ፈልግ

የኒካራጓ ዜጎች የሊቀ ጳጳስ አልቫሬዝን መታሰር በመቃወም ሠላማዊ ሰልፍ ሲያደርጉ የኒካራጓ ዜጎች የሊቀ ጳጳስ አልቫሬዝን መታሰር በመቃወም ሠላማዊ ሰልፍ ሲያደርጉ   (AFP or licensors)

ከ 3 አገሮች ውስጥ በአንዱ የሃይማኖት ነፃነት ጥሰቶች ይፈፀማሉ ተባለ

ዕርዳታ የሚያስፈልጓቸውን ቤተክርስቲያናት የሚረዳው የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅት ከ4.9 ቢሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች የሃይማኖት ነፃነት በማይከበሩባቸው አገሮች ውስጥ እንደሚኖሩ ዘንድሮ ባወጣው 16ኛ ሪፖርቱ ያለውን እውነታ አቅርቧል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

 ይህ የካቶሊክ የዕርዳታ ድርጅት (Aid to the Church in Need) የዘንድሮውን (የ2023) ዓመት ሪፖርት ባለፈው ሰኔ 15, 2015 ዓ.ም. ሐሙስ ዕለት ሮም ውስጥ ባወጡት ዘገባቸው ፥ በዚህ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ቀውስ ምክክር እየተደረገ ባለበት አውድ ውስጥ የሽብር ጥቃቶች ፣ ፀረ ለውጥ ሕጎች ፣ የገንዘብ ቀውሶች ፣ የምርጫ ማጭበርበሮች እና ግጭቶች እየጨመሩ መምጣታቸውን አቅርበዋል።
የካቶሊክ የእርዳታ ድርጅቱ ዓመታዊ ዘገባው ከ4.9 ቢሊዮን በላይ ሰዎች (ይህም ከሦስቱ አገሮች አንዱ) ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ የመጣው የሃይማኖት ነፃነት ጥሰት እየተፈፀመባቸው መሆኑን አመልክቶ ፥ በእምነታቸው ምክንያት በተወሰደባቸው ጥቃት ከተጠቁ 196 አገሮች መካከል 61ቱን ጠቅሶ አውጥቷል።

ሶስት ምድቦች

በዝርዝሩ አናት ላይ የተቀመጡት ሃይማኖታዊ ጥቃት የደረሰባቸው እና በ ‘ቀይ’ ምድብ ውስጥ የተመደቡ ሃገሮች ናቸው። እንደ ዘገባው ከሆነ በዚህ ምድብ ከተመደቡት 28 ሃገራት ውስጥ 13ቱ በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ሁኔታው እጅግ የተባባሰባቸው ሃገራት እንደሆኑ አመላክቷል።
33 ሃገራት የተካተቱበት እና በ “ብርቱካናማ” ምድብ ውስጥ የተዘረዘሩት ሀገራት ፥ በአብዛኛው አናሳ ሀይማኖቶች ላይ የሚደርሰውን መድልዎ አስመልክቶ የቀረቡ ሲሆን ከባለፈው ዓመት ሪፖርት አኳያ ጉልህ የሆነ የደረጃ ለውጥ ያሳዩ ሃገራት ናቸው።
ሦስተኛው እና የመጨረሻው ምድብ “በክትትል ውስጥ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን የሃይማኖት አለመቻቻል ፣ አድልዎ እና የሃይማኖት ስደት እየጨመረ ያሉባቸውን አገሮችን ያጠቃልላል።

ያለመከሰስ ሁኔታ መጨመር

ጥናቱ እንደሚያሳየው አብዛኛዎቹ የተዘገቡ ጉዳዮች እንደሚያሳዩት መንግስታት የሃይማኖት ነፃነትን የሚገድቡ ወይም የእምነት ማህበረሰቦችን የሚያገሉ አወዛጋቢ ህጎችን ያለምንም ተቃውሞ በመተግበር ላይ እንደሚገኙ ነው። በሀይማኖት ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደ ‘መደበኛ’ ድርጊት እየታየ እና በተለይም በላቲን አሜሪካ ውስጥ ጉዳዮቹ በባለስልጣናት ደረጃ የማይታዩ መሆናቸውንም ይጠቅሳል።
ዘገባው በናይጄሪያ እና ኒካራጓ ብዙ ሀይማኖተኞች የሚሰደዱበት ሃገራት መሆናቸውን ጠቅሶ ፥ በዚህ ድርጊት የተሳተፉትም ተጠያቂ የማይሆኑበት እና ያለመከሰስ ባህልም እያደገ መምጣቱን ይናገራል።
በዚህ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ቤተክርስቲያናትን የሚረዳው ይህ የካቶሊክ የዕርዳታ ተቋም እይታ ዉስጥ ከገቡ ሃገራት መሃል ጥቂቶቹ ህንድ ፣ ፓኪስታን ፣ ኢራን ፣ ምያንማር ፣ ሞዛምቢክ ፣ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ፣ ማሊ እና ቡርኪናፋሶ ናቸው።
በመጨረሻም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሙስሊሞች ላይ እየደረሰ ያለው ስደት መጨመሩን እና በአውሮፓ ደግሞ ፀረ-ሴማዊነት እየተስፋፋ መምጣቱን ዘገባው አመልክቷል።
 

26 June 2023, 11:48