ፈልግ

በሩዋንዳ የተፈጸመ የዘር ማጥፋት ወንጀል መታሰቢያ በሩዋንዳ የተፈጸመ የዘር ማጥፋት ወንጀል መታሰቢያ   (AFP or licensors)

የዘር ማጥፋት ወንጀልን ለመከላከል ገና ረጅም መንገድ መጓዝ እንደሚገባ ተነገረ

የዘር ማጥፋት ወንጀል፣ የሰለባዎቹ ሰብዓዊ ክብር እና ወንጀሉን የመከላከል ዓለም አቀፍ ቀን ሰኞ ኅዳር 30/2017 ዓ. ም. ተከብሯል። ወንጀሉን በመቅረፍ ረገድ በተገኘው ለውጥ ላይ በማሰላሰል በዓለም ዙሪያ መሰል ጭካኔያዊ ተግባሮችን በመከላከል ረገድ ቀጣይ ተግዳሮቶች መኖራቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በታኅሳስ 9/1948 የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ የዘር ማጥፋት ወንጀልን መከላከል እና በወንጀሉ መጣል የሚገባውን ቅጣት በአንድ ድምፅ አጽድቋል። ይህም የዘር ማጥፋት ወንጀልን እንደ ወንጀል እና ግልጽ የሆነ የሰብዓዊ መብት ረገጣ መሣሪያነት ለመፈረጅ የመጀመሪያ ስምምነት እንደሆነ ታውቋል።

የተባበሩት መንግሥታት የዘር ማጥፋት ወንጀል፣ የሰለባዎቹ ሰብዓዊ ክብር እና የወንጀሉ መከላከያ ዓለም አቀፍ ቀን 76ኛ ዓመት መታሰቢያ በተከበርበት በዘንድሮው ዓመት፥ መንግሥታት እና መሪዎቻቸው ሰዎችን በዘራቸው፣ በብሔራቸው ወይም በሃይማኖታቸው ምክንያት የዘር ማጥፋት ወንጀል በመፈጸም እየተከሰሱ ይገኛሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ኮንቬንሽን መሰል ድርጊቶችን ለመለየት እና ወንጀለኛ ለማድረግ ቢረዳም፥ ወንጀሉን ሙሉ በሙሉ መከላከል አልቻለም። እንዲያውም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1948 ጀምሮ በዓለም ዙሪያ ያሉ የተለያዩ ሕዝቦች የዘር ማጥፋት እልቂት እየደረሰባቸው ይገኛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፍልስጤም እና በሱዳን ዳርፉር ግዛት የዘር ማጥፋት እልቂት ይፈጸማል የሚል ስጋት በግንባር ቀደምነት ተነስቷል።

የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከል ልዩ አማካሪ ወ/ሮ አሊስ ዋይሪሙ በሱዳን ስላለው ሁኔታ በማንሳት፥ ምክር ቤቱ የዘር ማጥፋት አደጋ ምልክቶችን በከፍተኛ ሁኔታ መመልከቱን እና ወንጀሉ ቀድሞውኑ ተፈጽሟል የሚል ውንጀላን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በግንቦት 2024 ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

“ንጹሃን ዜጎች ዛሬም ቢሆን ከአደጋው አልተረፉም ያሉት ወ/ሮ አሊስ ዋይሪሙ፥ በሲቪሉ ሕዝብ ላይ የሚፈጸም የዘር ማጥፋት ወንጀል በማንነት ላይ የተመሠረተ እንደሆነም አስረድተዋል። በዳርፉር እና በኤል ፋሸር የሚኖሩ ንፁሃን ዜጎች ጥቃት የሚፈጸመባቸው በቆዳቸው ቀለም፣ በብሔራቸው እና በማንነታቸው ምክንያት እንደሆነ አክለው አስረድተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል በጋዛ ሕዝቦች ላይ የምትፈጽመው ከፍተኛ የነፍስ ማጥፋት ተግባር የቀጠለ ሲሆን አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ በርካታ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች “እስራኤል በፍልስጤም ሕዝብ ላይ እየፈጸመች ያለው ድርጊት የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው” በማለት የሚያቀርቡትን ክስ እስራኤል “በውሸት ላይ የተመሠረተ ነው” በማለት ማስተባበሏን ገልጸዋል።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ሌሎች የመብት ተሟጋች ቡድኖች፥ በሁቱም የዓለም ክፍሎች የሚፈጸሙት ሁከቶች ዘርን ማጥፋት እና ይህን ተግባር ኢላማ ያደረገ ጥቃት ተብሎ ሊገለጽ እንደሚችል የገለጹ ሲሆን፥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለምሳሌ በሩዋንዳ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወይም ከዚያ ያነሰ በአርሜኒያ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ተግባር በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ቸልተኝነት የተፈጠረ የአመጽ እና የእንግልት ጠባሳ መሆኑ ይታያል።

በአርሜኒያውያን ላይ የተፈጸመ የዘር ማጥፋት ወንጀል (1915-1923)
“በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1915 እስከ 1923 የኦቶማን አገዛዝ በአርሜኒያውያን ላይ የፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል የመጀመሪያው ነበር” በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወንጀሉ የተፈጸመበትን መቶኛ ዓመት በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሚያዝያ 12/2015 ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ማክበራቸው ይታወሳል።

በእነዚያ ስምንት ዓመታት ውስጥ ሁለት ሚሊዮን አርመናውያን በግፍ መገደላቸውን እና መሰቃየታቸውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አምነዋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 1915 የኦቶማን ባለስልጣናት የአርመንን ሕዝብን ለማጥፋት ሲሉ ምሁራንን እና የማኅበረሰብ መሪዎችን በማሰር እና በመግደል የዘር ማጥፋት ዘመቻን የጀመሩበት ዓመት ነበር። የዘር ማጥፋት ዘመቻው ያነጣጠረው የኦቶማን አገዛዝ ከመፈጠሩ ከረጅም ጊዜ በፊት በክልሉ ውስጥ ለዘመናት በኖረው የአርመን ጎሳዎች ላይ ነበር። በቀጠሉት በርካታ ዓመታትም አርመኖች ከአያት ቅድመ አያቶቻቸው ዘንድ በግዳጅ ተወስደዋል። ብዙ ጊዜ በሶርያ በረሃ ውስጥ ወደሚገኙ ማጎሪያዎች ተወስደው በሞት ይቀጡ ነበር። በጉዞ ላይ እያሉ ለረሃብ፣ ለበሽታ እና ለአስቸጋሪ ሁኔታዎች በመጋለጣቸው ብዙዎች ሞተዋል። እንደዚሁም የኦቶማን ወታደሮች ወንዶችን፣ ሴቶችን እና ሕፃናትን በአሰቃቂ ሁኔታ ፈጅተዋቸዋል። 

በሩዋንዳውያን ላይ የተፈጸመ የዘር ማጥፋት ወንጀል (1994)
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ልክ ከ30 ዓመታት በፊት ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1994 በሩዋንዳ የሚገኙ አክራሪ ሁቱ ሚሊሻዎች ከ800,000 የሚበልጡ ቱትሲዎችን እና ለዘብተኛ ሁቱዎችን የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ተብሎ በሚታወቀው ሁከት ገድለዋል። የዘር ጭፍጨፋው የተቀሰቀሰው በፕሬዚዳንት ጁቬናል ሃቢያሪማና ግድያ ሲሆን፥ የመንግሥት እና የጦር ሠራዊት አባላትን ጨምሮ በአናሳ የቱትሲ ጎሳዎች እና ከእነርሱ ርዕዮተ ዓለም ተቃራኒ የሆኑትን ሁሉ ለማጥፋት የተፈፀመው ነበር። ለ100 ቀናት የዘለቀው ይህ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንደ ጅምላ ግድያ፣ ጾታዊ ጥቃት እና መላውን ማኅበረሰብ ማውደም የመሳሰሉ አሰቃቂ ድርጊቶችን ያካተተ ነበር።

እየሆነ ያለው ግልጽ ቢሆንም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እርምጃ ለመውሰድ እጅግ ዘግይቷል። በሩዋንዳ የነበሩት የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ሃይሎች ውጤታማ ባለመሆናቸው እና ግድያው በመቀጠሉ የምዕራባውያን መንግሥታት ጣልቃ ሊገቡ አልቻሉም። በሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈጸም እና በቦስኒያ ጦርነት ሲካሄድ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሲሆኑ፥ በሩዋንዳ የተፈፀመውን ድርጊት “አሳዛኝ የዘር ማጥፋት ወንጀል” ሲሉ ገልጸው በሕዝቡ ላይ በሚደርሰው ስቃይ የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸዋል።

ጭካኔያዊ ተግባር ሲፈጸም ምዕራባውያን በርቀት ቆመው ይመለከቱት ነበር። በወቅቱ አሜሪካ ባዘጋጀችው የዓለም የእግር ኳስ ጨዋታ ብራዚል አሸናፊ ሆነች። ጄፍ ቤዞስ የአማዞን ተቋምን አስጀመረ። ለመጀመሪያ ጊዜ የጽሑፍ መልዕክት መላክ ተቻለ። በጃፓን “ፕሌይ ስቴሽን” (PlayStation) የተባለ የመዝናኛ ፕሮግራም ተለቀቀ። በተመሳሳይ ዓመትም የማስተርችት ስምምነት በአውሮፓ ተግባራዊ ሆነ። በደቡብ አፍሪካ ኔልሰን ማንዴላ ከእስር ተፈታ። ነገር ግን ይህ ሁሉ ሲሆን የሩዋንዳ ሕዝብ ሊታሰብ የማይችል የጭካኔ ተግባር ተፈጽሞበታል።

ዋና ዋና የተባሉ ኃያላን መንግሥታትን ጨምሮ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረቱን በሌሎች ጉዳዮች ላይ በማድረግ፥ ለምሳሌ ለስሬብሬኒካ እልቂትን ምክንያት በሆነው የቦስኒያ ጦርነት፣ በጊዜው የቦስኒያ-ሰርብ ሃይሎች በተባበሩት መንግሥታት የተመደበውን የስሬብሬኒካ አስተማማኝ ቦታን በመቆጣጠር ወደ 8,000 የሚጠጉ የቦስኒያ ወንዶችን እና ልጆችን ገድለዋል። ይህ እልቂት ሌሎቹ ጦርነቶች ከሚያስከትሉት የሰው ሕይወት መጥፋት ጋር ተዳምሮ በብዙ መንግሥታት እና ተቋማት ዘንድ እንደ ዘር ማጥፋት ወንጀል ተቆጥሯል።

የታዩ ድክመቶችን በመቀበል የተወሰዱ እርምጃዎች
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1994 የተፈጸመውን የሩዋንዳ የዘር ማጥፋት ወንጀልን ተከትሎ ለችግሩ ምላሽ በመስጠት ረገድ ያሳየውን ድክመት በመገንዘብ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተባበሩት መንግሥታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ ከፍተኛ ማሻሻያዎችን በማድረግ፥ ከአደጋ የመጠበቅ ኃላፊነት አስተምህሮ (R2P) እንዲዳብር አድርጓል። አስተምህሮው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የአንድ አገር ሕዝብ ለጅምላ ግድያ በሚጋለጥበት ወቅት የመከላከል እና ጣልቃ የመግባት ሃላፊነት እንዳለበት አፅንዖት ይሰጣል።

ይሁን እንጂ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጣልቃ በመግባት ግጭቶችን ለማስቆም ባሳየው ፍላጎት እና ባስመዘገበው ስኬት ላይ ማተኮር አስፈላጊ ነው። ቀደም ሲል በተጠቀሰው የቦስኒያ ጦርነት ውስጥ (1992-1995) ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ጣልቃ በመግባት በተለይም ከስሬብሬኒካ እልቂት በኋላ የኔቶ ኃይል ሁከት እንዲቆም እገዛ አድርጓል። መጀመሪያ ላይ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እርምጃ ለመውሰድ የዘገየ ቢሆንም ተከታዩ ወታደራዊ ጣልቃገብነት ጦረኛ ወገኖችን ወደ ድርድር እንዲመጡ በማስገደድ ደም መፍሰስ እንዲቆም ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።

ነገሮች እንደሚሻሻሉ ተስፋ አለ
ዛሬ በዓለማችን ላይ እየደረሰ ያለውን ብጥብጥ እና ሰቆቃ እንዲሁም ሱዳንን ጨምሮ የተወሰኑ አካባቢዎች ከምዕራቡ ዓለም ትኩረት መነፈጋቸውን ለይቶ ማወቅ አያዳግትም። ሆኖም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውሳኔዎች ሥራ ላይ ባሉበት እና በቀጠለው የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት አንዳንድ ትምህርቶችን መውሰድ ተችሏል። እውነታው የሚነግረን ገና ብዙ እንደሚቀር ነው። ነገር ግን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአንድነት በመሰባሰብ በዓለም ዙሪያ እየተፈጸመ ያለውን ግፍና በደል ለማረጋገጥ ጥረት እንደሚያደርግ ተስፋ አለ። እነዚህ ግፎች እና በደሎች በይፋ እና በሕጋዊ መንገድ “የዘር ማጥፋት ወንጀል” ተብለው ሊፈረጁ ይችላሉ ወይስ አይችሉም? ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ጦርነት ምን ጊዜም ቢሆን ሽንፈት ነው” ሲሉ ደጋግመው መናገራቸው ይታወሳል።

 

10 December 2024, 16:32