ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሞት ፍርድ እስረኞችን ቅጣት ወደ እስራት መቀየራቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የስልጣን ዘመናቸው ከማብቃቱ በፊት ባደረጉት የምህረት እርምጃ በፌደራል የሞት ፍርድ ከተፈረደባቸው 40 እስረኞች መካከል የ37ቱን የቅጣት ፍርድ ወደ እድሜ ልክ እስራት አሻሽለውታል።
የቅጣት ማቅለያው አስተዳደራቸው በፌዴራል ደረጃ ከሽብርና ጥላቻ ተኮር ግድያዎች ውጪ የሞት ቅጣትን ለማስቀረት በወሰነው መሠረት የተከናወነ መሆኑን ያስታወቁ ሲሆን፥ ባይደን በዚህን ወቅት እንደተናገሩት እነዚህ ነፍሰ ገዳዮች በፈጸሙት አፀያፊ ተግባር ሰለባ ለሆኑት እና ሊጠገን የማይችል ኪሳራ ላጋጠማቸው ቤተሰቦች ሁሉ ከልብ ማዘናቸውን ውሳኔያቸውን ባስታወቁበት መግለጫ ገልጸዋል።
ፕረዚዳንት ባይደን አክለውም “በህሊናዬ እና በተሞክሮዬ በመመራት... በፌዴራል ደረጃ የሞት ቅጣትን መጠቀም ማቆም እንዳለብን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እርግጠኛ ሆኛለው” ካሉ በኋላ አዲሱ አስተዳደር የሞት ቅጣትን እንዲያቆም ጥሪ አድርገዋል።
ሆኖም ግን ዶናልድ ትራምፕ በሚቀጥለው ጥር ወር ላይ የፕሬዝዳንትነት ቃለ መሃላ ከፈጸሙ በኋላ በፌዴራል ደረጃ የሞት ቅጣቱን እንደሚቀጥሉ ቢያስታውቁም፥ ባይደን አሁን ላይ ለሞት ፍርደኞች ያደረጉትን የምህረት ውሳኔ ተተኪያቸው ሊሽሩት እንደማይችሉ ግን ተገልጿል።
ትራምፕ በቀድሞው የስልጣን ዘመናቸው ከሃያ ዓመታት እገዳ በኋላ የፌዴራል ግድያዎችን እንደገና አስጀምረው የነበረ ቢሆንም ጆ ባይደን ወደ ሥልጣን ሲመጡ ውሳኔውን ሽረው እንደነበር ይታወቃል።
ባይደን የሞት ፍርድ እስረኞችን ቅጣቶች ለማቃለል የወሰዱት ውሳኔ በሽብርተኝነት እና በጥላቻ ምክንያት በጅምላ ግድያ የተከሰሱ ሶስት እስረኞችን አያካትትም። ውሳኔውን ተከትሎ በፌዴራል ደረጃ የሞት ቅጣት የሚጠብቃቸው ሦስት ፍርደኞች ናቸው። እነዚህም በደቡብ ካሮላይና ዘጠኝ ጥቁር የቤ/ክ ዓባላትን የገደለው ዲላን ሩፍ፣ በቦስተን ማራቶን የቦምብ ጥቃት የፈጸመው ጆሃር ሳርናዬቭ እንዲሁም በፒትስበርግ የአይሁድ ቤተ እምነት ውስጥ 11 ሰዎችን የገደለውና በአሜሪካ ታሪክ በርካታ ሕይወት የጠፋበት ፀረ አይሁድ ጥቃት ተብሎ የተመዘገበውን ድርጊት ፈጽሟል የተባለው ሮበርት ባወርስ ናቸው።
ከእነዚህም በተጨማሪ በመንግስት ደረጃ ሞት የተፈረደባቸው ከ2,200 በላይ የሚሆኑ እስረኞች ላይ ፕሬዝዳንቱ ምንም ስልጣን እንደሌላቸው ተገልጿል።
የሃይማኖት መሪዎች ውሳኔውን በደስታ ተቀብለዋል
የአሜሪካ ብጹአን ጳጳሳትን ጨምሮ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ መንፈሳዊ መሪዎች የፕሬዚዳንቱን ውሳኔ በደስታ ተቀብለዋል።
የዋሽንግተን ዲ.ሲ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ዊልተን ግሪጎሪ ፕሬዚዳንት ባይደን ያስተላለፉትን የሞት ፍርድ ማቅለያ ውሳኔ ማድነቃቸውን ገልጸው “በሌሎች ሰዎች ሕይወት ላይ እንደዚህ ዓይነት ስቃይ እና መከራ ያደረሱትን የእነዚያ ሰዎች ሕይወት እንኳን ሳይቀር ለሰው ልጅ የበለጠ ክብር ለመስጠት አንድ አስፈላጊ እርምጃ ነው” ብለዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ግሪጎሪ በመግለጫቸው፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከቀደምቶቹ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሃሳብ ጋር በሚስማማ መልኩ የሞት ቅጣትን “የሰው ልጅ ማኅበራዊና ሥነ ምግባራዊ ክብር የሚጻረር እና ለህብረተሰቡ ጥበቃ ለማድረግ አስፈላጊ አይደለም” በማለት ገልጸው እንደነበር አስታውሰው፥ “የሞት ቅጣት ለሰዎች ህይወት ያለንን ሰብዓዊ ክብር የሚያሳጣ አንድ ተጨማሪ ተግባር ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ መሪ ሊቀ ጳጳስ ቲሞቲ ብሮሊዮ በበኩላቸው የባይደንን ውሳኔ በማድነቅ ፕረዚዳንቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እና ሌሎች በርካታ ሰዎች ያቀረቡትን ጥሪ በመስማት እና በመታዘዛቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። በተመሳሳይ ጊዜ እነዚህ ግለሰቦች ለወጡበት ማህበረሰብ ኃላፊነት ስላለባቸው ሕይወታቸው ሊወሰድባቸው እንደማይገባ በመገንዘባቸው በጣም መደሰታቸውን እና ጆ ባይደን በፕረዚዳንትነት የመጨረሻ የስልጣን ዘመናቸው ይሄንን እርምጃ በመውሰዳቸው አመስግነዋቸዋል።
የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጥሪ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በቅርቡ ለ2025 የዓለም የሰላም ቀን ያስተላለፉትን መልዕክት ጨምሮ የሞት ቅጣት እንዲወገድ በተደጋጋሚ ጥሪ ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን፥ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ባቀረቡት የመልዓከ እግዚያብሄር ጸሎት ላይ ምዕመናን በዩናይትድ ስቴትስ በሞት ፍርድ ላይ ላሉ እስረኞች እንዲጸልዩ ጥሪ በማቅረብ፣ እንዲሁም በፍርደኞቹ ላይ የተላለፈው የሞት ፍርድ ውሳኔ እንዲሻሻል ምዕመኑ ጠንክሮ እንዲጸልይ በማሳሰብ፣ “እነዚህን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችንን እናስብ፥ ጌታ አምላካችን ከሞት እንዲያድናቸው ጸጋውን እንለምነው” ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ታህሳስ 10 ቀን 2017 ዓ.ም. ከጆ ባይደን ጋር በስልክ ባደረጉት ውይይት ወቅት ጥሪያቸውን በድጋሚ ማቅረባቸው ተገልጿል።
የዩናይትድ ስቴትስ ብጹአን ጳጳሳት እንደ ካቶሊክ ሞቢሊዚንግ ኔትወርክ እና ሌሎች የሃይማኖት እና የሰብአዊ ተሟጋች ቡድኖች የመሳሰሉ የካቶሊክ ድርጅቶች ጥሪዎችን በማስተጋባት ጆ ባይደን የፌዴራል የሞት ፍርድ እስረኞችን ቅጣት እንዲያቃልሉ ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል።