COLOMBIA-VENEZUELA-CRISIS-BORDER-SCRAP MERCHANTS

የነፍሳችን ቀንደኛ ጠላቶች ሶስት ናቸው!

የነፍሳችን ቀንደኛ ጠላቶች ሶስት ናቸው። ሰይጣን፣ ዓለም እና ሥጋችን። ሰይጣንና ዓለም በውጪ ሆነው ጦርነት ያካሂዱብናል፤ ሥጋችን ደግሞ በውስጥ ሆኖ ይዋጋናል። ከነዚህ ከሶስቱ ጠላቶች በነፍሳችን ያየለና የበረታ ዘውትር የሚፈታተነን ከእኛ ጋር ያለ ሥጋችን ነው። “ከሁሉ አስቀድሞ ውጊያችን ከሥጋችን ክፉ ምኞች ጋር ነው፤ ቀጥሎ ደግሞ በዚህ አንጻር የጨለማ ገዢዎች ይለናል ቅዱስ አምብሮስዮስ።

እርሱ እንደተናገረው ዓለምንና መንፈሱን እየናቅን ልናሸንፋቸው እንችላለን። የሥጋችንን ኃይለኛ ፈተናን መጥፎ ዝንባሌውንና አመሉን ማሸነፍ በጣም ከባድና ብርቱ ጥረት የሚጠይቅ ነው፤ ሰይጣንን ደግሞ በጸሎትና በተጋድሎ ልናሸንፈው እንችላለን። ከአዳም ኃጢአት በፊት ሥጋችን በቁጥጥራችን ሥር በመዋል ይታዘዘን ነበር። ከአዳም ኃጢአት በኋላ ግን ለነፍሳችን መታዘዝ እምቢ አለ ፈረጠጠ፣ ተቃራኒም መሆን ጀመረ።

ነፍሳችንና ሥጋችን አፈጣጠራቸው የተለየ ነው። ሥጋችን ምድራዊና ጊዜያዊ ሲሆን ነፍሳችን ግን መንፈሳዊትና ዘለዓለማዊት ናት። “ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው፣ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው” (ዮሐ. 3፣17) ይላል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ። መንገዳቸው፣ ሐሳባቸውና ፍላጐታቸው የተለያየ ነው።

ቅዱስ ጳውሎስ በነፍስና ሥጋ አለመግባባት ተቃራኒነትና ጦርነት ውጊያ ሲናገር እንዲህ ይላል። “የሥጋ ምኞት ከመንፈስ ምኞት ጋር ተቃራኒ ነው፣ የመንፈስ ምኞት ከሥጋ ምኞት ጋር ተቃራኒ ነው” መንፈስና ሥጋ እርስ በርሳቸው ይቃረናሉ። የሥጋ ሥራዎች የታወቁ ሲሆኑ እነርሱም «ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ሟርት፣ ጠላትነት፣ ንትርክ፣ ቅንዓት፣ ቁጣ፣ ራስ ወዳድነት፣ ጥላቻ፣ መለያየት፣ አድመኝነት፣ ምቀኝነት፣ ስካር፣ ዘፋኝነት እነዚህን የመሳሰሉ ናቸው። ይህን የሚያደርግ ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት አያይም።

የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች ግን “ፍቅር፣ ደስታ፣ ትእግሥት፣ ደግነት፣ በጐነት፣ ታማኝነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት” (ገላ 5፣16-17) ናቸው። የሥጋ ፍላጐት ምኞች ከነፍስ ፍላጐትና ምኞች ይበረታል እጅግ ያይላል። ይህን ለነፍስ መልካምና አስፈላጊ መሆኑን እየተረዳን ብዙ ጊዜ ችላ እንለዋለን። ለሥጋ ግን ብርቱና ክፉ መሆኑን እያወቅን ተጨፍነን እናደርገዋለን። ሥጋ መጥፎ የተረገመ ነው። ላደረገው የምፈልግ ነገር አይደለም የማደርግ ላደርገው የማይፈልግ ክፉ ነገር እንጂ ይህ ደግሞ እኔ አይደለሁም የማደርገው ከእኔ ጋር ያለው ሥጋ ነው። እንጂ ደግሞ ለማድረግ እፈልጋሁ፤ ነገር ግን ሐሳቤና ፍላጐቴ ስኬት አይሆንልኝም እምቢ ይለኛል። መንፈሳዊ እንደመሆኔ መጠን የእግዚአብሔርን ሕግ እወዳለሁ ሥጋዊ እንደመሆኔ ግን ይህን ሕግ እጠላለሁ። የሥጋ ምኞት ወደ ሞት ሲወስደን የነፍስ ፍላጐት ግን ወደ ሕይወትና ሰላም ያደርሰናል።

“ሥጋቸውን የሚያገለግሉ እግዚአብሔርን ለማስደሰት አይችሉም” (ሮሜ 3፣ 8-12) ይላል ቅዱስ ጳውሎስ። ቀጥሎ ደግሞ የሚከተለውን ምክር ይሰጠናል። “ወንድሞች ሆይ ሥጋ በእናንተ ላይ ምንም ሥልጣን የለውም የእናንተ ገዥ አይደለም። በሥጋ መንገድ እንድትሄዱ የሚያስገድዳችሁን የሥጋችሁን ፍላጐት በመንፈስ ብታሸንፉት ድል ብትመቱ ግን ሕይወት ታገኛላችሁ። እነዚያ በመንፈስ የሚመሩ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው። እግዚአብሔር ሥጋችንን ለነፍሳችን እንዲታዘዝላትና እንዲያከብራት ሲል የፈጠረው ጓደኛዋና አጋዥ እንዲሆን ነው። እንግዲህ ሥጋችን አምላክ የሰጠውን ውሳኔ እንዲጠብቅ እናደርግው መንፈሳዊ መወዳደሪያና መሰናከያ እናድርግለት።   

 

13 December 2023, 12:01