እህት ነቢላ ሳሌህ እህት ነቢላ ሳሌህ 

እህት ናቢላ፥ የዓለም መሪዎች በጋዛ የደረሰውን ጥፋት በዓይናቸው እንዲመለከቱት አሳስቡ

በጋዛ የሚገኘው የቅዱስ ቤተሰብ ካቶሊካዊ ቁምስና አባል የሆኑት እህት ነቢላ ሳሌህ፥ ቅዳሜ ታህሳስ 6/2016 ዓ. ም. ጋዛ ውስጥ በእስራኤል ጦር ስለተገደሉት ሁለት ካቶሊክ ምእመናን እና የቤተ ክርስቲያኗ አባቶች ያቀረቡትን አዲስ የሰላም ጥሪ በማስመልከት ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ገለጻ አድርገዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እህት ናቢላ በገለጻቸው፥ “የዓለም መሪዎች ጋዛ ውስጥ በሕጻናትን እና ንጹሃን ሰዎች ላይ የሚደርሰውን የማያባራ ሞት እና በንብረት ላይ የሚደርሰውን ውድመት ለመመልከት ዓይኖቻቸውን እንዲከፍቱ እንጠይቃለን" ብለዋል።

የኢየሩሳሌም የመቁጠሪያ ጸሎት ማኅበር አባል የሆኑት መነኩሲት እህት ናቢላ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደተናገሩት፥ በቁምስናው ውስጥ ተጠልለው በነበሩት የቁምስናው ምዕመናን ላይ የእስራኤል ጦር ቅዳሜ ታህሳስ 6/2016 ዓ. ም. በከፈተው ተኩስ ሁለት ምዕመናን መገደላቸውን ገልጸዋል። የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒዛባላ ያለፈው ቅዳሜ በሰጡት መግለጫ፥ ሁለቱ ምዕመናን በእስራኤል ልዩ ተኳሽ ኃይል በጥይት ተመትተው መሞታቸውን አረጋግጠዋል።

እህት ናቢላ በዕለቱ የሆነውን ነገር ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ባልደረባ ፌደሪኮ ፒያና ሲገልጹ፥ “የልጅ እናት ናሂዳ፥ በጥበቃ ኬላ ውስጥ የነበሩ የእስራኤል ልዩ ኃይሎች በጥይት መትተው ከገደሏት በኋላ፥ ቀጥሎም እናቷን ለመርዳት የደረሰች ልጇንም ጭንቅላቷ ላይ ተኩሰው ገለዋታል” ብለዋል። እህት ናቢላ ክስተቱን በቅርብ ሆነው በማየታቸው እንዳዘኑ እና የእስራኤል ታንኮችም ቤተ ክርስቲያኑን በመክበብ የማያቋርጥ ተኩስ በመክፈታቸው ምዕመናኑ ከተጠለሉበት ወጥተው የሚያስፈልጋቸውን ምግብ እና ውሃ ማግኘት የማይችሉ መሆኑን ገልጸዋል።

“እዚህ ምንም የጦር መሣሪያ የለም!”

“የእስራኤል ሃይሎች ኅብረተሰቡ ከቀኑ አሥር ሰዓት በኋላ ወደ ውጭ እንዳይወጣ ትእዛዝ አስተላልፈዋል” ያሉት እህት ናቢላ፥ በየቦታው ተኩስ እና የማያቋርጥ ውጥረት መኖሩን ተናግረው፥ በግቢያቸው መብራትም ሆነ የመጠጥ ውሃ እንደሌለ አስረድተዋል። እህት ናቢላ አክለውም፥ “ይሁን እንጂ እስዚህ ሰዓት ድረስ ቢያንስ ሞት ስለሌለ እግዚአብሔርን እናመሰግናለን፤ ይህ ጦርነት በቅርቡ እንዲያበቃ ብለን እንጸልያለን” ብለዋል።

የእስራኤል ባለስልጣናት መላው የጋዛ ክርስቲያን ማኅበረሰብ በቤተ ክርስቲያኑ ግቢ እንዲጠለል ማሳሰቢያ የተሰጠው በመሆኑ የቁምስናው ምዕመናን ማኅበረሰብ በቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ ጦርነት እንደሚባባስ እንደማይጠብቅ መሆኑን እህት ናቢላ ገልጸው፥ “በቁምስናቸው ምንም የጦር መሣሪያ እና ሙስሊም ማኅበረሰብ የለም" ብለዋል።

ቤተ ክርስቲያኑ በቅዳሜው ጥቃት የተጎዱት እና የሕክምና ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰባት ሰዎችን እንዳሉ እህት ናቢላ ገልጸው፥ የሀገረ ስብከቱ ተወካይ አባ ዩሱፍ ዕርዳታ እንዲደረግላቸው የጠየቁ ቢሆንም ነገር ግን በአካባቢው እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት መቼ እንደሚመጣ አያውቁም ብለዋል። በቅዱስ ቤተሰብ ቁምስና ውስጥ ተጠልለው ከሚገኙት ስደተኞች መካከል ብዙዎቹ የአካል ጉዳተኛ ወይም የታመሙ ሕጻናት መሆናቸውን አክለው አስረድተዋል።

ሁሉም ም ዕመናን ለብርሃነ ልደቱ በዓል ለመዘጋጀት የጓጉ ቢሆንም፥ ነገር ግን አስቸጋሪ እንደሚሆን እህት ናቢላ ተናግረው፥ "የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ሁል ጊዜ ልባችንን በደስታ የሚሞላ ስለሆነ፥ ምንም ቢኖርም በተቻለን መጠን ለበዓሉ ለመዘጋጀት እንሞክራለን” ብለዋል።

ግፍን በዝምታ መመልከት ከጦርነት ይበልጥ ይጎዳል

እህት ናቢላ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ውይይቱ ማጠቃለያ ላይ ለዓለም መሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት፥ “ሕፃናትን እና ንፁሃን ዜጎችን እየገደለ ያለውን የማያባራ ግድያን እና የንብረት ውድመት ለመመልከት ዓይኖቻቸውን እንዲከፍቱ” በማለት ጠንካራ ተማጽኖ አቅርበው፥ “ስለ ፍትህ አለመናገር ከጦርነት ይበልጥ ይጎዳል” በማለት በምሬት ተናግረዋል።

የቅድስት ሀገር ካቶሊክ አባቶች የብርሃነ ልደቱ መልዕክት

በጋዛ ውስጥ ሰብዓዊው ሁኔታ አሳዛኝ በሆነበት በዚህ ወቅት፥ የቅድስት አገር ካቶሊክ አባቶች ጉባኤ (AOCTS) ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲያበቃ በማለት ሌላ አዲስ ተማጽኖ አቅርበዋል። በጉባኤው የፍትህ እና የሰላም ምክር ቤት ሰኞ ታኅሳስ 8/2016 ዓ. ም. ባስተላለፈው የብርሃነ ልደቱ መልዕክት፥ ባለፉት 70 ቀናት ውስጥ የተገደሉትን በሺዎች የሚቆጠሩ ወንዶች፣ ሴቶች እና ህፃናት፣ ፍልስጤማውያን እና እስራኤላውያንን አስታውሷል።

“ጦርነቱ ስለራሳቸው እና ስለቤተሰባቸው በየዕለቱ በመፍራት በሚኖሩ ሕጻናት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል” ሲል ያስነበበው መልዕክቱ፥ "በጋዛ ውስጥ ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ የተገደሉት የፍልስጤም ሕጻናት ቁጥር በዓለማችን ውስጥ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በተከሰቱ ግጭቶች ከሞቱት ሕጻንት የበለጠ ነው” በማለት አስረድቷል።

በሐማስ ታጣቂዎች እና በእስራኤል ሠራዊት መካከል ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ከመስከረም 26/2016 ዓ. ም. ጀምሮ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ወይም ከ 85% በላይ የጋዛ ሕዝብ መፈናቀሉ እና አብዛኛዎቹ መጠለያ የሌላቸው እና ሳያቋርጡ ከቦታ ወደ ቦታ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ መሆናቸው ታውቋል።

በአካባቢው የሚገኙ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች በመግለጫቸው፥ "ለጠፋው ሕይወት እናዝናለን፣ የሕክምና አገልግሎት ማግኘት ለማይችሉት እና ለቆሰሉትን እንሰጋለን፣ እንዲሁም መጠለያ ለሌላቸው ሰዎች እንጨነቃለን" ብለዋል።

ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የቀረበ አቤቱታ

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች እጅግ አስፈሪ እና አሳዛኝ ክስተት በታየበት በዚህ ወቅት፥ የብርሃነ ልደቱን በዓል ለማክበር ዝግጅት ላይ የሚገኙት በሙሉ ለቅድስት ሀገር ሰላም እንዲጸልዩ ጠይቀው፥ የዓለም መሪዎችም ጦርነቱን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ እና "በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ፍትሃዊ ሰላም የሚመጣበትን መንገድ እንዲያመቻቹ” በማለት አሳስበዋል።

በቤተልሔም፣ በጋዛ እና በቅድስት ሀገር በሙሉ ሰላም እንዲሰፍን እንጸልያለን” ያሉት የቤተ ክርስቲያን መሪዎቹ፥ “ሁከት እንዲያበቃ እና የታሰሩትን በሙሉ እንዲፈቱ እንጸልያለን፤ ተኩሱ በዘላቂነት እንዲቆም፣ ከጭቆና ይልቅ የውይይት ጊዜ እንዲመጣ፣ ከጫናዊ መፍትሄ ይልቅ ፍትሕ እንዲሰፍን፣ እርስ በርስ የመገዳደል ህልም ሳይሆን አብሮ ለመኖር እንጸልያለን” ብለዋል።

ለፈጣን የተኩስ አቁም ስምምነት የሚያግዝ ዓለም አቀፍ የተግባር ቀን

ይህ በንዲህ እንዳለ፣ ካሪታስ ኢንተርናሽናልስ የተሰኘ ካቶሊካዊ የ ዕርዳታ ድርጅት፥ በየአገራቱ ከሚገኙ 162 ብሔራዊ አባል ድርጅቶች ጋር በመሆን፥ ሰኞ ታኅሳስ 8/2016 ዓ. ም. በጋዛ ሰርጥ እና በእስራኤል ላይ የሚደርሰውን ሰብዓዊ አደጋ ለመከላከል እና ተጨማሪ የንጹሃን ሕይወት ሞት ለመከላከል የሚያግዝ የተኩስ አቁም የሚጠራውን ዓለም አቀፍ የድርጊት ቀንን ተቀላቅለዋል። አቤቱታው በዓለም ዙሪያ ከ 800 በላይ ድርጅቶችን ያካተተ ሲሆን ከ 3.5 ሚሊዮን በላይ ፊርማዎችን መሰብሰቡ ታውቋል።

"በዚህ ዓለም አቀፍ የድርጊት ቀን በቅድስት ሀገር የሚገኙ ወገኖች በሙሉ በአስቸኳይ ተኩስ እንዲያቆሙ እናሳስባለን፤ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሕዝቦች በአንድነት፥ ተኩስ ይቁም! አሰቃቂ የቦምብ ጥቃት ይቁም! በማለት ዓለም አቀፍ ድምፅ ሊያሰሙ ይገባል፤ የዓለም መሪዎችም እስራኤል እና ሃማስ በቅድስት ሀገር የሚካሄደውን ተኩስ እንዲያቆሙ፣ በግጭቱ የተጎዱትን ሰላማዊ ዜጎች በሙሉ እንዲጠብቁ፣ ዓለም አቀፍ ህግጋትን እንዲያከብሩ፣ ሰብዓዊ ዕርዳታ ተደራሽነትን እና ደህንነትን እንዲያረጋግጡ፣ ታጋቾችን እና በዘፈቀደ የታሰሩ እንዲፈቱ ማሳሰብ አለባቸው” በማለት የካሪታስ ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አቶ አሊስታይር ዱተን ተናግረዋል።

 

20 December 2023, 18:01