ፈልግ

በሰሜን ጋዛ ሰሜናዊ ክፍል በሚገኘው ቤት ላሂያ ከተማ በሚገኘው ካማል አድዋን ሆስፒታል ውስጥ በአምቡላንስ ላይ የደረሰውን ጉዳት የሚያሳይ ምስል ያሳያል በሰሜን ጋዛ ሰሜናዊ ክፍል በሚገኘው ቤት ላሂያ ከተማ በሚገኘው ካማል አድዋን ሆስፒታል ውስጥ በአምቡላንስ ላይ የደረሰውን ጉዳት የሚያሳይ ምስል ያሳያል  (AFP or licensors)

ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል የጋዛ የጤና አጠባበቅ ስርዓት እየፈራረሰ በመምጣቱ ያሳስበኛል አለ

በሰሜናዊ የጋዛ ሰርጥ የጤና አጠባበቅ ስርዓት ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ በመውደሙ ህብረተሰቡ ለከፋ አደጋ እየተጋለጠ መሆኑን ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ አስጠንቅቋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በሰሜናዊ የጋዛ ሰርጥ የጤና አጠባበቅ ስርዓት በመውደሙ በአከባቢው የሚገኙ ሲቪሎች ለከፋ አደጋ እየተጋለጡ መሆኑን ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ አስጠንቅቋል።

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ (ICRC) በሆስፒታሎች እና በአካባቢው የሚደረጉ ተደጋጋሚ ግጭቶች በሰሜናዊ ጋዛ ያለውን የጤና አጠባበቅ ስርዓቶችን በማፍረሱ በአከባቢው የሚገኙ ሲቪሎች የህይወት አድን እንክብካቤ እንዳያገኙ እያደረገ በመምጣቱ ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ገልጿል።

ከዚህም ባሻገር የቀይ መስቀል ኮሚቴው በዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ህግ መሰረት ለህክምና ተቋማት ክብር እና ጥበቃ እንዲደረግ አሳስቧል።

ባለፈው ማክሰኞ ዕለት 45 ሰዎች በደቡባዊ ካን ዮኒስ ከተማ የሚገኘውን የአውሮፓዊያን ሆስፒታል ለቀው በኬረም ሻሎም ድንበር በኩል ወደ እስራኤል የተጓዙ ሲሆን፥ በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ህክምና እንደሚደረግላቸው ዘገባዎች ጠቁመዋል።

ህሙማኑ ሆስፒታሉን ለቀው ለመውጣት የተገደዱበት ዋናው ምክንያት የእስራኤል ጦር በጋዛ እያደረገ ያለውን ወረራ እና ጥቃት አጠናክሮ በመቀጠሉ ሲሆን፥ ህሙማኑ ለቀው ሲወጡ ከ100 በላይ በሚሆኑ ዘመዶቻቸው ታጅበው እንደነበር ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የእስራኤል ጦር ባለፈው ሳምንት ሐማስ ማዘዣ ማዕከል አድርጎ እየተጠቀመበት ነው በሚል ምክንያት የካማል አድዋን ሆስፒታል ላይ ያነጣጠረ ዘመቻ ማድረጉ ይታወሳል።

የጋዛ ጤና ባለሥልጣናት እንደገለጹት በጋዛ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን የውጭ አገር የሕክምና እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።

እስራኤል ግንቦት ወር ላይ ደቡባዊውን የራፋህ ከተማን ከያዘች በኋላ ወደ ጋዛ የሚወስዱ መግቢያ እና መውጫ መንገዶችን በሙሉ ተቆጣጥራለች።

በሌላ ዜና የእስራኤል ጦር የአየር ሃይሉ የመን ውስጥ በሚገኙ የሁቲ አማፂያን የተተኮሰበትን ሚሳኤል ማክሸፉን የገለጸ ሲሆን፥ ከየመን የተተኮሰው ሮኬት የእስራኤል ግዛት ከመድረሱ በፊት በአየር ሃይሉ ተመትቶ እንደተጣለ የወታደራዊ ጦሩ ቃል አቀባይ ተናግረዋል። ይሄንን ተከትሎም የእስራኤሉ የማገን ዴቪድ አዶም የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት ክፍል ምንም ዓይነት ሞት እና የአካል ጉዳት ሪፖርት እንዳልደረሰው ተናግሯል።

በሌሎች ክልላዊ ጉዳዮች ቱርክ ኤስ.ዲ.ኤፍ. ተብሎ ከሚታወቀው እና በአሜሪካ ከሚደገፈው የኩርድ ጦር ጋር በሰሜን ሶሪያ ማንቢጅ ግዛት ዙሪያ የሚተገበር የተኩስ አቁም ስምምነት እየተካሄደ መሆኑን የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።

አማፂ ቡድኖች ወደ ደማስቆ ዘምተው የሶሪያን የበሽር አል አሳድ መንግስት ከስልጣን ካስወገዱ በኋላ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ አሜሪካውያን ለመጀመሪያ ጊዜ በታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ አስችለዋል።
 

01 January 2025, 11:39