ፈልግ

የ2025 የዛይድ ሽልማት የዳኞች ኮሚቴ አባላት ከር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር የ2025 የዛይድ ሽልማት የዳኞች ኮሚቴ አባላት ከር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

የዛይድ ሽልማት እጩዎች ችግር በበዛበት ዓለም ውስጥ ‘የተስፋ ሐዋርያት’ ናቸው ተባለ

የ2025 የዛይድ ሽልማት ለሰብዓዊ ወንድማማችነት የዳኞች ኮሚቴ አባላት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ሳምንታዊ ጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮን ከተከታተሉ በኋላ ከብጹእነታቸው ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ ሰዎች ሰላምን እና ወንድማማችነትን ለማጎልበት ለሚያደርጉት ከፍተኛ ጥረት እውቅና መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በርካታ ሚሊዮን ህዝብ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት እየተቸገረ እና በቆሻሻ ክምር ውስጥ ምግብ እየፈለገ ለረሃብ በተጋረጠበት በአሁኑ ወቅት ዓለም ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለጦር መሣሪያ ምርት እና ግዢ እያወጣች መሆኑ እንደሚያሳስባቸው ለኮሚቴው አባላት ገልጸዋል።

የዓለም ንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ንጎዚ ኦኮንጆ-ኢዌላ ቅዳሜ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ለድሆች ደህንነት ስላላቸው ስጋት አጋርተዋል።

ስድስቱ የ2025 የዛይድ ሽልማት ለሰብአዊ ወንድማማችነት የዳኞች ኮሚቴ አባላት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ሳምንታዊውን ጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ከተከታተሉ በኋላ በቅድስት መንበር የኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ከጋዜጠኞች ጋር ቆይታ አድርገዋል።

የዛይድ ሽልማት ለሰብአዊ ወንድማማችነት ዋና ጸሃፊ የሆኑት ዳኛ መሀመድ አብደልሰላም እንደገለጹት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በጎረጎሳዊያኑ በ2019 ከአል-አዝሀር ታላቁ ኢማም ሼክ አህመድ መሐመድ አል ጣይብ ጋር ከተፈራረሙት የሰብአዊ ወንድማማችነት ሰነድ ጋር በተገናኙ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ ቡድኖች በዚህ ጳጳሳዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ላይ ሲገኙ ይህ ለ20ኛ ጊዜ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ጋር ያለው እያንዳንዱ ግንኙነት የሰው ልጅን የወንድማማችነት እሴቶች ለማሳደግ በሚያደርጉት ጥረት በግል ከፍተኛ ብርታት እንደሚሰጣቸው የተናገሩት ዳኛ አብደልሰላም፥ አክለውም “በዚህ መንገድ ለመቀጠል ያለን ፍላጎት ሁልጊዜ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጋር ስንገናኝ ይታደሳል” ብለዋል።

የጳጳሳዊ የሳይንስ እና የማህበራዊ ሳይንስ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ዋና ሃላፊ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፒተር ቱርክሰን በበኩላቸው ስለ ቡድኑ ድርሻ ሲገልጹ፥ የዳኞች ኮሚቴ ተግባር የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን የተስፋ እና የወንድማማችነት መልዕክትን የሰው ልጅ ሰላምን በተለየ መንገድ በራሳቸው ሕይወት ለሚገልጹት ወደ 100 ለሚጠጉ የዛይድ ሽልማት እጩዎች አመለካከት ውስጥ ማስረጽ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ካርዲናል ቱክሰን አክለውም የተስፋ ኢዮቤልዩን ስንጀምር በዙሪያችን ባለው ድቅድቅ ጨለማ እና ጎጂ ባህሎች እንዳንጠመድ መዘንጋት የለብንም ያሉ ሲሆን፥ እጩዎቹ የወንድማማችነት መልዕክትን በራሳቸው መንገድ ለማዳበር የሚጥሩ “የተስፋ ሐዋርያት” ተብለው ሊጠሩ ይችላሉ ብለዋል።

‘ኮመንዌልዝ ኦፍ ኔሽን’ የተባለ ተቋም ዋና ፀሃፊ እና ሌላዋ የኮሚቴው አባል ፓትሪሺያ ስኮትላንድ እንዳሉት የዛይድ ሽልማት ለሰብአዊ ወንድማማችነት ዓለም የሰውን መንፈስ ከፍ ለማድረግ በሚጥሩ ሰዎች ላይ እንዲያተኩር ያስችለዋል ብለዋል።

አክለውም ‘ሽልማቱ ሰላም ተስፋ ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ ነባራዊ እውነታ መሆኑን እና ሰዎች ይህን ለማሳካት እየሰሩ መሆናቸውን ሁሉም ሰው እንዲገነዘብ ይረዳል’ ሲሉም ተናግረዋል።

የሴኔጋል የቀድሞ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል በበኩላቸው ዓለማችን በራስ ወዳድነት፣ በጠብ እና በግጭት የተሞላች መሆኗን በመጥቀስ፥ ይልቁንም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ “ተስፋ እና ጥበብ” የሚል መልዕክት በማቅረብ፥ ሌሎች ሰዎች ምድራችን ሰላም የሰፈነባት ዓለም እንድትሆን ጠንክረው እንዲሰሩ ያበረታታሉ ብለዋል።

የቀድሞው ፕረዚዳንት አክለውም በዛይድ ሽልማት በኩል ዓለም የሰው ልጅን ወደ ሞላው መልካምነት ለማድረስ ሃይማኖቶችን እና ጎሳዎችን ያማከለ የወንድማማችነት መልዕክት ተሰጥቶታል ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶች የአብዛኛው ወላጆች አቅልለው ስለሚመለከቱት በጭንቀት የተሞላ ዓለም እንደሚያጋጥሟቸው አብዛኛው የዳኞች ኮሚቴ አባላት መገንዘባቸውን ገልጸዋል።

ዶክተር ኦኮንጆ-ኢዌላ ለጦር መሳሪያ ምርት እና ግዢ ለቁጥር የሚታክት ገንዘብ እየወጣ በሚገኝበት ዓለም፥ 300 ሚሊየኑ ከአፍሪካ አህጉር የሆኑበት 700 ሚሊዮን ሰዎች በረሃብ አረንቋ ውስጥ እንደሚገኙ በቁጭት ገልጸዋል።

የስፔን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆሴ ሉዊስ በበኩላቸው በእሳቸው እድሜ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ ከፍተኛ ግጭቶችን እና ግልጽ ጦርነቶችን ማየታቸውን በማስታወስ፥ “ለዓለማችን አዲስ ስልት እና እይታ እንፈልጋለን” ካሉ በኋላ፥ “በአሁኑ ወቅት ስለ ሰላም ብለን አንድ ላይ መሰባሰብ በጣም ያስፈልገናል” ብለዋል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አክለውም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለዓለም “ጠንካራ” የሆነ የተስፋ፣ የሰላም፣ እንዲሁም ለድሆች እና በግጭት ምክንያት ለሚሰቃዩ ሰዎች እንክብካቤ እንድንሰጥ መልዕክት ማስተላለፋቸውን በማስታወስ፥ “እኛ የአንድ ቤተሰብ አባላት ነን፥ ሁሉም ሃይማኖቶች፣ ሁሉም አስተሳሰቦች፣ ሁሉም አገሮች አንድ ሰብአዊ ቤተሰብ ናቸው” ብለዋል።

ብጹእ ካርዲናል ቱርክሰን የወንድማማችነትን ትርጉም ሲያስረዱ ቃሉ ‘አዴልፎስ’ ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም “ከተመሳሳይ ማህፀን የወጣ” ማለት ነው ብለዋል።

የጋና ተወላጅ የሆኑት ካርዲናሉ “ከአንድ ማህፀን የመጡ ሰዎች የተለያየ ክብር ሊኖራቸው አይችልም” ካሉ በኋላ፣ ሁላችንም ያንን ክብር የምንጋራ እንደሆነ እና የግንኙነታችንን ፍላጎቶች ማክበር እንዳለብን በማስታወስ፥ የሰው ልጅ ወንድማማችነት ለግንኙነታችን ወሳኝ የሆነ መሰረት ይጥላል ብለዋል።

ብጹእ ካርዲናል ቱርክሰን በመጨረሻም የዛይድ ሽልማት ለሰው ልጅ ወንድማማችነት ሁሉም ሰው ዓለምን የተሻለች ቦታ ላይ ሆና ማየት እንደሚፈልግ የሚያስታውስ መሆኑን ጠቁመው፥ “ማንኛውም ሰው የሰላም ዋና ተዋናይ ሊሆን ይችላል” ሲሉ አሳስበዋል።
 

16 December 2024, 12:51