ፈልግ

በእስራኤል ላይ የሁለትዮሽ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንዲጣል በለንደን የተደረገ ሰላማዊ ሰልፍ በእስራኤል ላይ የሁለትዮሽ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንዲጣል በለንደን የተደረገ ሰላማዊ ሰልፍ  (AFP or licensors)

የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለእስራኤል የጦር መሳሪያ መሸጥ እገዳ ሀማስን ይጠቅማል አሉ

የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዳሉት ለንደን ለእስራኤል የምታደርገውን የጦር መሳሪያ ሽያጭ ማቆም ሃማስን ይበልጥ ያጠናክራል ብለዋል።

 አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሎርድ ዴቪድ ካሜሮን ዩናይትድ ኪንግደም በጋዛ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ለእስራኤል የምታቀርበውን የጦር መሳሪያ መገደብ ሃማስን ከማጠናከር ውጭ ምንም ፋይዳ ዬለውም ብለዋል።

እስራኤል በጋዛ እየፈጸመችው ባለው ጥፋት ምክንያት ዘመናዊ መሳሪያዎችን በሽያጭ እና በድጋፍ ሲያስታጥቋት የነበሩት ምዕራባውያን አገራት የሚያቅርቡላትን ጦር መሳሪያ እንዲያቆሙ ጥሪ ሲቀርብላቸው እንደነበር ይታወሳል።

ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ለእስራኤል የምታደርገው ወታደራዊ ድጋፍ “በአነጻራዊነት አነስተኛ” እንደሆነ ቢነገርም፥ እንደ ዩኬ መንግሥት አሃዝ ከሆነ እ.አ.አ. 2022 ላይ ለእስራኤል በሽያጭ የተላለፈው ጦር መሳሪያ መጠን 42 ሚሊዮን ፓውንድ ግምት አለው።

ዩኬ እ.አ.አ. ከ2008 ጀምሮ ጦር መሳሪያዎችን ለእስራኤል ለመሸጥ የንግድ ስምምነት ከአገሪቱ ጋር ተፈራርማለች። በዚህ ስምምነት እስራኤል አሜሪካ ሰራሽ ለሆኑ የጦር አውሮፕላኖች መለዋወጫዎችን ከዩኬ በሽያጭ ማግኘት ያስችላታል።

የዩኬ መንግሥት ይህን ስምምነት ተግባራዊ ማድረግ እንዲያቆም ከፍተኛ ጫና ሲደረግበት እንደነበረ የሚታወቅ ሲሆን፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ስምምነቱ ተግባራዊ ሆኖ እንዲቀጥል እስራኤል ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ሕጎችን እንድታከብር በአጽንዖት ሲጠይቁ ነበር።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ለብሪታኒያው ቢቢሲ እንደተናገሩት እገዳው የእስራኤል ታጋቾችን ለማስለቀቅ በሚደረገው ድርድር ላይ አሉታዊ ሚና እንዳለው እና ሃማስን እንደሚያጠናክረው በመግለጽ፥ ‘በእገዳው ምክንያት ዛሬ የጦር መሳሪያ ወደ ውጭ በመላክ ላይ ያለንን አካሄድ እንደምንቀይር እናሳውቃለን’ ብለዋል።

እስራኤል የጦር መሳሪዎችን ወደ ውጭ በመላክ ከቀዳሚ አገራት ተርታ ብትሰለፍም የአገሪቱ ጦር የተዋጊ አውሮፕላኖችን፣ ቦምቦችን እና የሚሳኤሎች ፍላጎቱን የሚያሟላው ከሌሎች አገራት በከፍተኛ መጠን በማስገባት ነው።

በጋዛ ላይ እየተካሄደ ያለው ድብደባ

ይህ በእንዲህ እንዳለ እስራኤል እሁድ ጧት በጋዛ ሰርጥ ላይ ተጨማሪ የአየር ጥቃቶችን እንዳደረሰች እና በጥቃቱም ሁለት ዶክተሮች መገደላቸውን አንዳንድ ዘገባዎች እያሳዩ ይገኛል።

የእስራኤል ጦር በሰሜን ጋዛ ያሉ አሸባሪዎችን 'አስወግጃለሁ' ካለ በኋላ፥ ፍልስጤማውያን ከደቡብ ለቀው እንዲወጡ ከእስራኤል ጦር የተላለፈውን ትእዛዝ ተከትሎ ቢያንስ 100,000 ፍልስጤማዊያን ወደሰሜን አካባቢ መጓዝ አለባቸው ብሏል።

 እንደ እስራኤል ጦር ገለፃ ከሆነ ራፋህ ውስጥ የነበሩ ወደ 300,000 የሚጠጉ ሰዎች የቀረበላቸውን ትዕዛዝ በመቀበል ከተማዋን ለቀው ወደ ‘ሰብዓዊ ቀጠና’ መጓዛቸውን ገልጿል። ይህንንም በማስመልከት ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ በርካታ ሰዎች 'አል-ማዋሲ ከተማ ወደሚገኘው የሰብአዊነት ቀጠና እየሄዱ ነው' ሲል የእስራኤል ጦር ቅዳሜ ዕለት ገልጿል።

ባለፈው ወር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ለእስራኤል የሚደረግ የጦር መሳሪያ አቅርቦት እንዲቆም በ28 ድጋፍ፣ በ6 ተቃውሞ እና በ13 ድምጸ ታዕቅቦ ውሳኔ ማሳለፉ የሚታወስ ሲሆን፥ ለእስራኤል ጦር መሳሪያ በማቅረብ ትልቁን ድርሻ የሚይዙት አሜሪካ እና ጀርመን ግን ይህን የመንግሥታቱ ድርጅትን የውሳኔ ሃሳብ ተቃውመውት ነበር።

መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ሃማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት በማድረስ በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን ከገደለ እና 250 ሰዎችን አግቶ ከወሰደ በኋላ እስራኤል በጋዛ ውስጥ የምታካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ቀጥሎ ጋዛ ውስጥ ብቻ ከ30 ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል። 128 ታጋቾች አሁንም በሃማስ እና በሌሎች ታጣቂ የፍልስጤም ቡድኖች ታግተው እንደሚገኙ ዘገባዎች ያሳያሉ።
 

13 May 2024, 15:13