ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሮም ውስጥ የሚኖር የናይጄሪያ ማኅበረሰብን በቫቲካን ተቀበሉ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሮም ውስጥ የሚኖር የናይጄሪያ ማኅበረሰብን በቫቲካን ተቀበሉ   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሮም የሚኖር የናይጄሪያ ማኅበረሰብ አንድነቱን እንዲያጎለብት አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሮም ውስጥ የሚኖር የናይጄሪያ ማኅበረሰብን በቫቲካን ተቀብለው መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው ለማኅበረሰቡ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ማኅበረሰቡ ለሚያቀርበው የወንጌል ምስክርነት ምስጋናቸውን አቅርበው፥ “በናይጄሪያ ውስጥ ያለው የብሔር፣ የባሕል እና የቋንቋ ልዩነቶች ችግርን የሚፈጥሩ ሳይሆን ለመልካም ተግባር የሚሆኑ ስጦታዎች ናቸው" በማለት አስገንዝበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰኞ መጋቢት 16/2016 ዓ. ም. ጠዋት በሮም ውስጥ የሚኖሩ ናይጄሪያዊ ማኅበረሰብን በቫቲካን ውስጥ በሚገኝ ጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ውስጥ ተቀብለዋል። ምዕመናኑ የወንጌልን መልዕክት በደስታ በመመስከራቸው እንዲሁም የእግዚአብሔርን ጥሪ ተቀብለው በጋስነት፣ በትሕትና እና በትዕግሥት መልስ በመስጠት ለክህነት አገልግሎት እና ለምንኩስና ሕይወት ራሳቸውን ላቀረቡት በርካታ ናይጄሪያውያን ወንድ እና ሴት ወጣቶች ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።  

ሮም ከተማ ውስጥ ከሚኖር የናይጄሪያ ማኅበረሰብ መካከል የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች እና ከልዩ ልዩ ገዳማት የመጡ ወጣቶች መኖራቸውን የተመለከቱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ወጣቶቹ ዘወትር የወንጌል መልዕክተኛ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ በማበረታታት፣ “እምነታችንን በቅንዓት እንድንሰብክ፣ የበለጠ ፍትሐዊ እና ሰብዓዊነት የሰፈነበት ዓለምን ለመገንባት አስተዋጽኦአችንን  እንድናበረክት ላደረገን  የእግዚአብሔር ጥሪ ምስጋናችንን እናቀርባለን” ብለዋል።

በልዩነት ውስጥ ያለው ሃብት

ናይጄሪያ ያላትን የዘር እና የባሕል ስብጥር ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ናይጄሪያ ውስጥ የሚገኘው የብሔረሰቦች፣ የባሕላዊ ወጎች እና የቋንቋዎች ልዩነቶች ችግርን የሚፈጥሩ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያንንም ሆነ የመላውን ኅብረተሰብ አንድነት የሚያበለጽግ፥ እንዲሁም የጋራ መግባባትን እና አብሮ የመኖር እሴቶችን ለማስተዋወቅ የሚያስችል ስጦታ ነው” ብለዋል።

ራስን ለሌሎች ዝግ የማድረግ አደጋ

በሮም ከተማ ውስጥ የሚኖር የናይጄሪያ ማኅበረሰብ ዘወትር ታላቅ እና ሁሉን አቀፍ ቤተሰብ ሊመስል እንደሚችል የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ አባላቱ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች የሆኑትን ልዩ ልዩ ስጦታዎቻቸውን እና ተሰጥኦዎቻቸውን ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ፥ ማኅበረሰቡ በደስታ እና በሐዘን፣ በስኬት እና በችግር ጊዜያት እርስ በርስ ሊደጋገፍ እና ሊበረታታት እንደሚችል፥ በዚህ መንገድም ማኅበራዊ እና ሰላማዊ የወዳጅነት ግንኙነትን ለአሁኑም ሆነ ለመጪው ትውልድ መዝራት ይቻላል” በማለት ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ይህን መንገድ ሊያደናቅፍ የሚችል አደጋ ሊኖር እንደሚችል ያስጠነቀቁት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አደጋው ራስን ለሌሎች ክፍት አለማድረግ እና መነጠል እንደሆነ ተናግረው፥ በተለይ የጎሳ ልዩነት ትልቅ አደጋን ሊያስከትል እንደሚችል፥ የጎሳ ልዩነትን በማስወገድ ማኅበራዊነትን ማሳደግ አስፈላጊ እንደሆነ አሳስበዋል። ይህን መንገድ መከተል ሁሉንም ሰው እንደሚጠቅም እና ተፈጻሚ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረው፥ የሚያስፈልገን ዓለማቀፋዊነት እንጂ በራስ ባሕል ብቻ ተዘግቶ መቆየት እንዳልሆነ፥ ባሕል የሚያቀራርብ ስጦታ እንጂ የሚያራርቅ ሊሆን እንደማይገባ አሳስበዋል።

ከሁሉም ጋር መደማዳመጥ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም እርስ በርስ መወያየት እንደሚገባ መክረው፥ አለመታደል ሆኖ በብዙ የዓለም ክልሎች ግጭቶች እና መከራዎች መኖራቸውን በማስታወስ ናይጄሪያም እንዲሁ በአስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ እንደምትገኝ ገልጸዋል። ለታዳሚዎቹ ባስተላለፉት መልዕክትም፥ ለናይጄሪያ ደህንነት፣ አንድነት እና መንፈሳዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጸሎት እንደሚያቀርቡ አረጋግጠውላቸዋል። የውይይት ባሕል እንዲጎለብት እና አንዱ ለሌላው ራሱን ግልጽ በማድረግ ከልብ እንዲደማመጡ፥ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ ሕይወት እና በሃይማኖት ምክንያት ማንም ላይ ልዩነት ሳይደረግበት አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ ጋብዘዋል።

የእግዚአብሔርን "ዘይቤ" መከተል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደዚሁም ናይጄሪያውያን የእግዚአብሔርን ታላቅ ምሕረት አብሳሪዎች በመሆን ለእርቅ እንዲሠሩ፣ የድሆችን እና የተቸገሩ ሰዎችን ሸክም በማቃለል፥ የእግዚአብሔርን ዘይቤ በመከተል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚችሉ አበክረው ገልጸዋል። “የእግዚአብሔር ዘይቤም እርስ በርስ መቀራረብ፣ ርኅራኄ እና ለጋስነት ነው” በማለት አስረድተዋል።

ይህን ዘይቤ እንደራሳቸው አድርገው በመያዝ “ሁሉም ናይጄሪያውያን በወንድማማችነት በመተሳሰብ እና በስምምነት መጓዝን ሊቀጥሉ ይችላሉ” ብለዋል።

26 March 2024, 15:36