ፈልግ

የሶርያ ጦርነት የሶርያ ጦርነት  (AFP or licensors)

ብፁዕ ካርዲናል ዘናሪ በሶርያ ዕርቅ እንደሚወርድ እና ማዕቀብ እንደሚነሳ ያላቸውን ተስፋ ገለጹ

እስላማዊ አማፂ ሃይሎች ወደ ሶርያ ዋና ከተማ ደማስቆ የገቡ ሲሆን ፕሬዚደንት አል አሳድ ሀገሪቱን ለቀው መውጣታቸው ተነግሯል። በደማስቆ የሚገኙት የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ብፁዕ ካርዲናል ዘናሪ፥ የሶርያ መዲና ደማስቆ አሁን በአማፂያኑ እጅ በገባችበት የመጨረሻዎቹ ሰዓታት ላይ ሲናገሩ፥ አገሪቱ ከገባችበት ችግር ወጥታ በሰላም አብሮ የመኖር እና ከምንም በላይ ለሃይማኖታዊ ወጎች አክብሮት እንደሚሰጣቸው ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ ዓለም አቀፍ ማዕቀቦችን ማስወገድ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እስላማዊ አማፂ ሃይሎች መብረቃዊ ወረራን የጀመሩት ባለፈው ሳምንት ሲሆን፤ ወደ ደማስቆ ከመዝለቃቸው በፊት አሌፖን፣ ሃማን እና ሆምስን በፍጥነት መያዛቸው ታውቋል። የመንግሥት ተቃዋሚ ኃይሎች እሁድ ዕለት ማለዳ የቴሌቭዥን እና የሬድዮ ጣቢያዎችን በተቆጣጠሯቸው ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ‘የደማስቆን ውድቀት እና የፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድ መንግሥት ማብቃቱን’ አስታውቀዋል።

የሶርያው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መሐመድ ጋዚ ጃላሊ ለህዝቡ ባደረጉት ንግግር፥ በስልጣናቸው እንደሚቀጥሉ እና በሀገሪቱ ያለውን ቀጣይ አስተዳደር ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። የሃያት ታህሪር አል ሻም (ኤችቲኤስ) አማፂ ቡድን መሪ አቡ ሙሐመድ አል ጁላኒ፥ ኃይሎቻቸው ወደ ሕዝባዊ ሕንፃዎች እና ተቋማት እንዳይቀርቡ ከልክለው፥ በይፋ ተላልፈው እስኪሰጡ ድረስ በሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቁጥጥር ስር እንደሚቆዩ ገልጸዋል።

የደማስቆ ውድቀት በአሳድ ቤተሰብ እና በሶርያ ባዝ ፓርቲ አገዛዝ 50 ዓመታትን ያስቆጠረ እንደሆነ ታውቋል። ባሽር አል-አሳድ አባታቸውን ሲተኩ እንደ ለውጥ አራማጅ የታዩ ቢሆንም ነገር ግን በአረቡ አብዮት ወቅት በተቃዋሚዎች ላይ በወሰዱት እርምጃ ያ ስማቸው ጠፍቷል።

በዚያን ወቅት በአማፂ ይዞታዎች ላይ የኬሚካል ጦር መሣሪያ መጠቀምን ጨምሮ ከጭካኔያዊ ድርጊቶች ጋር እንደተቆራኙ ይነገርራል። ይህ አጭር ሕዝባዊ አመጽ ሲቪሎችን ሰለባ በማድረግ በሳምንት ጊዜ ውስጥ ተባብሶ ከ 300,000 በላይ ሰዎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎች እንደተገደሉ ወይም እንደቆሰሉ እንደሚታሰብ እና ቢያንስ 370,000 የሚሆኑት ከቀያቸው መፈናቀላቸውን አስታውቋል። የሶርያ አረመኔያዊ የእርስ በርስ ጦርነት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2011 የጀመረው፥ ፕሬዚዳንት አል አሳድ በዴሞክራሲ ጠያቂዎች ላይ እርምጃ ከወሰዱ በኋላ እንደ ነበር ይታወሳል።

በደማስቆ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ብፁዕ ካርዲናል ዘናሪ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ አገሪቱ ከነበረችበት መከራ ወጥታ ለዲሞክራሲያዊ አስተዳደር የሚያበቃት ሰላማዊ ሽግግር እንደምታደርግ ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል።

በዋና ከተማዋ ደማስቆ የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማ የተናገሩት ብጹዕነታቸው፥ በፍርሃት ተውጠው እንደ ነበር ገልጸው፥ አሁንም ቢሆን በጎዳናዎች ላይ የተኩስ እሩምታ የሚሰማ ቢሆንም ብዙ ጭንቀቶችን ፈጥሮ የቆየው ጉዳይ መፍትሄ በማግኘቱ ነዋሪው ደስታውን እየገለጸ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሽግግሩ ያለ ደም መፋሰስ በመከናወኑ ፈጣሪን ያመሰገኑት ብፁዕ ካርዲናል ዘናሪ፥ ከፊታቸው ያለው መንገድ አስቸጋሪ እንደሚሆን ተናግረው፥ የመንግሥት ስልጣንን የተረከቡት ሁሉንም ሰው ለማክበር፣ አዲስ ሶርያን ለመገንባት ቃል መግባታቸውን እና እነዚህን ተስፋዎች እንደሚጠብቁ ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።

“ዓማጽያኑ ከድል በኋላ ወዲያ በአሌፖ ከሚገኙት ብጹዓን ጳጳሳት ጋር ተገናኝተው ልዩ ልዩ ቤተ እምነቶችን እና ክርስቲያኖችን እንደሚያከብሩ አረጋግጠውላቸዋል” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ዘናሪ፥ “ይህን ቃል ኪዳናቸውን ጠብቀው ወደ እርቅ እንደሚሄዱ ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል። ከእርቅ በተጨማሪ ሶርያ ውስጥ የተወሰነ የዕድገት ምልክት እንደሚታይ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ ሰዎች ወደሚሰደዱበት ደረጃ መድረሳቸውን እና በአገራቸው ውስጥ መኖር አለመቻላቸውን አስረድተዋል።

ወጣቶች በአገራቸው ውስጥ ምንም ዓይነት የወደፊት ተስፋ ባለማየታቸው በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ወደ ሌሎች አገራት መሰደዳቸውን ገልጸዋል። በማከልም ከዚህ በፊት የነበራቸው ተስፋ መሞቱን ገልጸው፥ ዛሬ ግን ሶርያውያን ወደ እርቅ እና መልሶ ግንባታ ጎዳና ተመልሰው ቢያንስ ሁሉንም ሰው ወደ ብልጽግና የሚወስደው መንገድ ሊጀመር ይችላል” ሲሉ አስረድተዋል።

“ስልጣኑን የያዙት ሰዎች በዲሞክራሲያዊ መርህ ላይ የተመሠረተች አዲሲቷን ሶርያ ለመፍጠር የገቡትን ቃል እንደሚያከብሩ፥ በአገሪቱ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ለድሆች ከፍተኛ ሸክም መሆኑን በመገንዘብ፥ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማዕቀቡ ቀስ በቀስ እንዲነሳ በማድረግ ምላሽ እንደሚሰጥ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

 


 

09 December 2024, 16:36