ፈልግ

አንድ ሱዳናዊ ስደተኛ በማጋን አቅራቢያ በሚገኝ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ውሃ ተሸክሞ አንድ ሱዳናዊ ስደተኛ በማጋን አቅራቢያ በሚገኝ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ውሃ ተሸክሞ   (AFP or licensors)

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኢትዮጵያ ለአማራ ክልል ሲሰጥ የነበረውን የምግብ እርዳታ ለማቆም ማሰቡ ተነገረ

በኢትዮጵያ ግጭት እየተካሄደ ባለበት በአማራ ክልል ውስጥ አምስት የረድኤት ሰራተኞች በታጣቂዎች እንደተገደሉ እና አስራ አንዱ ደግሞ ታፍነው መወሰዳቸው ከተነገረ በኋላ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብ እርዳታን ጨምሮ በክልሉ ውስጥ ሲያደርግ የነበረውን ሰብአዊ ድጋፍ ለማቆም ሃሳብ እንዳለው እየተነገረ ይገኛል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የተባበሩት መንግሥታት በአማራ ክልል የሚያደርገውን የሰብዓዊ ድጋፍ ለማቆም ሃሳብ እንዳለው የገለጸው በክልሉ ውስጥ እየተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኞች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ የሚደርሰውን የምግብ እርዳታ ለማቆም እያሰበ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ ሆኖም ግን ዕቅዱ የተለያዩ ተቃውሞዎች እንደገጠሙት ተነግሯል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ነሐሴ ወር ላይ ያዘጋጀው ይህ ረቂቅ ምክረ ሃሳብ ባለፈው ዓመት ከጥር ወር ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራት ብቻ 5 የሰብአዊ እርዳታ ድርጅት ሰራተኞች እንደተገደሉ፣ በአስሩ ላይ አካላዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው፣ እንዲሁም 11ዱ ደግሞ ባልታወቁ ወንጀለኛ ቡድኖች መታገታቸው በሰነዱ ላይ ተመላክቷል።

ረቂቅ ምክረ ሃሳቡ በተባበሩት መንግስታት ሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ የተዘጋጀ ሲሆን፥ ሰነዱ በኢትዮጵያ የሰብአዊ ድጋፍ ቢሮ፣ ለጋሾች፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ለመንግስታቱ ድርጅት ቢሮዎች እንደተጋራም ተገልጿል።

የሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያዘጋጀው ባለሦስት ገጽ ውስጣዊ ሰነድ እንደሚያመላክተው ድርጅቱ በክልሉ ሲያደርግ የነበረውን የሰብአዊ እርዳታ ስራዎችን በጊዜያዊነት ለማቆም በጥሞና እያሰላሰለ መሆኑን ያሰፈረ ሲሆን፥ ይሁን እንጂ የተባበሩት መንግስታት የሚሰጠውን ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያቋርጥ ከሆነ ህይወቱ በምግብ እርዳታ ላይ የተመረኮዘው ከ 2.3 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው የአማራ ህዝብ ላይ አስከፊ ተጽእኖ ይኖረዋል በሚል በርካታ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ለጋሾች ድርጊቱን ተቃውመዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።

ክልሉ ከ36 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የሚገኝበት ሲሆን በጎረቤት ሱዳን እየተካሄደ ያለውን ጦርነትን ሸሽተው በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች የመጀመሪያ ማረፊያቸውን አማራ ክልል ላይ እንዳደረጉ ይታወቃል።

በኢትዮጵያ ጦር እና በአማራ ፋኖ ታጣቂዎች መካከል ሃምሌ 2015 ዓ.ም. የተቀሰቀሰው ጦርነት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድሎ በሺዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ከቤት ንብረታቸው እንደተፈናቀሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ግምት ያሳያል።

ከዚህ ግጭት በፊት በቅርቡ ለሁለት ዓመታት በዘለቀው እና በትግራይ ክልል ላይ ሲካሄድ በነበረው የእርስ በርስ ግጭት ላይ ኢትዮጵያ ረሃብን እንደ ጦር መሣሪያ ትጠቀማለች የሚል ክስ ቀርቦባት እንደነበረ ይታወሳል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ የሆኑት ራሚዝ አላክ-ባሮቭ ለሮይተርስ እንደተነገሩት ከሆነ በሠራተኞች ላይ የሚደርሱ ግድያዎች እና እገታዎች “የሰብዓዊ ድጋፍ ሠራተኞች ሥራቸውን እንዳያከናውኑ ስለሚያደርግ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ድጋፍ ወደሚያስፈልገው ማኅበረሰብ የምንደርስበት መንገድ በአግባቡ እስኪመቻች ድረስ ድጋፉ ይቋረጣል” ብለዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰነድ መሰረት ድርጅቱ በአማራ ክልል የሚያደርገውን የሰብአዊ እርዳታ ስራ እንደገና ለመጀመር የኢትዮጵያ መንግስት ተጨባጭ የሆኑ ቃል ኪዳኖችን እና ተጨማሪ የደህንነት እርምጃዎች ላይ መስማማት ይኖርበታል ተብሏል።

በክልሉ ሲደረግ የነበረውን የእርዳታ ሥራ ለማስቀጠል የሰብዓዊ ድጋፍ የሚሰጡ ሠራተኞች በአማራ ክልል ደኅንነታቸው ተጠብቆ መንቀሳቀስ መቻላቸውን ዋስትና መስጠት ከተቻለ፣ እንዲሁም በክልሉ በሠራተኞች ላይ የተፈጸሙ እገታዎች እና ግድያዎች በገለልተኛ አካላት የሚመረመሩ ከሆነ ብቻ እንደሆነም ተገልጿል።
 

11 October 2024, 12:38