የሰኔ 06/2013 ዓ.ም የዕረገት በዓል እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የሰኔ 06/2013 ዓ.ም የዕረገት በዓል እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የሰኔ 06/2013 ዓ.ም የዕረገት በዓል እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ!

የዕለቱ ንባባት

1.    ዕብ 1፡1-14

2.   1ጴጥ 3፡18-22

3.   ሐዋ 1፡1-11

4.   ማር 16፡14-20

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ከዚያም ዐሥራ አንዱ በማዕድ ላይ ሳሉ ተገለጠላቸው፤ ከተነሣ በኋላ ያዩት ሰዎች የነገሯቸውን ስላላመኗቸው፣ አለማመናቸውንና የልባቸውን ድንዳኔ ነቀፈ። እንዲህም አላቸው፤“ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ፤ ያመነ የተጠመቀ ይድናል፤ ያላመነ ግን ይፈረድበታል። የሚያምኑትን እነዚህ ምልክቶች ይከተሏቸዋል፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ልሳንም ይናገራሉ፤ እባቦችን በእጃቸው ይይዛሉ፤ የሚገድል መርዝ ቢጠጡ እንኳ አይጐዳቸውም፤ እጃቸውንም በሕመምተኞች ላይ ይጭናሉ፤ እነርሱም ይፈወሳሉ።”

ጌታ ኢየሱስ ይህን ከተናገራቸው በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ። ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ወጥተው፣ በየስፍራው ሁሉ ሰበኩ፤ ጌታም ከእነርሱ ጋር ይሠራ ነበር፤ ትምህርታቸውንም ተከትለው በሚፈጸሙ ምልክቶች ቃሉን ያጸና ነበር

ዘዕርገት

በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም መልካም ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ! ዛሬ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ስርዓት አቆጣጠር በዓለ ዕርገትን እናከብራለን በዛሬው በመጀመሪያ መልዕክት ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን በፃፈው መልዕክቱ እግዚአብሔር በአምሳሉና በመልኩ ለፈጠራቸው ሰዎች በተለያየ ዓበይትና ንዑሳን ነብያቶች ያስተምር እንደነበረና የተባለው ጊዜ በደረሰ ጊዜ ደግሞ በአንድያ ልጁ አማካኝነት እንደተናገረ ይነግረናል።

እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባን ነገር እነዚህ የብሉይ ኪዳን ዓበይትና ንዑሳን ነብያት ሁሉ ወደ ክርስቶስ የሚወስደውንና የሚመራውን መንገድ አሳዩ ፣ አመላከቱ እንጂ ስለራሳቸው አልመሰከሩም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ራሱ በሙሉ ስልጣንና ኃይል አስተማረ ስለአባቱ መሰከረ ስለዚህ ይህ ብሉይ ኪዳን በአዲስ ኪዳን ፍፃሜውን እንዳገኘ ይመሰክርልናል። ይህንንም እውነታ በ2ኛ ቆሮ 2፡20 ላይ እግዚአብሔር የሰጠው የተስፋ ቃል የሚፈጸመው የእግዚአብሔር ክብር የሚገለፀው በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ይናገራል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብ ነፀብራቅ ነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቅድስት ሥላሴ ሁለተኛ አካል ነው። ገና ዓለም ከመፈጠሩ በፊት እንኳ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ጋር ነበር ቅዱስ ሕዋርያው ጳውሎስ በ2ኛ ቆሮ 4፡4 ላይ እንዲሁም በቆላ 1፡15 ላይ ይህንን እውነታ ሲመሰክር  “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚታየው የእግዚአብሔር አብ ምሳሌና መገለጫ ነው” ይላል ስለዚህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእምነትና በመንፈሳዊ አይናችን ስንመለከተው እግዚአብሔር አብን ተመልክተነዋል ማለት ነው። በቆላ 2፡2 ላይ “የመለኮት ፍጹም ሙላት በሰውነት ተገልጦ የሚኖረው በክርስቶስ እንደሆነ” ይናገራል። 

አንድ ራሱን ክርስቲያን ነኝ ብሎ ለሚጠራ ሰው ወይም ደግሞ የሚያምን ሰው ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ውጪ ሕይወት የለውም ምክንያቱም በዓለም የሚገኝ ነገር ሁሉ ተያይዞ ጸንቶ የሚቆመው በእርሱ ነውና ቆላ 1፡17

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማይም በምድርም ከሚገኙ ፍጥረታት ሁሉ የበለጠ ነው ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር “አንተ ልጄ ነህ” “እርሱ የምወደው ልጄ ነው አላለም” ልጅ የሆነ ሁሉ ደግሞ የአባቱ የሆነ ሁሉ የመውረስ መብት አለው። ስለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ የመውረስ መብት አለው ማለት ነው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሁለት መንገድ በኩር ነው፡ አንደኛ ብቸኛ የእግዚአብሔር ልጅ በመሆኑ በኩር ነው ሁለተኛ ደግሞ በራሱ ስልጣን ከሞት በመነሣት በኩር ነው። እግዚአብሔር ለዚህ ለአንድያ ልጁ ጸጋውን በሙላት ሰጥቶታል ስለዚህ እንደ እግዚአብሔር በኩር ልጅ ማንኛውም ነገር በሥልጣኑ ለመፈጸም ተሰጥቶታል።

ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ የእግዚአብሔርን አምላክነት ፣ ዘለዓለማዊነት ሲመሰክር አንተ ግን ያው አንተ ነህ ዓመታቶችህም ከቶ አያልቁም ይላል እንግዲህ ይህ ዘለዓለማዊነት ለቅድስት ሥላሴ አካላት ሁሉ ያገለግላል። መዝ 102፡25-27  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቸኛው በአብ ቀኝ የተቀመጠ አንድያ ልጁ ነው በእግዚአብሔር አባቱ ዙፋን ላይ ተቀምጦ በኃይልና በስልጣኑ ይገዛል። ይህ ቃል እኛም በየትኛውም አቅጣጫ ብንጓዝ ይህንን የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ ካልያዝን በእርሱ ካልተደገፍን በስተቀር በየትኛውም መንገድ ብንጓዝ ውጤታማ ልንሆን አንችልም ምክንያቱም ከእርሱ ውጪ የሚንቀሳቀስና በእርሱ በረከት ያልተሞላ ሰው በጉዞው ውስጥ የሚያስፈልጉ በረከቶችና ጸጋዎች ይጎሉናልና።

በዛሬው ሁለተኛ ንባብ ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ዙፋን የተቀመጠው ብዙ የመከራን ጉዞ አድርጎ እንደሆነ ማስታወስ ያስፈልጋል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መከራን ሲቀበል መከራውን በእኛ ለማየት የሚያደርገው ነገር ቢኖር እርሱ ምንም ክፋት ሳይኖርበት ሰው ሳይበድል በመልካምነቱ የተቀበለው መከራና የፍቅር መስዋዕትነት ነው። ዛሬ እኛም በተለያየ መንገድ መከራ ሲደርስብን ደስ ሊለን ይገባል ምክንያቱም የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌነት ተከትለናልና  ፤ በመከራ ከርሱ ጋር እንደነበርን በደስታም አብረን እንሆናለንና ነው በ1ኛ ጴጥ 2፡24 ላይ ጻድቁ ስለኃጢአታችን ሞተ ይላል። 

ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አብረን እስከመጨረሻ ከተጓዝን በኋላም ያለምንም ጥርጥር የክብሩ ተካፋዮች እንሆናለን።

በጥፋት ውኃ ዘመን በኖኅ መርከብ ውስጥ ገብተው በሕይወት እንደተረፉት ሰዎች ዛሬ እኛም  በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ ገብተን መጠለል ከቻልን የኃጢአትን ፍላጻ ሁሉ ማስወገድና ከሰይጣን ወጥመዶች ሁሉ መትረፍ እንችላለን። ይህንንም በማድረጋችን ደግሞ የዘለዓለም ሕይወት ተቋዳሾች እንሆናለን ማለት ነው። በጥምቀታችን አማካኝነት  ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አብረን ሞተናል እንዲሁ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አብረን ተነሥተናል የዘለዓለም ሕይወትም ወርሾች ሆነናል።    

የዛሬው ወንጌል ክፍል ከቅዱስ ማርቆስ 16:15-20 ሲሆን ፤ ከሙታን የተነሣው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ ወደ አባቱ ከማረጉ በፊት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኘበትን ታሪክ ያቀርብልናል። አብዛኛውን ጊዜ የመሰናበቻ ትዕይንቶች የሚያሳዝኑ ናቸው። እርሱ በሸኚዎች ልብ ውስጥ ጥሎት የሚያልፍ አንድ ጠባሳ ይኖራል ፣ ብቻ የመቅረት ስሜት ሊያስከትል የሚችል ቢሆንም ነገር ግን ከእነዚህ ስሜቶች ውስጥ አንዳቸውም በደቀ መዛሙርት ላይ አልተከሰቱም ነበር። ከጌታ ቢለዩም ፣ በሐዘን የተጎዱ አይመስሉም ፣ ይልቁንም ደስተኞች እና  ልዑክ ሆነው ወደ ዓለም ለመሄድ ዝግጁ ናቸው።

ደቀ መዛሙርቱ ለምን አያዝኑም? እኛስ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲያርግ ስናይ እኛም መደሰት ያለብን ለምንድን ነው? ብለን ስንጠይቅ ምክንያቱም ዕርገቱ በመካከላችን የኢየሱስን ተልዕኮ ያጠናቅቃል። በእርግጥ ኢየሱስ ከሰማይ የወረደው ለእኛ ነው። ወደ ሰብአዊነታችን ከወረደ እና ከተበዤን በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ። እናም በዚህ ምስጢር እያንዳንዳችን የወደፊት መድረሻችንን እናሰላስላለን። በጭራሽ ብቻችንን የቀረን አለመሆናችንን ያየንበት ትልቅ መለኮታዊ ምስጢር ነው ፣ ምክንያቱም ኢየሱስ ለዘለዓለም ከደቀመዛሙርቱ ጋር ፤ ከእኛ ጋር ፤ በአዲስ መልክ ይኖራል።

በዚህም እርሱ ካረገ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአዲስ መልክ በእኛ መኻል ይገኛል ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን ሃሳብ ስንመለከት

ደቀ መዛሙርቱን ከመሰናበቱ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ በአደራው ትእዛዝ በሰጠበት ወቅት አንድ አስፈላጊ ገጽታ እንዳለ እንገነዘባለን “ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” (ማርቆስ 16፡15) ። ኢየሱስ በደቀ መዛሙርቱ ስብከት በዓለም ውስጥ መኖሩን ይቀጥላል። በእርግጥ ወንጌላዊያኑ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲያርግ ካዩ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ወዲያው “ወጥተው በየቦታው ሁሉ ሰበኩ” ይለናል (ማርቆስ 16፡20) ይህ የሚሆነው መንፈስ ቅዱስ ከወረደ በኋላ መሆኑን እናውቃለን። በዚህ መለኮታዊ ኃይል እያንዳንዳችን በትንሣኤ እና በመጨረሻው ምጽአቱ መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ ስለ ኢየሱስ የመመሥከር አደራ አለብን።

ይህ ተልዕኮ ለእኛ አነስተኛ ኃይል ላለን ሰዎች ፣ ውስንነቶቻችንን እና ኃጢአቶቻችንን ስንመለከት ለእኛ በጣም ያልተመጣጠነ ተልዕኮ ሊመስል ይችላል። ቅዱስ ወንጌሉ ግን “ጌታም ከእነርሱ ጋር ይሠራ ነበር ፤ ትምህርታቸውንም ተከትለው በሚፈጸሙ ምልክቶች ቃሉን ያጸና ነበር” (ማርቆስ 16፡20) ። የቅዱስ ወንጌል የማብሰር ተልዕኮ ፣ እሱ በሚጠይቀው ፣ የሚከብድ እና ከሰው አቅም በላይ ሊሆን ይችል ይሆናል ፣ ነገር ግን በእርሱ ጸጋ ፣ በእያንዳንዳችን እና በመላው ቤተክርስቲያን ጥረት እውነተኛ እና ውጤታማ ይሆናል እርሱም በእኛ በኩል እንዲሠራ ያስችለዋል።

መንፈስ ቅዱስ ይህንን ያደርጋል ለእርሱ የምንሠራ መሣሪያዎች ያደርገናል። በዚህ መንገድ ፣ በዓለም ውስጥ በአዲስ መንገድ የሚቀርቡት የኢየሱስ አካል “አምስቱ ህዋሳት” ልንሆን እንችላለን አይኖቹ ፣ እጆቹ ፣ ጆሮውቹ እና ድምፁ ፣ ጣዕሙ እና የማሽተት ስሜቱ ያለን የምንለይ ሰዎች ልንሆን እንችላለን። በዚህ መንገድ ፣ በእኛም በኩል ክርስቶስ የተረሱ ወይም የተገለሉ ሰዎችን ፍላጎቶችን ማየት ይችላል ፣ የቆሰሉትን መንካት እና መፈወስ ይችላል ፣ ድምፅ የሌላቸውን ጩኸት ሊሰማ ይችላል ፣ የርህራሄ ፣ የተስፋ ቃላት ሊናገር ይችላል ፣ የኃጢአት መጥፎ ሽታ ባለበት ስፍራ የቅድስና ጥሩ መዓዛ ሊሸት ይችላል።

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ በዚህ ዕርገት በዓል ላይ ፣ ክርስቶስ ወደ ላይ ወጥቶ በአባቱ ቀኝ የተቀመጠበትን መንግሥተ ሰማያትን እያሰብን ፣ በተጨባጭ የሕይወት ሁኔታዎች ውስጥ ያረገውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በዓለም ላይ የእርሱ ታማኝ ምስክሮች እንድንሆን የሰማይ ንግሥት የሆነችውን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ከሁላችንም ጋር ይሁን።

የሰማነውን ቃል በሕይወት መኖር እንድንችል ጸጋና በረከቱን ያብዛልን !

ምንጭ፡ ሬዲዮ ቫቲካን የአማርኛ የስርጭት ክፍል

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

12 June 2021, 18:26