ጋር ያለው ጦርነት በሚቀጥለው ዓመት እንደሚያበቃ ያላቸውን ተስፋ የገለጹ ሲሆን፥ ሆኖም ቅዳሜ ዕለት አገርሽቶ በተከሰተው አዲስ ግጭት ምክንያት የጦርነቱ ማብቂያ አሁንም ሩቅ ይመስላል ተብሏል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የዩክሬን ጦር በክሬሚያ ባሕረ ገብ መሬት ላይ ባለው ትልቁ የነዳጅ ተርሚናል ላይ ጥቃት ማድረሱን ያስታወቀ ሲሆን፥ ጥቃቱ በሩስያ ቁጥጥር ስር ባሉ የኃይል ማመንጫዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ነው ተብሏል። የኪዬቭ ባለስልጣናት እንደተናገሩት የሀገሪቱ የሚሳኤል ሃይሎች በፌዮ-ዶሲያ ከተማ በሚገኘው ትልቁ የነዳጅ ማቀነባበሪያ ተቋምን በአንድ ጀንበር መምታታቸዉን ገልጸዋል፡፡

ዩክሬን ባስወነጨፈችው ሁለት ሚሳኤሎች ምክንያት በሞስኮ ቁጥጥር ስር በምትገኘው ክሬሚያ ውስጥ ያለው የነዳጅ ማከማቻ ተርሚናል ለአራት ቀናት በላይ በእሳት ሲጋይ በማየታቸው የአይን እማኞች መደናገጥቸውን የገለጹ ሲሆን፥ በፍንዳታው ምክንያት ወደ 60 ሜትር ከፍታ ያለው የእሳት ነበልባል ማስነሳቱንም የአይን እማኞቹ ጨምረው ተናግረዋል።

የሩሲያ ባለስልጣናት ጥቃቱ ስለመፈጸሙ ባያረጋግጡም በተቋሙ ላይ የእሳት ቃጠሎ መድረሱን ግን አምነዋል። በፍንዳታው ምንም አይነት ጉዳት አልደረሰም የተባለ ሲሆን፥ በቃጠሎው ሳቢያ 300 ሰዎች ከፌዮ-ዶሲያ ከተማ እንዲወጡ መደረጉን እና አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል ሲል በሩሲያ መንግስት ስር የሚተዳደረው ታስ የዜና አገልግሎት ዘግቧል።

ለሩሲያ ወታደራዊ ሃይሎች እጅግ አስፈላጊ የሆነውን ነዳጅ ሲያቀርብ የነበረው እና በፌዮዶሲያ ከተማ የሚገኘው የነዳጅ ማከማቻ ተርሚናል እንዲመታ መጀመሪያ ላይ ታቅዶ የነበረው የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ማክሰኞ ዕለት ካከበሩት 72ኛ የልደት በዓል ጋር እንዲገጣጠም ነበር ተብሏል። የነዳጅ ማከማቻው ከተመታበት ጊዜ ጀምሮ አሁንም ድረስ እሳቱ እየነደደ ሲሆን፥ ፍንዳታዎቹም እየተባባሱ መምጣታቸውን ዘገባዎች ያሳያሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በሞስኮ የሚገኘው የመከላከያ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በኪየቭ ከተወነጨፉ 21 ሰው አልባ አውሮፕላኖች 12ቱን ማክሸፉን ይፋ ያደረገ ሲሆን፥ የዩክሬን ኃይሎች ጥቃቱን አስመልክቶ ባወጡት መግለጫ ከተርሚናሉ የሚላኩ የነዳጅ ምርቶች “የሩሲያን ወራሪ ጦር ፍላጎት ለማሟላት እየዋሉ ነው” በማለት ይከሳሉ።

ኪየቭ በሩሲያ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ የወሰደችው ጥቃት ሩሲያ ለምትፈጽመወቁ ጥቃቶች ፍትሃዊ የበቀል እርምጃ እንደሆነም ተናግራለች።

በሌላ ዜና ቅዳሜ ዕለት የዩክሬን ሃይሎች በምስራቅ ዩክሬን በምትገኘው እና በሩሲያ ቁጥጥር ስር ባለችው ሉሃ-ንስክ ክልል ውስጥ ያሉ የነዳጅ ማከማቻ መጋዘኖችን በመምታታቸው ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ ማስከተሉን ተነግሯል። ሆኖም የሩሲያ ጦር ሰሞኑን በወሰደው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ በምስራቅ ዩክሬን ያሉትን ሁለቱን የጦርነት ቀጠና የሆኑ መንደሮች መያዙን ያሳወቀ ሲሆን፥ ይህም ሞስኮ በጦርነት ከያዘቻቸው የዩክሬን ግዛቶች የቅርብ ጊዜዎቹ እንደሆኑ ተገልጿል።

እ.አ.አ በ 2014 ዓ.ም. ሩሲያ በሕገ-ወጥ መንገድ ክሪሚያን ከዩክሬን በመቀማት የራሷ ግዛት አድርጋ መቀላቀሏን ዩክሬን ትከሳለች።

የሁለቱን ሃገራት ጦርነት ዜና ለመሸፈን ለሚዲያ ሰራተኞች የበለጠ አደገኛ እየሆነ መምጣቱ የተነገረ ሲሆን፥ ዩክሬን የ 27 ዓመቷ ዩክሬናዊ ጋዜጠኛ ቪክቶሪያ ሮሽ-ቺና ሞት ላይ ምርመራ እንደሚካሄድ አስታውቃለች።

'ተይዛ ታስራለች'
ጋዜጠኛዋ በ 2015 ዓ.ም. በሩሲያ ስለተያዙት የዩክሬን አካባቢዎች ስትዘግብ በሩሲያ ሃይሎች ተይዛ መታሰሯ የተነገረ ሲሆን፥ ባለሥልጣናቱ ወጣቷ መስከረም 9 ቀን 2017 ዓ.ም. የእስረኛ ልውውጥ በተደረገበት ቀን ላይ እንደሞተች ይናገራሉ።

ምንም እንኳን እነዚህ ሁሉ መሰናክሎች ቢኖሩም የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ቀጣይነት ያለው ወታደራዊ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ለመጠየቅ ወደ ጀርመን፣ በርሊን ተጉዘው ባደረጉት ንግግር በሚቀጥለው ዓመት ከሩሲያ ጋር ያለው ጦርነት “እንደሚቆም” ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልስ በበኩላቸው በዚህ ዓመት ጀርመን እና የአውሮፓ ህብረት አጋሮቿ ተጨማሪ የጦር መሳሪያዎችን እና 4 ቢሊዮን ዩሮ ወይም 4.4 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሰብአዊ እርዳታ ወደ ዩክሬን እንደሚልኩ ቃል ገብተዋል።
 

14 October 2024, 13:24