56ኛው የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ዓመታዊ መደበኛ ጉባኤ መጠናቀቁ ተገለጸ
አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
ከታህሳስ 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ሲመክር እንደ ነበር እንዲሁም ጉባኤው የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የአሥር ዓመት ሐዋርያዊ እና ልማታዊ ዕቅድ በደማቅ ሥነ ሥርዓት ይፋ በሆነበት ማግስት ይህ ጉባኤ መደረጉ ልዩ እንደሚያደርገው እና በጉባኤው ወቅት በእቅዱ አተገባበር ላይ ሰፊ ውይይት መካሄዱን ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ሱራፌል ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን፥ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዘዳንት በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል።
ብጹዕነታቸው እንደተናገሩት፥ ሃገራችን አሁን ካለችበት ተፈጥሮአዊ እና ሰው ሠራሽ ችግሮች አንፃር ህዝቡ በተቸገረበት እና በተሰደደበት አከባቢ ሁሉ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቶሎ ደርሳ መርዳት በምትችልባቸው መንገዶች ላይ ውይይት እንደተካሄደ አክለው ገልጸዋል።
56ኛው መደበኛ ጉባኤ ሌላው ከተወያየባቸው ጉዳዮች ውስጥ፥ በሚቀጥለው ዓመት ጥቅምት 2017 ዓ. ም. ስለሚደረገው የሲኖዶሱ የማጠቃለያ ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት ላይ ሲሆን፥ ብጹዕነታቸው እንደተናገሩት፥ እስካሁን ሲደረጉ የነበሩት የሲኖዶስ ውይይቶች በዚህኛው ጉባኤ መቋጫ እንደሚያገኙ በመግለጽ መላው ካቶሊካዊያን በተሳትፎ፣ በህብረት እና በአንድነት ወንጌልን ማስፋፋት እንዲቻል ጠንክረው እንዲሠሩ መልዕክታቸውን በማስተላለፍ፥ እስከዛው ድረስ በሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቷ መዋቅሮች የሲኖዶሱ ውይይቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል።
ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ አክለው እንደገለጹት፥ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት 56ኛ መደበኛ ጉባኤ በቅርቡ በጳጳሳዊ ምክር ቤት የእምነት አስተምህሮ ጽሕፈት ቤት “የቡራኬ ሐዋርያዊ ትርጓሜ” ብሎ ባስተላለፈው ሠነድ ላይ ማብራሪያ እንደሰጠ እና ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲ ያን አንዲት፣ ቅድስት እና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን እንደመሆኗ መጠን የምታስተምረው ትምህርተ ክርስቲያናዊ አስተምህሮ እንደማይቀየር በማስተወስ በተለይ በጋብቻ ላይ ያላት ሕግ የፀና እንደሆነ እና ጋብቻ በአንድ ወንድ እና በአንዲት ሴት መካከል ብቻ የሚመሠረት የቤተ ክርስቲያን ምስጢር እንደሆነ፥ የዚህም ምስጢር ፍሬዎች ልጆች እንደሆኑ ቤተ ክርስቲያኒቷ በጽኑ እንደምታምን በመግለጽ በዚህም ብጹዓን ጳጳሳት በጥልቀት ተወያይተው ማብራሪያ እንደሰጡበት አመልክተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ አሁን ያለንበት ወቅት የመድኃኒታችን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓልን ለማክበር እየተዘጋጀን ያለንበት ወቅት እንደመሆኑ፥ በቅድስት ሃገር እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት የጌታችን የውልደት ሥፍራ የሆነችውን ቤተልሔምን ጨምሮ በሌሎችም ሃገራት በዓሉ እንደማይከበር ጠቁመው፥ የሚወለደው የሠላሙ ንጉሥ ለምድራችን ሠላሙን እንዲያመጣልን አበክረን እንድንጸልይ አደራ በማለት፥ ለቤተ ክርስቲያኒቷ ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክትም፥ ሁሉም በሚኖርበትም ሆነ በሚሠራበት አከባቢ ስለ ሃገራችን ሠላም ተግተው እንዲጸልዩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
በመጨረሻም ብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን፥ 56ኛው ዓመታዊ ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ተጀምሮ እንዲያልቅ ላደረጉት ሁሉ ምስጋናቸውን በመግለጽ ደምድመዋል።