አባ ኒቆዲሞስ ሺናበል በኢየሩሳሌም ከሚኖሩ ካቶሊካዊ ምዕመናን ጋር ሆነው አባ ኒቆዲሞስ ሺናበል በኢየሩሳሌም ከሚኖሩ ካቶሊካዊ ምዕመናን ጋር ሆነው 

በእስራኤል የሚገኙ ካቶሊካዊ ስደተኞች ችግር ውስጥ ቢገኙም በእምነታቸው ጠንካሮች እንደሆኑ ተመሰከረ

በእስራኤል የሚገኙ ስደተኛ ምዕመናን ሐዋርያዊ ተንከባካቢ የሆኑት ክቡር አባ ኒቆዲሞስ ሽናበል፣ በዚያች አገር የሚኖሩ ስደተኞች ብዙውን ጊዜ መገለል እና አድልዎ ቢደርስድባቸውም በእምነት ወደ እግዚአብሔር መቅረባቸውን ገለጹ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኢየሩሳሌም የላቲን ሥርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሰበካ ውስጥ የሰደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ሐዋርያዊ ተንካባብካቢ ክቡር አባ ኒቆዲሞስ ሽናበል ይህን አገልግሎት ከጀመሩ አንድ ዓመት ሆኗቸዋል። በኢየሩሳሌም የላቲን ሰበካ ፓትሪያር ብጹዕ አቡነ ፒዬርባቲስታ ፒሳባላ በኢሩሳሌም ለሚገኙ ከ 100,000 በላይ ለሚሆኑ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ሐዋርያዊ አገልግሎቶችን ለማቅረብ፣ ከእነዚህም መካከል መሠረታዊ ትምህርት፣ ትምህርተ ክርስቶስን እና ቅዱሳት ምስጢራትን ለመስጠት በማቀድ የተግባር መርሃ ግብርን በ 2010 ዓ. ም. ማዋቀራቸውን የሰደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ሐዋርያዊ ተንካባብካቢ ክቡር አባ ኒቆዲሞስ ሽናበል አስረድተዋል። የኢየሩሳሌም ሰበካ በአካባቢው አገሮች ውስጥ ማለትም በቆጵሮስ፣ በእስራኤል፣ በዮርዳኖስ እና በፍልስጥኤም ውስጥ ከሚገኙ የዕብራይስጥ ቋንቋ ተናጋሪ ክርስቲያን ማኅበረሰብ ሰበካዎች መካከል አንዱ መሆኑ ታውቋል። ክቡር አባ ኒቆዲሞስ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንዳስረዱት፣ ሐዋርያዊ አገልግሎት በማበርከት ላይ የሚገኙበት የኢየሩሳሌም ሰበካ ወደ መቶ ሺህ የሚደርሱ ስደተኛ ካቶሊካዊ ምዕመናን የሚገኙበት ሰበካ እንደሆነ፣ ከስደተኞቹ መካከል አብዛኛዎቹ ሥራ ያላቸው መሆኑን አስረድተዋል። አባ ኒቆዲሞስ አክለውም ሥራ ካላቸው ካቶሊካዊ ስደተኞች መካከል ዘጠና ከመቶ ሴቶች እንደሆኑ፣ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ እስራኤል የገቡ፣ በቱሪስት ቪዛ የገቡ ቢሆንም ጊዜው ያለፈበት እና የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃድ የሌላቸው መሆኑን አስረድተዋል።

ሕገወጥነት እና የጉልበት ብዝበዛ

የኢየሩሳሌም ሰበካ ከበርካታ አገራት የመጡ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የሚኖሩበት እንደሆነ ያስረዱት ክቡር አባ ኒቆዲሞስ፣ ከፊሊፒንስ፣ ከስሪላንካ፣ ከሕንድ፣ ከቻይና፣ ከዩክሬን፣ ከፖላንድ፣ ከሮማኒያ፣ እንግሊዘኛ እና ፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ አገራት የመጡ አፍሪካውያን ስደተኞች የሚገኙበት ሰበካ መሆኑን አስረድተዋል። ጥገኝነት ጠያቂዎችን በማስመልከት በሰጡት ማብራሪያ፣ ከኤርትራ እና ከኢትዮጵያ የመጡት ጦርነትን እና አመጽን ሸሽተው የመጡ በመሆናቸው ስደተኞች ሳይሆኑ ጥገኝነት ጠያቂዎች መሆናቸውን አስረድተዋል። እነዚህ ጥገኝነት ጠያቂዎች ታዲያ ካናዳን ወደመሳሰሉ አገራት የመሄድ ዕድል ስለሚያገኙ ባሁኑ ጊዜ ቁጥራቸው እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸው፣ ሌላው የስደተኛ ወገን ሥራ እና የተረጋጋ ኑሮ ፍለጋ የተሰደደ በመሆኑ ቁጥሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን አስረድተዋል።  ሥራ እና የተረጋጋ ኑሮ ፍለጋ ምክንያት የተሰደዱት የተሻለ ኑሮ እንዳላቸው የገለጹት አባ ኒቆዲሞስ፣ የእነዚህ ስደተኞች አገራት መንግሥት ከእስራኤል መንግሥት ጋር ውል የተፈራረመ በመሆኑ፣ ከስሪላንካ፣ ከሕንድ እና ከፊሊፒንስ የሚመጡ ስደተኞች ሕጋዊ የመኖሪያ እና የሥራ ፍቃድ ያላቸው መሆኑን አስረድተዋል።

ቢሆንም በአገሪቱ ጥቂት የሥራ ዕድል ብቻ መኖሩን የገለጹት አባ ኒቆዲሞስ፣ በአሠሪዎች እና ሰራተኞች መካከል ብዙውን ጊዜ አለመስማማት መኖሩን ገልጸው፣ ይህ የሚከሰተው በቤት ውስጥ ጥቃት እና ወሲባዊ ብዝበዛ ምክንያት መሆኑን አባ ኒቆዲሞስ ገልጸው፣ ስደተኞቹ እነዚህን እና ሌሎች ችግሮችን ችለው መኖራቸውን አስረድተዋል። በሕገወጥ መንገድ ወደ እስራኤል አገር የገቡ ስደተኞች ሁኔታ አስከፊ እንደሆነ የገለጹት አባ ኒቆዲሞስ፣ በአንድ ክፍል ውስጥ ከ 20 እስከ 25 ሆነው መኖር፣ በተለያዩ የጽዳት ሥራዎች መሰማራት እና በቀጣሪዎቻቸው በኩል የጉልበት ብዝበዛ መፈጸሙ ከሕገ-ወጥ ስደተኞች አብይ የሕይወት ገጽታዎች መካከል ጥቂቶቹ መሆኑን አስረድተዋል።

ለእናቶች እና ለሕጻናት የሚደረግ ዕርዳታ እና ጥበቃ

እናቶች እና ሕጻናት እንክብካቤን የሚያገኙበትን ማዕከል በመክፈት ዕርዳታን በማድረግ ላይ የሚገኙር አባ ኒቆዲሞስ፣ ስደተኞች በአገሪቱ ውስጥ ጋብቻን መፈጸም እንደማይፈቀድላቸው፣ የፈጸሙም ከሆነ ሕገወጥ መሆኑን ገልጸው፣ ሳይፈልጉ ያረገዙ እና ሕጻናት ያሏቸው በርካታ እናቶች መኖራቸውን አስረድተዋል። ክርስቲያን ማኅበረሰቦች ለሕይወት በሚሰጡት ከፍተኛ ክብር፣ ወደው ሳይሆን ያለውዴታ ቢሆንም የሚወለዱ ልጆችን ለማሳደግ በአቅም ማነስ ምክንያት እንደሚቸገሩ በመገንዘብ፣ በአገሪቱ ከሚገኙ ገዳማውያት እና ገዳማውያን ጋር በመተባበር የመዋዕለ ሕጻናት ትምህርት ቤትን እና የብቸኛ እናቶች የዕርዳታ ማዕከልን ማቋቋማቸውን ገልጸዋል። ክቡር አባ ኒቆዲሞስ አክለውም የእነዚህ ጨቅላ ሕጻናት እናቶች በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው ልጆቻቸውን እና እነርሱን ወደ ማዕከሉ አስገብተው የሃያ አራት ሰዓት ስነ ልቦናዊ እና ማህበራዊ ዕርዳታን በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ገልጸው፣ ሕይወትን ለመታደግ ከተነሳን አይቀር ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች በሙሉ መቋቋም ይኖርብናል ብለዋል።

በጸሎት መተጋገዝ

እነዚህ በሙሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘወትር ሳይሰለቹ የሚነግሩን የህልውና ክፍሎች መሆናቸውን የገለጹት አባ ኒቆዲሞስ፣ በእስራኤል አገር በሚኖሩ ስደተኞች መካከል ጠንካራ እና ታላቅ የእምነት ጥንካሬ እንዳለ ተናግረው፣ ለዚህም አዎንታዊ ጎኑ ስደተኞቹ በእምነት ወንድሞቼ እና እህቶቼ ናቸው በማለት ገልጸዋል። በክርስትና እምነት ውስጥ የጀርመን፣ የሕንድ ወይም የስሪላንካ ጥምቀት የለም ያሉት ክቡር አባ ኒቆዲሞስ፣ አንድ ጥምቀት ብቻ መኖሩን አስረድተው፣ ይህ ማለት ደግሞ በእውነት ወንድሞቼ እና እህቶቼ መሆናቸውን ከመመስከር በተጨማሪ በጥምቀት አንድ ለሆኑት መላው የቤተ ክርስቲያናቸው ጓደኞችም መመስከር መቻላቸውን አስረድተዋል።

በርካታ በማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት የተዋቀሩ የጸሎት ማኅበራት መኖራቸውን የገለጹት አባ ኒቆዲሞስ፣ በዲጂታል ሚዲያ አማካይነት የሚደረግ የጸሎት ማኅበር ለምቾት ሳይሆን ከንፁህ ፍላጎት የተነሳ መሆኑን ገልጸዋል። የአምልኮ ሥነ ሥርዓትን በዩቲዩብ፣ በፌስቡክ ወይም በኢንስታግራም አማካይነት ወዲያው በስፋት ማሰራጨት የተለመደ መሆኑን የተናገሩት ክቡር አባ ኒቆዲሞስ፣ የማኅበራዊ ሚዲያዎች፣ የዩቲዩብ፣ የፌስቡክ ወይም የኢስታግራም መኖር ለስደተኞቹ ትልቅ በረከት እንደሆነ ገልጸው፣ በየቀኑ ወደ ቅዱስ ቁርባን በጸሎት መቅረብ ለሚፈልጉት እና እሑድን ጨምሮ በሌሎች ቀናት የሚቀርቡ የጸሎት ሥነ ሥርዓቶችን መካፈል ለሚፈልጉት በሙሉ መልካም ምላሽ የሰጠ መሆኑን አስረድተዋል።

እምነት እና ውዳሴ

ወደ ቅድስት አገር በተሰደዱት ወንድሞች እና እህቶች የእምነት ጥንካሬ ልባቸውን እጅጉን የተነኩት የቅዱስ ብሩክ ገዳማውያን ማኅበር አባል የሆኑት ክቡር አባ ኒቆዲሞስ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር የነበራቸውን ቃለ ምልልስ ሲያጠቃልሉ፣ በመንበረ ታቦት ላይ ሆነው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን በሚመሩበት ወቅት፣ ስደተኞቹ ከማኅበረሰቡ መገለል፣ አድልዎ እና ሌሎች በርካታ ችግሮች ቢደርስባቸውም በደስታ ተሞልተው ያላቸውን ጥንካራ እምነት በሕብረት ዝማሬ እና አምልኮ ሲገልጹ መመልከት ልብ የሚሰብር መሆኑን ገልጸው፣ ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ማገልገል እንደ ካህን፣ እንደ መነኩሴ፣ እንደ የሥነ መለኮት ሊቅ ልዩ ዕድል እንደሆናቸው እና ከእርሳቸው ይልቅ ስደተኞቹ ወደ እግዚአብሔር ይበልጥ የቀረቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

24 August 2022, 16:09