ፈልግ

የዘንድሮ የኤድልስታም ሽልማት ተሸላሚው ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሃቅ የዘንድሮ የኤድልስታም ሽልማት ተሸላሚው ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሃቅ   (Edelstam Foundation)

ለረጅም ጊዜያት እስር ላይ የሚገኘው ኤርትራዊ ጋዜጠኛ የሰብአዊ መብት ሽልማት አሸናፊ ሆነ

ፍርድ ቤት ሳይቀርብ ለ23 ዓመታት የታሰረው ኤርትራዊ ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሀቅ የሰብአዊ መብት ተሸላሚ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ በኤርትራ እስር ቤት የሚገኘው እና ያለበት ሁኔታ የማይታወቀው ጋዜጠኛው የንግግር ነጻነት እንዲከበር ባደረገው ትግል ምክንያት ሽልማቱን እንደሚያገኝ ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የስውዲን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ዳዊት ይስሃቅን የታዋቂው የኤድልስታም ፋውንዴሽን ሽልማት አሸናፊ እንደሆነ እና ጋዜጠኛው ፍርድ ቤት ሳይቀርብ ለረጅም ዓመታት ያለበት ሁኔታ ሳይታወቅ በእስር ላይ እንደሚገኝ በሰጠው መግለጫ ገልጿል።

ጋዜጠኛ ዳዊት ወደ ስውዲን የተሰደደው በ 1979ኙ የኤርትራ ጦርነት ወቅት ሲሆን፣ ኤርትራ ነጻ አገርነቷን ካወጀች በኋላ የስውዲን ዜግነት አግኝቶ በ1985 ዓ.ም. ወደ ኤርትራ ተመልሷል።

የኤርትራ እና ስዊድን ጥምር ዜግነት ያለው ጋዜጠኛ ዳዊት፣ ‘ኤድልስታም’ ተብሎ የሚታወቀው ሽልማት የሚበረከተለት “ልዩ ለሆነ ጀግንነቱ” እንደሆነ ተቋሙ አስታውቋል።

ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሃቅ በኤርትራ የመጀመሪያ እና ብቸኛ ነጻ ጋዜጣ የሆነውን ‘ሰቲት’ ከመሰረቱት ውስጥ አንዱ እንደሆነም የሚታወቅ ሲሆን፥ በሰቲት ጋዜጣ ላይ ካቀረባቸው ጽሑፎች መካከል የኤርትራን መንግሥት የሚተቹ እና ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እንዲመጣ እንዲሁም የንግግር ነጻነት እንዲከበር የሚጠይቁ እንደሚገኙበት፥ ብሎም ለእስር የዳረጉትም እነዚህ ጽሁፎች ሳይሆኑ እንዳልቀረ ይገመታል ተብሏል።

‘ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን’ የተባለው የፕሬስ ነፃነት ድርጅት ጋዜጠኛ ዳዊትን እና የሴቲት ጋዜጣ ባልደረቦቹን ‘በዓለም ላይ ለረጅም ጊዜያት ያለምንም ክስ የታሰሩ ጋዜጠኞች’ ብሎ የሰየማቸው ሲሆን፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ክፍል ጋዜጠኞቹ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ያለማቋረጥ ሲጠይቅ እንደነበር ይታወቃል።

ጋዜጠኛ ዳዊት የዛሬ 23 ዓመት በ 1993 ዓ.ም. በሃገሪቷ ላይ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እንዲመጣ የሚጠይቅ ጽሑፍ በጋዜጣው ላይ ከታተመ በኋላ ነበር በኤርትራ መንግሥት በቁጥጥር ሥር የዋለው።

በዚህም ምክንያት ህዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም. የስዊድን የሰብአዊ መብት ተቋም ጋዜጠኛ ዳዊትን ለዲሞክራሲያዊ መርሆዎች ታማኝ ጠበቃ ለሆኑት ግለሰቦች እውቅና የሚሰጠው የኤድል-ስታም ሽልማት አሸናፊ አድርጎ መርጦታል።

የኤርትራ መንግሥት ወደ 20 የሚጠጉ ከፍተኛ ሚኒስትሮችን፣ የፓርላማ አባላትን እና ገለልተኛ ጋዜጠኞችን ሲያስር ዳዊትም ከእነዚህ መካከል አንዱ ነበር።

ባለፉት ዓመታት የኤርትራ መንግሥት ዳዊት የት እንዳለ እና ስለ ጤናውም ሁኔታ መረጃ ያልሰጠ ሲሆን፥ ከዳዊት ጋር አብረው የታሰሩ ሰዎች ሞተዋል ተብሎ ይታመናል።

የፋውንዴሽኑ ፕሬዝዳንት የሆኑት ካሮላይን ኤድልስታም ከቫቲካን ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ዓለም አቀፉ ሽልማት በዓመት ሁለቴ እንደሚሰጥ የገለጹ ሲሆን፥ በዚህ ዓመትም ለጋዜጠኛ ዳዊት ይስሃቅ ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ላደረገው የላቀ አስተዋጽዖ እና ወደር ለሌለው ጀግንነቱ ሽልማቱን እንደሚሰጠው አስታውቀዋል።

በመስራቹ ስም የሚጠራው ኤድልስታም ፋውንዴሽን የዘንድሮውን ሽልማት የሚሰጠው እ.አ.አ. በ1970ዎቹ ከመፈንቅለ መንግስት ጋር በተያያዘ ከሃገራቸው ለተሰደዱት ላቲን አሜሪካውያን የፖለቲካ ጥገኝነት በሰጠው የስዊድን ዲፕሎማት ሃራልድ ኤድልስታም ስም እንደሆነም ተገልጿል።

ከ 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የኤርትራ መንግስት ስለ ጋዜጠኛ ዳዊት ምንም ዓይነት መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ስላልሆነ እና ዬት እንዳለ ስለማይታወቅ፥ በዚህም ምክንያት ጋዜጠኛው ሞቷል ተብሎ ስለሚገመት፥ ሽልማቱን አስመልክቶ በተሰጠው መግለጫ የፋውንዴሽኑ ዳኞች የጋዜጠኛ ዳዊትን ጉዳይ በተመለከተ ግልጽ የሆነ መረጃ እንዲሰጥ የጠየቁ ሲሆን፥ ዳኞቹ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኤርትራ ባለስልጣናትን ስልታዊ በሆነ መንገድ ጋዜጠኞችን በማሰቃየት እና የፖለቲካ እስረኞችን በመሰወር ወንጀል ተጠያቂ እንዲያደርግ አሳስቧል።

የጋዜጠኛ ዳዊት ይስሐቅ ሴት ልጅ የሆነችው ቤተልሔም ዳዊት ሽልማቱን በሚቀጥለው ሳምንት ህዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም. በስቶክሆልም በሚካሄድ ሥነ ስርዓት አባቷን ወክላ ሽልማቱን እንደምትቀበል ተገልጿል።

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከ 1985 ዓ.ም. ጀምሮ ኤርትራን እየመሯት የሚገኙ ሲሆን፥ ኤርትራ አገር ከሆነች ጀምሮ ምንም አይነት ምርጫ ተካሂዶ አያውቅም።
 

13 November 2024, 12:52