ኢየሩሳሌም ከተማ ኢየሩሳሌም ከተማ 

የኢየሩሳሌሙ ማግኒፊካት ኢንስቲትዩት በቅድስት ሀገር አብሮ የመኖር ተምሳሌት ነው ተባለ

የቅድስት መንበር ኮሙንኬሽን ጽ/ቤት እና ‘የጳጳሳዊ አካዳሚ ለሕይወት’ የተባለው ተቋም በጋራ በመሆን በቅድስት ሀገር በሚገኘው እና የፍራንቺስካዊያን የሙዚቃ ትምህርት ቤት በሆነው 'ማግኒፊካት ኢንስቲትዩት' የተዘጋጀውን የሙዚቃ ኮንሰርት በሮም ከተማ አቅርበዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በጦርነት ምስቅልቅሏ እየወጣ ካለው ቅድስት ሀገር የመጣው እና 'አብሮ የመኖር ላብራቶሪ' የመሆን ዓላማ ያለው ኦርኬስትራ ሐሙስ አመሻሽ ላይ በትራስቴቬሬ በሚገኘው የሮማ ቤተ ክርስቲያን በሳንታ ማሪያ ባዛሊካ ውስጥ የሙዚቃ ኮንሰርቱን አቅርቧል።

ከሳንት ኤጂዲዮ ማህበረሰብ ጋር በመተባበር የወጣት አይሁዳውያን፣ የክርስቲያን እና የሙስሊም ሙዚቀኞችን አንድ ላይ የያዘው ይህ ስብስብ፥ ቅድስት ከተማ የሆነችው እየሩሳሌም በብዙ ግርግር እና አለመግባባት ውስጥ በምትገኝበት በአሁኑ ወቅት ተስማምቶ የመኖር ምስክርነትን በሙዚቃቸው አሳይተዋል።

የቫቲካን ዜና አባል የሆነው ሮቤርቶ ሴቴራ በቅድስት ሀገር የሚገኘውን የማግኒፊካት ኢንስቲትዩት የሙዚቃ ትምህርት ቤት አባላትን ኮንሰርቱ ከመቅረቡ ከጥቂት ሰዓታት በፊት በቫቲካን ረዲዮ ስቱዲዮ ውስጥ በመጋበዝ አነጋግሯቸው ነበር።

የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር የሆኑት አባ አልቤርቶ ፓሪ እንደገለፁት፥ ተቋሙ ጾታ፣ ቋንቋ፣ ዘር፣ ወይም ሃይማኖት ሳይለይ በኢየሩሳሌም አከባቢ ለሚገኙ ልጆች በሙዚቃ ከፍተኛ የአካዳሚክ ትምህርት ይሰጣል ብለዋል።

ትምህርት ቤቱ የተመሰረተው ከ25 ዓመታት በፊት ድሃ ለሆኑ ክርስቲያን ፍልስጤማውያን ልጆች እንዴት መዘመር እንዳለባቸው ግንዛቤ በማስጨበጥ የሙዚቃውን መሠረታዊ ነገሮችን ማስተማር በፈለጉት በአባ አርማንዶ ፒዬሩቺ እንደሆነም ተገልጿል።

ከዓመታት በኋላም ተቋሙ ወደ ከፍተኛ ሙዚቃ ትምህርት ቤትነት በማደግ አሁን ላይ አብዛኛዎቹ ክርስቲያኖች በሆኑና ነገር ግን ሙስሊም እና አይሁዳውያን የሚገኙበት 220 ተማሪዎችን እንዲሁም አብዛኛው አይሁዳዊያን የሆኑ 33 መምህራን አሉበት። በዚህም ተቋሙ “የአብሮ መኖር ቤተ ሙከራ” በመሆን ተማሪዎች የተለያዩ ባህሎቻቸውን እና ልምዶቻቸውን የሚያበለጽጉበት ትምህርት ቤት እንደሆነ ተነግሯል።
 

08 December 2023, 14:05