የጦር መሣሪያ አምራቾች በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ ግጭቶች ምክንያት ትርፋቸው እየጨመረ መምጣቱ ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ኢንስቲትዩት ባወጣው አዲስ ሪፖርት መሠረት የዓለም የጦር መሣሪያ ኢንዱስትሪ በ2023 ገቢው ወደ 632 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ማለቱን ገልጿል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ የሚገኘውን የጦርነት ስጋት ተከትሎ ዓለም ወታደራዊ ወጪውን በከፍተኛ መጠን ሲጨምር፥ በያዝነው ዓመት ብቻ 2.4 ትሪሊየን ዶላር ወጪ የተደረገ ሲሆን፣ ከ2023 ጋር ሲነጻጸር በ6.8 በመቶ ጭማሪ ታይቶበታል።
ይህ አሃዝ የሚያመለክተው በዩክሬን እና ጋዛ እየተካሄዱ ያሉ ጦርነቶችን፣ በምስራቅ እስያ እየተባባሰ የመጣውን ውጥረት እና የሃገራት ራስን በጦር መሳሪያ የማደራጀት ፕሮግራሞችን የመሳሰሉ የቀጣይ ግጭቶች ተጽእኖን ያሳያል የተባለ ሲሆን፥ ከዚህም በዘለለ አሁን ባለንበት ዓመት ግጭቶች እና ጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች ተጠናክረው በመቀጠላቸው፥ አሃዙ እያደገ ሊሄድ እንደሚችል መቀመጫውን ስዊድን ያደረገው ኢንስቲትዩት ባለሙያዎች ተናግረዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ
የተለያዩ አሃዞች እንደሚያሳዩት በጎረጎሳዊያኑ 2023 ዩናይትድ ስቴትስ በጦር መሣሪያ ዘርፍ በሃገሪቷ በሚገኙ 41 ኩባንያዎች አማካይነት በስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ኢንስቲትዩት የመጀመሪያዎቹ 100 ዝርዝሮች ውስጥ 317 ቢሊዮን ዶላር ወይም 50 በመቶው የዓለም የጦር መሣሪያ ሽያጭ ትርፍ በማግኘት የበላይነቱን ስፍራ የያዘች ሲሆን፥ ይህም ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ2.5 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ቻይና
በዓለም ሁለተኛዋ ትልቋ የጦር መሳሪያ አምራች የሆነችው ቻይና በተቀዛቀዘ ኢኮኖሚ ውስጥ ሆና በዘጠኝ የጦር መሳሪያ አምራች ድርጅቶቿ አማካይነት ያገኘችው ገቢ 103 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፥ የቻይና ኩባንያዎች በደቡብ ቻይና ባህር፣ ታይዋን እና ከህንድ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር ላይ ላሉት ስልታዊ ፍላጎቶቿ ምክንያት ወሳኝ የሆኑ የላቁ ሥርዓቶችን በመጠቀም የአገሪቱን ወታደራዊ ኃይል በማዘመን ላይ እንደሆኑ ተነግሯል።
የኔቶ አባል ሃገራት
በተቋሙ የወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው የጂኦፖለቲካዊ ውጥረቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ የጦር መሳሪያ ገቢን እንዴት እንደሚያሳድጉ ያሳየ ሲሆን፥ በአውሮፓ ሩሲያ ዩክሬንን በወረረችበት ወቅት የኔቶ አባል አገሮች ወታደራዊ ወጪያቸውን መጨመራቸው፥ በዚህም ምክንያት በተለያዩ አገሮች ያሉ የጦር መሣሪያ አምራች ኩባንያዎች የሽያጭ ጭማሪ አሳይተዋል።
ሩሲያ
ሩስያን አስመልክተው የሚወጡ አሃዞች ምንም እንኳን ያልተሟሉ ቢሆኑም ኢኮኖሚው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ግልጽ ምልክት ይሰጣል ተብሏል። ሪፖርቱ እንደሚያሳየው የሁለቱ የሩሲያ የጦር መሳሪያ አምራች ቡድኖች የሽያጭ መጠን በ40 በመቶ ከፍ ያለ ሲሆን፥ ይህም የሆነበት ዋነኛው ምክንያት በመንግስት ባለቤትነት የሚተዳደረው ሮስቴክ 49 በመቶ የሽያጭ ጭማሪ በማስመዝገቡ ነው ተብሏል።
የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች
ግጭትና ውጥረት በማይለየው መካከለኛው ምሥራቅ የጦር መሳሪያ ግዢ ፍላጎት በፍጥነት እያደገ ይገኛል። በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት ወደዚህ አካባቢ የተሸጠው የጦር መሳሪያ መጠን ቀደም ሲል ከነበሩት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር በ25 በመቶ ከፍ ብሏል።
በመካከለኛው ምስራቅ ያሉ የጦር መሳሪያ አምራቾችም በዩክሬን ጦርነት እና በእስራኤል-ሃማስ ጦርነት ምክንያት በአማካይ የ18 በመቶ የሽያጭ ጭማሪ አሳይተዋል።
ሦስቱ ታዋቂ የእስራኤል አምራቾች የ13.6 ቢሊዮን ዶላር ሽያጭ ያስመዘገቡ ሲሆን፥ ይህም ከ 2014 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር በ15 በመቶ ከፍ ብሏል። ሰው አልባ አውሮፕላኖችን የሚያመርተው ባያካርን የመሳሰሉ የጦር መሳሪያ የሚያመርቱ በቱርክ ውስጥ የተመሰረቱት ሶስት ቡድኖች የሽያጭ መጠናቸው በ 24 በመቶ ጭማሪ ማሳየታቸው ተነግሯል።
እስያ
ቻይና ከታይዋን ጋር ባላት የሉዓላዊነት ጥያቄ እንዲሁም በህንድ-ቻይና የድንበር ግጭት ስጋት ምክንያት በእስያ ለጦር መሳሪያ የሚመደበው ገንዘብ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መጥቷል።
በተለይ አራቱ የደቡብ ኮሪያ የጦር መሳሪያ አምራቾች የሽያጭ መጠናቸው እየጨመረ የመጣበት ምክንያት በአከባቢው ሃገራት እየተለመደ የመጣው ራስን በጦር መሳሪያ የማስታጠቅ አዝማሚያ ከፍ ማለቱ እንደሆነ እና ገቢያቸው በአማካይ 39 በመቶ መጨመሩ አንዱ ማሳያ ነው ተብሏል። ከዚህም በተጨማሪም አምስት የጃፓን ኩባንያዎች የሽያጭ መጠናቸው በአማካይ የ35 በመቶ ጭማሪ አሳይተዋል።
ለጦር መሳሪያ ቅነሳ ር.ሊ. ጳጳሳት በተደጋጋሚ ያቀረቡት ጥሪ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለጦር መሣሪያ ማምረቻ የሚወጣውን ገንዘብን በቀጥታ ድህነትን ለመቅረፍ፣ ለልማት፣ ለጤና እና ለትምህርት እንዲውል በማድረግ የዓለምን ረሃብ ማስወገድ ይቻል እንደነበር በመናገር፥ ሰላም በምድራችን ላይ እንዲሰፍን ያለመታከት የጦር መሣሪያ ኢንዱስትሪውን መስፋፋትን እና ጦርነቶችን የሚያቀጣጥሉትን “የሞት መሣሪያዎች” ምርትን በማውገዝ ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ እንደነበር ይታወቃል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ በቅርቡ በብራዚል ሪዮ ዴጄኔሮ ለጂ-20 ቡድን አባላት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ይሄንን ሃሳባቸውን በማጉላት ረሃብንና ድህነትን የሚያስከትሉትን ለጦር መሣሪያ፣ ለስግብግብነት እና ለኢፍትሃዊነነት የሚወጣውን ወጪ አውግዘው የሰላም ጥሪያቸውን በድጋሚ አስተላልፈዋል።