ፈልግ

በጦርነቱ ምክንያት የተቃጠሉ መኪኖች በአቪቪም መንገድ በጦርነቱ ምክንያት የተቃጠሉ መኪኖች በአቪቪም መንገድ  

እስራኤል እና ሂዝቦላ በሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተነገረ

ለአንድ ዓመታት ያክል በሊባኖስ ሲካሄድ የነበረው የእስራኤል እና የሂዝቦላ ጦርነት በዩናይትድ ስቴትስ እና የረዥም ጊዜ የሊባኖስ አጋር በሆነችው ፈረንሳይ በተደረገ የተኩስ አቁም ስምምነት ጥረት ፍሬ አፍርቶ ወደ ተግባር የተሸጋገረ ሲሆን፥ በዚህም መሰረት በአደራዳሪ ወገኖች ክትትል የሚደረግበት የሁለቱም ተዋጊ አካላት ወታደሮች ስፍራውን ለቀው ለመውጣት እንደተስማሙ ተዘግቧል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በእስራኤል እና በኢራን በሚደገፈው የሊባኖስ ሚሊሻ መካከል የሚደረገውን ጦርነት ለማስቆም የ60 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ በአደራዳሪ ወገኖች ሲካሄድ የነበረው ጥረት ተሳክቶ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፥ በስምምነቱ መሰረት በእስራኤል እና በሄዝቦላህ በሚለቀቁ አካባቢዎች የሊባኖስ መንግስት ጦር እንደሚሰማራ ተነግሯል።

ሔዝቦላህ በጋዛ የሚገኘው ሐማስን በመደገፍ በእስራኤል ላይ ሮኬቶችን በመተኮሱ ፍጥጫው የጀመረው ባለፈው ዓመት መስከረም 27 እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፥ እስራኤል ከአየር ጥቃት በተጨማሪ ሊባኖስ ላይ ወረራ በመፈጸም የተቀናጀ ጥቃቷን አጠናክራ መቆየቷ ይታወቃል።

በዚህም ምክንያት በእስራኤል እና በሂዝቦላ መካከል ከአንድ ዓመት በላይ ሲደረግ የነበረው ድንበር ተሻጋሪ የትንኮሳ ጦርነት እና ወራትን ባስቆጠረው የገሃድ ጦርነት ከ 3,800 በላይ ሰዎች ሲሞቱ ወደ 900,000 የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው እንደተፈናቀሉ የተነገረ ሲሆን፥ ይሄን ተከትሎ በአደራዳሪ ሃገራት በኩል የተደረገው የተኩስ አቁም ስምምነት በሊባኖስ ተግባራዊ መሆን የጀመረው ከባለፈው ረቡዕ ህዳር 18 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሆነ ተገልጿል።

በአሜሪካ አደራዳሪነት የተደረሰው ይህ የተኩስ አቁም ስምምነት እስራኤል በሚቀጥሉት 60 ቀናት ከወረረቻቸው የሊባኖስ ደቡባዊ ክፍል ቀስ በቀስ ወታደሮቿን የምታስወጣ ሲሆን፥ በምትኩም የሊባኖስ መንግሥት ወታደሮች ስፍራውን እንደሚቆጣጠር እስራኤል እንደተስማማች፥ ይሄንንም አስመልክቶ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ “ሂዝቦላህ ስምምነቱን ከጣሰ እና ራሱን እንደገና ለማደራጀት ከሞከረ” አገራቸው ወታደራዊ ምላሽ የመስጠት መብቷ የተጠበቀ እንደሆነ ካሳሰቡ በኋላ፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስራኤል በሰሜናዊ ጎረቤቷ ከሚንቀሳቀሰው ሄዝቦላ ጋር ስምምነት መፍጠሯ የእስራኤል ጦር ትኩረቱን በኢራን ላይ ብቻ እንዲያደርግ እንደሚያስችለው ገልጸው ስምምነቱን “በመርህ ደረጃ” መቀበላቸውን ገልጸዋል።

የእርቁን ስምምነት የሚከታተለው ማን ይሆናል የሚለው ትልቁ አንገብጋቢ ጥያቄ መፍትሔ ያገኘ ሲሆን፥ በዚህም መሰረት በአሜሪካ የሚመራ እና ፈረንሳይን ጨምሮ አምስት አገራትን ያካተተ ኮሚቴ በመቋቋሙ የተኩስ አቁሙን በተመለከተ ምንም አይነት ከባድ እንቅፋት የለም መባሉ ተነግሯል።

በዚህም አግባብ በሊባኖስ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ጊዜያዊ ሃይል (ዩኒፊል) እና የሊባኖስ ጦር ከነበራቸው ድክመት አንፃር የተኩስ አቁም እንዴት ተግባራዊ ይሆናል የሚለው ስጋት የተቀረፈ ይመስላል።

ስምምነቱ ለስልሳ ቀናት የሚቆይ የሽግግር ደረጃ የሚሰጠው ሲሆን፥ በተመሳሳይ ሁኔታ የሂዝቦላህ ኃይሎች ከሊታኒ ወንዝ በስተሰሜን ካሉ አከባቢዎች ለቀው እንደሚወጡ ብሎም የሊባኖስ ጦር ድንበር ላይ እንደሚሰፍር ተመላክቷል።

ስምምነቱ በሄዝቦላህ እና በእስራኤል መካከል በአውሮፓውያኑ 2006 የተከሰተውን ጦርነት የቋጨው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 1701 በተሰኘው ውሳኔ የተመሠረተውን ድንበር መሠረት ያደረገ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፥ ይህም እስራኤል እና ሊባኖስ ከሚዋሰኑበት ሊታኒ ከተሰኘው ደቡባዊ ሊባኖስ ስፍራ የሄዝቦላህ ተዋጊዎች እንዲርቁ ማድረግን ያካተተ ነው ተብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በደቡባዊ ሊባኖስ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በእስራኤል ጦር እና በሊባኖስ ባለስልጣናት የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተግባራዊ ቢደረግም ህዝቡ ወደ ቤቱ እንዳይመለስ እየደረሳቸው ያለውን ማስጠንቀቂያ በማውግዝ ተቃውሟቸውን እያሰሙ እንደሆነ ተዘግቧል።

ወደዚህ ስምምነት ለመድረስ ከዲፕሎማሲያዊ ጥረቱ ጀርባ የነበሩት አሜሪካ እና ፈረንሳይ የክትትል ኮሚቴ አካል እንደሚሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ይህ እንዲሆን የተደረገበት ዋነኛ ዓላማ በተግባራዊ ሂደቱ ስምምነቶቹ “ሙሉ በሙሉ” መከበራቸውን ለማረጋገጥ እንደሆነ ተገልጿል።

“ይህ ስምምነት በስፍራው ዘላቂ መረጋጋትን ለማምጣት እና በሁለቱም አገራት የተፈናቀሉ ነዋሪዎች በሰላም ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ሁኔታዎችን ይፈጥራል” ሲል የስምምነቱን አፈጻጸም በጋራ ይከታተላሉ የተባሉት አሜሪካ እና ፈረንሳይ ገልጸዋል።

የዮርዳኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እንደተናገሩት በጋዛ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለማስቆም እየተደረገ ያለው ዓለም አቀፍ ጥረት ይሄንን የተኩስ አቁም ስምምነት ተከትሎ ተግባራዊ ሊደረግ የሚገባ ጠቃሚ እርምጃ ነው ብለዋል።

የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ረቡዕ ዕለት በሰጠው መግለጫ በሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት ድርድር የተገኘውን አወንታዊ ውጤት በደስታ በመቀበል ስምምነቱ ዘላቂ እንደሚሆንም ያለውን ተስፋ ገልጿል።
 

29 November 2024, 12:18