ፈልግ

የሰኔ 18/2015 ዓ.ም ዘአስተምህሮ እለተ ሰንበት ቃለ እግዚአብሔር የሰኔ 18/2015 ዓ.ም ዘአስተምህሮ እለተ ሰንበት ቃለ እግዚአብሔር  (ANSA)

የሰኔ 18/2015 ዓ.ም ዘአስተምህሮ እለተ ሰንበት ቃለ እግዚአብሔር

የእለቱ ምንባባት

1.      ሮሜ 5፡12-21

2.    3ኛው ዮሐንስ 1፡1-15

3.    የሐዋርያት ሥራ 16፡1-13

4.    ማቴዎስ 22፡1-22

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ሰርግ ድግስ ላይ የተጠሩ ሰዎች ምሳሌ

ኢየሱስም እንደ ገና እንዲህ የሚል ምሳሌ ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ ለልጁ ሰርግ የደገሰ ንጉሥ ትመስላለች፤ ንጉሡም የተጋበዙትን ሰዎች እንዲጠሩ አገልጋዮቹን ላከ፤ እነርሱ ግን አንመጣም አሉ። “እንደ ገናም ሌሎች አገልጋዮች ልኮ፣ ‘የተጋበዙትን፣ እነሆ፣ በሬዎችንና የሠቡ ከብቶቼን አርጄ ድግሱን አዘጋጅቻለሁ፤ ሁሉም ነገር ዝግጁ ስለ ሆነ ወደ ሰርጉ ኑ በሏቸው’ አለ። “ተጋባዦቹ ግን ጥሪውን ችላ ብለው፣ አንዱ ወደ ዕርሻው ሌላው ወደ ንግዱ ሄደ፤ የቀሩትም አገልጋዮቹን በመያዝ አጉላልተው ገደሏቸው። ንጉሡም በመቈጣት ሠራዊቱን ልኮ ገዳዮቻቸውን አጠፋ፤ ከተማቸውንም አቃጠለ። “ከዚያም አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፤ ‘የሰርጉ ድግስ ዝግጁ ነው፤ ነገር ግን የተጋበዙት የሚገባቸው ሆነው ስላልተገኙ፣ ወደ መንገድ መተላለፊያ ወጥታችሁ ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሰርጉ ድግስ ጥሩ።’ አገልጋዮቹም ወደ መንገድ ወጥተው ያገኙትን መልካሙንም ክፉውንም ሁሉ ሰብስበው የሰርጉን አዳራሽ በእንግዶች ሞሉት።

“ንጉሡም የተጋበዙትን እንግዶች ለማየት ሲገባ፣ አንድ የሰርግ ልብስ ያልለበሰ ሰው አየ፤ እንዲህም አለው፤ ‘ወዳጄ ሆይ፤ የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት እዚህ ልትገባ ቻልህ?’ ሰውየው ግን የሚመልሰው ቃል አልነበረውም። “ንጉሡም አገልጋዮቹን፣ ‘እጅና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል’ አላቸው፤ የተጠሩት ብዙዎች፣ የተመረጡት ግን ጥቂቶች ናቸውና።”

ግብር ስለ መክፈል

ከዚህ በኋላ ፈሪሳውያን ወጥተው በመሄድ በአፍ እላፊ እንዴት እንደሚያጠምዱት ተማከሩ። ደቀ መዛሙርታቸውን ከሄሮድስ ወገኖች ጋር ወደ እርሱ ልከው እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ እውነተኛና የእግዚአብሔርንም መንገድ በእውነት የምታስተምር እንደሆንህ፣ ለማንም ሳታዳላ ሁሉን በእኩልነት እንደምትመለከት እናውቃለን፤ ንገረን፤ ምን ይመስልሃል? ለመሆኑ ለቄሣር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?”

ኢየሱስ ግን ተንኰላቸውን በመረዳት እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ግብዞች ለምን በነገር ልታጠምዱኝ ትሻላችሁ? ለግብር የሚከፈለውን ገንዘብ እስቲ አሳዩኝ።” እነርሱም አንድ ዲናር አመጡለት። እርሱም፣ “በዚህ ገንዘብ ላይ የሚታየው መልክ የማን ነው? ጽሕፈቱስ የማን ነው?” አላቸው። እነርሱም፣ “የቄሣር ነው” አሉት። እርሱም መልሶ፣ “እንግዲያውስ የቄሣርን ለቄሣር፣ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው። ይህን ሲሰሙ ተደነቁ፤ ትተውትም ሄዱ። 

የእለቱ አስተንትኖ

በክርስቶስ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

ከሁሉም በማስቀደም መግባታችንን እና መውጣታችንን በጸጋው እየባረከ በሰላም እና በጤና እንድንጓዝ የሚያደርገንን እግዚአብሔር አባታችን ቅዱስ ስሙ የተባረከ ይሁን።

ምሕረቱን እየሰጠን እኛም እርስ በእርሳችን ምሕረት አድራጊዎች እንድንሆን የሚመክረን ልጁ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተመሰገነ ይሁን፣ በሐዘናችን፣ ተስፋ በምንቆርጥባቸው ጊዜያት ሁሉ ከእኛ ጋር በመሆን የምያጽናናን መንፈስ ቅዱስ ምስጋና ለእርሱ ይሁን።

የዛሬው ሰንበት የእግዚአብሔር ቃል በቅዳሚነት የተወሰደው ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ሮም ሰዎች ከጻፈው መልዕክቱ ከምዕራፍ 5:12-22 ላይ የተወሰደ ሲሆን “ሞት በአዳም ሕይወት ደግሞ በክርስቶስ እንደተሰጠን” የሚገልጸው ነው። በሁለተኛነትም ከሐዋርያት ሥራ 16:1-13 ላይ የተወሰደው “ጢሞቴዎስ ከሐዋርያው ጳዎሎስና ከሲላስ ጋር ለሐዋሪያዊ ተግባር መሰማራቱን” የሚገልጽ ነው። የእለቱ ቅዱስ ወንጌል የተወሰደው ከማቴዎስ ወንጌል 22:1-22 ላይ የተጠቀሰው “በሰርግ ድግስ ላይ የተጠሩ ሰዎች ምሳሌን የሚገልጸው እና የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርን ደግሞ ለእግዚአብሔር መስጠት ይገባል” የሚለው የኢየሱስ ቃል የሚገኝበት ነው።

በሀገራችንም ይሁን በተለያዩ የዓለማችን ሀገራት ውስጥ የሰርግ ግብዣ በሚዘጋጅበት ወቅት ሁሉ እንደየ ባሕሉ እና እንደየወጉ፣ እንደየ አቅማችን የሰርግ ልብስ በመልበስ፣ አምረን እና ደምቀን፣ የሙሽራውን እና የሙሽሪቷን በዓል ለማድመቅ የታችላንን ሁሉ በማድረግ ወደ ሰርጉ ግብዣ መሄድ የተለመደ ነው። በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሱት የሰርግ እንድምተኞች በአብዛኞቹ ተገቢ የሆነ የሰርግ ልብስ የለበሱ ሲሆን ነገር ግን አንድአንዶቹ በተለይም ከጎዳና ላይ የተጠሩ ሰዎች በቂ የሆነ ዝግጅት ሳያደርጉ በስርጉ ግብዣ ላይ መገኘታቸው ተጠቅሱዋል። በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰው እና ተገቢ የሆነ የሰርግ ልብስ ያለበሰው ሰው የተዘጋጀለትን የስረግ ልብ አለመልበሱ የጋባዡን ክብር የሚነካ ጉዳይ ነው። የሰርግ ልብስ የልብን መዘጋጀት ያመለክታል። ይሄው በክርስቶስ ማመን እና ከእርሱም ጸጋ የተነሳ ዘወትር ታዛዥ ሆኖ መገኘትን ያሳያል። ሁላችን ራሳችንን እንድንመረምር ክርስቶስ የሰርግ ልብስ ያለበሰውን ሰው ምሳሌ ተጠቅሞ ለእኛ ሲናገር ይደመጣል።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ በዛሬው ቀን ኢየሱስ ለእኔና ለእናንተ ያዘጋጀ ያላው መልእክት ይህ ነው። ጥልቅ የሆነ የልብ ዝግጅት እንድናደርግ፣ ሁል ጊዜም ቢሆን በእግዚአብሔር ጸጋ እና ክብር የተሞላ ሕይወት እንዲኖርን፣ ከክፉ ነገሮች ሁሉ እንድንርቅ፣ ኅጢአታችንን በንስሐ እንድናጥብ እና ለኢየሱስ ክብር የተዘጋጀ ሕይወት ይኖረን ዘንድ ጌታ ጥሪ ያደርግልናል።

ሁልጊዜም ቢሆን ቸልተኝነት የሚታየው እና የሚመጣው ከእኛው ከሰዎች በኩል ነው እንጂ እግዚአብሔር ሁሌም መሐሪ እና ይቅር ባይ ቁጣው የዘጌየ በምሕረት የተሞላ ነው። ርሰዕ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በአንድ ወቅት የእግዚአብሔርን ማሐሪነት እና የእኛን ግድየለሽነት በተመለከተ እንዲህ ብለው ነበር “እኛ ነን እንጂ እግዚአብሔርን ማረኝ ብለን መጠየቅ የምንሰለቸው፣ እግዚአብሔር ግን በፍጹም ምሕረትን ለእኛ ከማድረግ ሰልችቶ አያውቅም” ማለታቸው ይታወሳል። የእግዚአብሔር ልብ የምሕረት ልብ ነው፣ እግዚአብሔር የጸጋ እና የበረከት አምላክ ነው፣ ሁል ጊዜ መዘጋጀት እና የእርሱን ክብር ተላብሰን መኖር ያስፈልገናል። በኦሪት ዘፍጥረት ውስጥ የተጠቀሰው የአዳም እና የሔያዋን ታሪክ ይሄኑ የሚያጠናክር ነው። አታድርጉ የተባሉትን ባደርጉ ጊዜ የእግዚአብሔር ክብር ራቃቸው፣ እግዚአብሔርን ሸሹ. . .

እግዚአብሔር ከእኛ የሚጠብቀውን መንፈሳዊ ዝግጅት በማድረግ ልባችንን ከኃጢአት የማናነጻ ከሆነ እግዚአብሔር ብዙ ይታገሰናል ነገር ግን በሰርጉ ግብዣ ምሳሌ ላይ እንደ ተጠቀሰው በቂ ዝግጅት የማናደርግ ከሆነ ራሳችን በሰራነው ኃጢአት ተጠላልፈን የምንወደቀ ራሳችን ነን ““ንጉሡም አገልጋዮቹን፣ ‘እጅና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጥታችሁ ጣሉት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል’ አላቸው፤ የተጠሩት ብዙዎች፣ የተመረጡት ግን ጥቂቶች ናቸውና” (ማቴዎስ 22:13)። ይህ ቃል የሚያስረዳን በኃጢአታችን ተጸጽተን ንስሐ የማንገባ ከሆነ፣ ለእግዚአብሔር የተገባ ሕይወት ይማንኖር ከሆነ የሚጠብቀንን ከባድ የሆነ ቅጣት የሚያሳይ ነው።

በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ በቀጣይነት የምናገኘው ፍሬ ሐስብ “የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር” የሚለው ቃል ነው። ፍሪሳዊያን የሮማዊያንን አገዛዝ በብርቱ የሚቃወሙ ጠንካራ ብሔርተኞች ነበሩ፣ በአንጻሩም የሂሮድስ ወገኖች የተባሉትና ጥላቻ ያተረፉት የሂሮድስን ሮማዊ አገዛዝ ይደግፉ ነበር። በዚህ ጊዜ ግን ፈሪሳዊያን ኢየሱስን በሚናገረው ቃል ጠልፈው ለመያዝ የሂሮድስ ወገኖችን እርዳታ ስላስፈለጋቸው በሽንገላቸው ወደ ወጥመዳቸው እንዲገባ ካመቻቹ ቡኃላ “ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?” በማለት ድንገተኝ የሆነ ጥያቄ ሰነዘሩለት። “መክፈል አይገባም” ብሎ ቢመልስ ኖሮ የሂሮድስ ወገኖች በሮማዊያን እንደራሴዎች ፊት ለፊት ከሰውት በመንግሥት ተቃዋሚነት የሞት ፍርድ ባስበየኑበት ነበር፣ መክፈል ይገባል ብሎ ቢመልስ ደግሞ ለገዛ ወገኖቹ ታማኝ እንዳልሆነ በመቁጠር በሕዙቡ ዘንድ ልያጥላሉት ምክንያት ፈልገው ነበር።

ነገር ግን የሰውን ልብና ኩላሊት ሳይቀር መርምሮ የሚያውቀው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ተንኮላቸውን፣ ወጠዳቸውን ጠንቅቆ በአምላክነት ኃይሉ ስለተረዳ በሳንቲሙ ላይ ያለው ምስል “የቄሳር በመሆኑ የተነሳ የቄሳርን ለቀሳር የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር መስጠት ይገባል” በማለት ይመልስላቸዋል።

የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር መስጠት ይገባል የሚለው ቃል እኛ ዛሬ ሁላችን በሕይወታችን ልንተገብረው የሚገባን ትሕዛዝ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔርን ለእግዚብሔር ብሎ መናገሩ የሚያሳየው በቄሳር እና በእግዚአብሔር መካከል ከፍተኛ የሆነ ልዩነት እንዳለ እና ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል ሁሉ የእግዚአብሔር ሐሳብ ከእኛ ሐሳብ የተለየ መሆኑን ለማመልከት ነው።

ከዚህ የኢየሱስ ቃል ዛሬ እኛ ምን እንረዳለን? በሕይወታችን ስንት ጊዜ ነው የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር የዓለምን ለዓለም ሰጥተን የምናወቀ ስንት ጊዜ ነው? ስንት ጊዜ ነው የዓለምን ነገሮች እና የእግዚአብሔርን ነገር መለየት አቅቶን ስንዘበዝብ የምንገኘው?

በአሁኑ ወቅት በዓለማችን እየታየ የሚገኘው ትላቁ ፈተና ይሄው ጉዳይ ነው፣ የዓለምን እና የእግዚአብሔርን ነገሮች በጣም አቀላቅለናቸው፣ እግዚአብሔርን በማይገባው ስፍራ አስቀምጥነው። ዛሬ እኔ እና እናንተ ሕይወታችንን በመፈተሽ የተኛው የቄሳር የተኛው ነገር ደግሞ የእግዚአብሔር መሆኑን መረዳት ያስፈልገናል።

ኢየሱስ የቀሳርን ለቄሳር ብሎ መመለሱ አዎንታዊ የሆነ እድምታ አለው። ይህም እኛ ክርስቲያኖች በዚህ ምድር በምንኖርበት ወቅት ሁሉ ለማሕበራዊ ዋትና የበኩላችንን አስተዋጾ ማድረግ አስፈላጊ እንደ ሆነ፣ ክርስቲያን እንደ መሆናችን መጠን ክርስቲያናዊ እሴቶችን የተላበሱ አስተዋጾ ለማኅብረሰቡ እና ለሀገር ማበርከት እንደ ሚገባ፣ ሰላም እና ፍትህ ይሰፍን ዘንድ የየበኩላችንን ማድረግ እንድሚኖርብን፣ ለሌሎች የተገባውን ነገር ለራሳችን ጥቅም ማዋል እንደ ሌለብን፣ የሚያሳስብ ትልቅ መልእክት ያዘለ አነጋገር ነው። በአንጻሩም የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር መስጠትም ተገቢ እንደ ሆነ ኢየሱስ ይናገራል። በእነዚህ ሁለት ሀረጎች መካከል ያለው ግንኙነት የሚያሳየው ኢየሱስ ለወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የሚገባቸውን መስጠት እንዳለብን የሰዎችን ሀቅ መንካት እንደ ሌለብን የሚያሳይ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በተመሳስይ መልኩ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ማጠናከር እንዳለብን ይገልጻል። እዚህ ጋር ባልነጀራህን  እንደ ራስህ አድርገህ ወደድ እግዚአብሔር አባትህንም በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነብስህ፣ በፍጹም ኃይልህ ውደድ የሚለውን ያሰማል። ባልንጀሮቻንን የምንወደ ከሆነ የሚገባቸውን ነገሮች ሁሉ እንሰጣቸዋልን እንጂ አንነጥቃቸውም፣ እግዚአብሔርን የምንወደ ከሆነ ደግሞ እርሱን በሕይወታችን እናከብረዋለን ማለት ነው።

በመንፈሳዊ ሕይወታችን እየጠነከርን እንድንሄድ፣ የእግዚአብብሄርን ለእግዚአብሔር የቄሳርን ለቄሳር መስጠት የምንችልበትን ጸጋ ከልጇ ዘንድ እንድታሰጠን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን አማላጅነት ልንማጸን ይገባል።

ምንጭ የቫቲካን ሬዲዮ የአማርኛው አገልግሎት 

24 June 2023, 16:24