ፈልግ

ፕሬዝደንት በሽር አል አሳድ ከስልጣን ከተወገዱ ህዝቡ ደስታውን ሲገልጽ ፕሬዝደንት በሽር አል አሳድ ከስልጣን ከተወገዱ ህዝቡ ደስታውን ሲገልጽ  

አማፂያኑ የአሌፖ ከተማን ከተቆጣጠሩ በኋላ በህዝቡ ዘንድ ብሩህ ተስፋ ይታያል ተባለ

የሶሪያ ሁለተኛዋ ትልቋ ከተማ አሌፖ ከህዳር 20 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ‘ሃያት ታህሪር አል ሻም’ ተብሎ በሚጠራው እስላማዊው ቡድን ቁጥጥር ሥር መተዳደር የጀመረች ሲሆን፥ የማሪያም ታናናሽ ወንድሞች ማህበር አባል የሆኑት ወንድም ጆርጅ ሳቤ ለቫቲካን ዜና እንደገለጹት ከተማዋ መረጋጋትዋን ተከትሎ ወደ ቁምስናቸው መመለሳቸውን እና ክርስቲያናዊ ስርዓቶችም እንደወትሮው መቀጠላቸውን ተናግረዋል።

አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የማሪያም ታናናሽ ወንድሞች ማህበር ወይም ‘ሜሪስት’ ተብለው የሚታወቁት ገዳማዊያን አባል የሆኑት ወንድም ጆርጅ ሳቤ ከአሌፖ በመረጋጋት እና በእፎይታ መንፈስ ውስጥ ሆነው በስልክ እንደተናገሩት “እዚህ የመጣሁት መልካም ዜና ላበስር ነው፥ አሁን በደንብ ተረጋግቻለው” ብለዋል።

አሁን ያሉበት የዕለት ተዕለት ህይወታቸው የአማፂ ቡድኑ ከመምጣቱ በፊት ከነበረው ህይወት ጋር በጣም ተመሳሳይ መሆኑን ያስረዱት ወንድም ጆርጅ፥ ምንም እንኳን ትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች ገና ሥራ ባይጀምሩም የህዝቡ እንቅስቃሴ እንደ ወትሮው መሆኑን እና አብዛኛው ሱቆች ክፍት መሆናቸውን ካስረዱ በኋላ፥ ከሁሉም በላይ ደግሞ ‘በከተማው ውስጥ እውነተኛ መረጋጋት መኖሩን’ ጠቁመዋል።

በሶሪያ ሁለተኛ ትልቋ ከተማ የሆነችው አሌፖ፣ በኢስላማዊው አንጃ ሀያት ታህሪር አል ሻም (HTS) በሚመራው አማፂ ቡድኖች ቁጥጥር ስር ከገባች ከአንድ ሳምንት በላይ ያስቆጠረች ሲሆን፥ እነዚህ ቡድኖች እንደ ውሃ፣ መብራት እንዲሁም የዳቦ እና የምግብ አቅርቦቶችን የመሳሰሉ መሰረታዊ አገልግሎቶች ስርጭትን ወደ ነበሩበት ለመመለስ እየሰሩ እንደሆነም ጭምር አስረድተዋል።

በሰሜናዊ ሶሪያ በምትገኘው የአማፂያኑ ጠንካራ ይዞታ በሆነችው ኢድሊብ ከተማ በ 2009 ዓ.ም. በተመሰረተው ‘ሃገርን ማዳን’ ተብሎ ከሚታወቀው የመንግሥት ሥርዓት ጋር የሚመሳሰል የአስተዳደር ሞዴል ቀስ በቀስ ተግባራዊ እየሆነ እንደሆነም ተነግሯል።

ከዚህም በተጨማሪ አማፅያኑ በድህረ ገጻቸው ላይ ዝርዝር መረጃ የያዙ አገልግሎቶችን እና አድራሻዎችን አስፍረዋል ሲል ኤ.ኤፍ.ፒ. የዘገበ ሲሆን፥ ወንድም ጆርጅ ሳቤ ይሄንን አስመልክተው እንደተናገሩት “አማፂያኑ በሃገሪቱ  የኢንዱስትሪውን እንቅስቃሴ ለማነቃቃት እና መላውን ሕዝብ ለማረጋጋት ዓላማ አላቸው” ብለዋል።

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የመጠጥ ውሃ በተለያዩ ሰፈሮች እየተከፋፈለ ሲሆን፥ የመብራት አገልግሎትም በከፊል ወደነበረበት መመለሱ ተመላክቷል።

የአናሳ ክርስቲያኖች እጣ ፈንታ
በሀያት ታህሪር አል ሻም የሚመራው የአማፂያን ቡድን አሌፖን ከተቆጣጠረ በኋላ፣ የክርስቲያን ክብረ በዓላት መጀመሪያ አከባቢ ቆመው የነበረ ሲሆን፥ ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ እንደወትሮው መከበር መጀመራቸው ተመላክተዋል።

ወንድም ሳቤ ይሄንን ሲገልጹ “በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል እንደነበረው ሁሉ፣ እዚህም እንቅስቃሴያችንን እንድንቀጥል ተጋብዘናል፥ ለዚህም ከባለሥልጣናት የደህንነት ማረጋገጫ አግኝተናል” ያሉ ሲሆን፥ “ከሌሎች እኩል እንደ ዜጋ እንደምንቆጠር ተስፋ አደርጋለሁ” ካሉ በኋላ፥ “ሁለተኛ ዜጋ መሆን ወይም ጥበቃ እንደሚደረግላቸው አናሳ ቁጥር ያላቸው ሃይማኖቶች መታየት አንፈልግም፥ እኛ በእውነት እኩል ዜጎች መሆን እንፈልጋለን” ሲሉም አክለዋል።

የወጣቱ መመለስ የተስፋ ጭላንጭል ነው
በአሳድ መንግስት የተፈናቀሉ ሶሪያዊያን ወደ ቤታቸው እንዲመለሱም የተጠየቀ ሲሆን፥ ወንድም ሳቤ፣ አማፂያኑ ወደ ከተማዋ በገቡበት ወቅት ሸሽተው የሄዱ በርካታ ሰዎች አሁን ላይ መመለሳቸው በጣም እንዳስደሰታቸው በመግለጽ፥ በተጨማሪም ቀደም ሲል ለውትድርና አገልግሎት ተመልምለው የነበሩ ወጣት ወንዶች ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘት ችለዋል ብለዋል።

በውጭ አገር የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሶርያውያን ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ጥሪ በመደረጉ እና በዚህም ምክንያት አንዳንድ ህፃናት በሕይወታቸው ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የሶሪያን መሬት እንደሚረግጡ የገለጹት ወንድም ጆርጅ፥ “ወደ አገራቸው መመለስ እና ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልጉ ሰዎችን ማየት ተስፋ ሰጪ ምልክት ነው” ብለዋል።

በጎርጎሳዉያኑ 2011 የተቀሰቀሰው የሶሪያ ግጭት ሀገሪቱን ቀውስ ውስጥ ከቷት ያለፉትን 13 ዓመታት ገደማ የደም ምድር አድርጓታል። በጦርነቱ ግማሽ ሚሊዮን ያህል ሶሪያዉያን ተገድለዋል፤ ከስድስት ሚሊዮን የሚልቁቱ ደግሞ ሀገር ጥለው በመላው ዓለም በስደት ተበትነዋል። በጦርነቱ ሶሪያ ከደረሰባት ሰብአዊ ውድመት እና ማህበራዊ ቀውስ ባሻገር በገንዘብ ሊገመት የማይችል የንብረት ውድመት ደርሶባታል። ውብ ከተሞቿ በደረሰባቸው ውድመት እንዳልነበር ሆነው በትዝታ ሲቀሩ ፤ ታሪካዊ፣ ዓለም ያደነቃቸው እና በቅርስነት የመዘገባቸው በርካታ ታሪካዊ ቅርሶች ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል።

ወንድም ጆርጅ ስለ ደማስቆ አገዛዝ ፈጣን ውድቀት እና ስለ ወደፊቱ ጊዜ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፥ “ይህ የአዲስ ምዕራፍ ጅማሮ ነው፥ ሙሉ በሙሉ ተስፋ አደርጋለሁ ባልልም፣ ነገር ግን ተስፋችንን በእርግጠኝነት መገንባት ጀምረናል፥ ይሄንንም ስናደርግ በጥበብ እና በማስተዋል አገራችንን እንገነባለን” በማለት አጠቃለዋል።
 

11 December 2024, 14:09