የኖቤል የሰላም ተሸላሚው ቶሺዩኪ ሚማኪ ‘የሰውን ልጅ ከኑክሌር ጦር መሳሪያዎች እናድን’ ማለታቸው ተነገረ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
እ.አ.አ. ነሐሴ 6 ቀን 1945 አሜሪካ በሂሮሺማ እና ነጋሳኪ ከተሞች ላይ የአቶሚክ ቦምብ በመጣሏ ወደ 140,000 የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸው የሚታወስ ሲሆን፥ ከዚህ የሂሮሺማ የአቶሚክ ቦምብ ጥቃት የተረፉት ቶሺዩኪ ሚማኪ እና ሌሎች ጃፓናውያን ያቋቋሙት "ሂባኩሻ" ማህበር የ2024 የሰላም ኖቤል ሽልማትን አሸንፏል።
አሁን ላይ የ82 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት ሚማኪ ጥቃቱ በደረሰበት ወቅት የሦስት ዓመት ህፃን የነበሩ ቢሆንም ጥቃቱ ያስከተለውን የማይታሰብ እና አሰቃቂ ክስተት በልጅነት አዕምሮዋቸው መዝግቦ የያዙት ሲሆን፥ ይህንን የሰውን ልጅ ታሪክ ከመቀየር ባለፈ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈውን የሄሮሺማ አሳዛኝ ክስተት ትዝታ ከ ‘ላ ኦዘርቫቶሬ ሮማኖ’ ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ አጋርተውታል።
ሂባኩሻ የተባለው ይህ ማህበር እ.አ.አ. በ1945 በሂሮሺማ እና ናጋሳኪ ከደረሰው የቦምብ ጥቃት የተረፉ ሰዎችን ያቀፈ ማህበር ሲሆን፤ ማህበሩ ዓለምን ከኒውክሌር ጦር መሣሪያ ጥፋት ለመታደግ በተደረገው ጥረት ላበረከተው አስተዋፅኦ በኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ እውቅና በማግኘት ታህሳስ 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ሚማኪ የማህበሩ ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን የኖቤል የሰላም ሽልማትን በኦስሎ ተቀብለዋል።
ለኒውክሌር ጦር መሳሪያ እገዳው መመስረት ትልቅ አስተዋፅዖ አድርጓል የተባለው ይህ ማህበር ሥራውን የጀመረው የሂሮሺማ እና ናጋሳኪ ውድመት ከደረሰ ከ10 ዓመታት በኋላ ሲሆን፥ ከጥቃቱ የተረፉትን ሰዎች በጋራ በማሰባሰብ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዲታገድ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል።
የኖርዌይ የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ ለዚህ ጥረት እውቅና በመስጠት፥ “ሁላችንም የሂባኩሻን ተልዕኮ የማስቀጠል ግዴታ አለብን፥ የእነሱ የሞራል ትግል ለእኛ ትሩፋት ነው፥ አሁን የእኛ ጉዳይ ነው፥ አውዳሚ መሳሪያውን ለማስቆም የሚደረግው ትግል ቀጣይነት ያለው እና ሁለንተናዊ ድጋፍን ይጠይቃል” ብሏል።
ማህበሩ በኒውክሌር ጦር መሳሪያ አጠቃቀም ምክንያት ስለደረሰው "አሰቃቂ ጉዳት" እና ስቃይ የተረፉትን ሰዎች ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች በመላክ ትምህርት ይሰጥ የነበረ ሲሆን፥ ከዚህ ቀደም በ2005 በኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ ልዩ እውቅና ያገኘበትን ጨምሮ ብዙ ጊዜ ለኖቤል ሽልማት እጩ እንደነበር ተጠቅሷል።
ሚማኪ ጥቃቱ በደረሰበት ወቅት የሦስት ዓመት ህፃን እንደነበሩ በማስታወስ፥ ከእናታቸው እና ታናሽ ወንድማቸው ጋር በመሆን በወቅቱ በሂሮሺማ የባቡር መስመር ይሠራ የነበረውን አባታቸውን ሲፈልጉ ለኒውክሌር ቦምቡ ጨረር ተጋልጠው እንደነበር ከገለጹ በኋላ፥ በጥቃቱ ስፍር ቁጥር የሌለው ሰው እንደሞተ፣ በርካታ ሕንፃዎች በእሳት እንደጋዩ እንዲሁም ታናሽ ወንድማቸው አሁን ላይ በጭንቅላት ካንሰር እየተሰቃየ እንደሚገኝ እና ህክምና እየተደረገለት እንደሆነ ገልጸዋል።
እንደነዚህ ያሉትን ትዝታዎች መልሶ ማስታወስ ህመም ቢኖረውም፣ እነዚህን ልምዶች ለሌሎች ማካፈል የሂባኩሻ ማህበር ተልእኮ ወሳኝ ተግባር እንደሆነ የጠቀሱት ሚማኪ፥ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች ጥቃት ፈጽሞ እንደማይደገም ማረጋገጥ ተገቢ እንደሆነ ተናግረው፥ ከቦምብ ፍንዳታው የተረፈው ቀሪ ህይወታቸው ሊያልቅ በተቃረበ ቁጥር ይህ ተልዕኮ ይበልጥ አጣዳፊ እንደሚሆን ገልጸዋል።
“ሂሮሺማ እነዚህን ምስክሮች ለመጠበቅ እርምጃዎችን ወስዳለች” ያሉት ሚማኪ፥ ከተማዋ ወጣቶችን በማስተማር ታሪኮቻቸውን ለመጪው ትውልድ የሚያስተላልፉ መልዕክተኞች እንዲሆኑ በማሰልጠን በርካታ ሥራዎችን እንደሰራች አብራርተዋል።
ሚማኪ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለኒውክሌር ጦር መሣሪያ ቅነሳ ላሳዩት ቁርጠኝነት ጥልቅ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፥ ብጹእነታቸው እ.አ.አ. ጥቅምት 2019 ሂሮሺማን እና ናጋሳኪን በጎበኙበት ወቅት ከእሳቸው ጋር የመገናኘት ዕድል አግኝተው እንደነበር በማስታወስ፥ በወቅቱም ቀይ መያዣ የነበረው ሜዳሊያ እንደሰጧቸው እና የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን ለማጥፋት በርትተው እንዲሰሩ መጠየቃቸውን፣ ብሎም በዕለቱ ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጋር የተነሱትን ፎቶግራፍ በልዩ ሁኔታ እንዳስቀመጡት ገልጸዋል።
ዓለም አቀፋዊ አውዳሚ መሳሪያዎችን የማስፈታት ጥያቄ ቢኖርም፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ አጠቃቀምን እና የአቶሚክ ግጭትን በተመለከተ ውይይቶች ተጠናክረው መቀጠላቸው የሚታወቅ ሲሆን፥ አሁንም የዚያን አስከፊ ቀን ጠባሳ ለተሸከሙት ሚማኪ፣ የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎችን እንደገና ጥቅም ላይ ለማዋል ማሰብ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው።
“የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንደገና ጥቅም ላይ ከዋለ የሰው ልጅ መጨረሻ ነው” ሲሉ ያስጠነቀቁት ሚማኪ ይሄም እንዳይከሰት የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ያላቸው ሀገራት መሪዎች መሳሪያዎቹን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ቁርጠኛ እንዲሆኑ የዘወትር ጥያቄዬ ነው ብለዋል።
ሚማኪ በመጨረሻም በተለይ በጋዛ እና በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ግጭት በጣም አስከፊ መሆኑን ጠቁመው፥ “የሩሲያው ፕሬዝዳንት ፑቲን የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን ለመጠቀም የሚያስችለውን ገደብ በማንሳት በማንኛውም ጊዜ መጠቀም የሚያስችላቸውን ህግ አጽድቀዋል” ሲሉ ስጋታቸውን ከገለጹ በኋላ “የኒውክሌር ጦር መሣሪያ በሰው ሕይወት ላይ የሚያደርሰውን አስከፊ ተጽዕኖ በዓይን አይቶ መመስከር እንዲችል ሁሉም ሰው ወደ ሂሮሺማ እና ናጋሳኪ በመጓዝ የአቶሚክ ቦምብ ሙዚየምን እንዲጎበኝ እጠይቃለሁ” ብለዋል።