2020.03.15 BUON PASTORE

የታኅሣሥ 21/2016 ዓ.ም /ዘስብከት 3ኛ/ ዘኖላዊ ቅዱስ ወንጌል እና የዕለቱ መልዕክቶች አስተንትኖ

የዕለቱ ምንባባት

1.    ዕብ 13፡ 16-25

2.   1ጴጥ 2፡21-25

3.   ሐዋ 11፡22-30

4.   ዮሐንስ 10፡ 1-21

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

እረኛና መንጋው

“እውነት እላችኋለሁ፤ ወደ በጎች ጒረኖ በበሩ ሳይሆን፣ በሌላ በኩል ዘሎ የሚገባ ሌባና ነጣቂ ነው፤ በበሩ የሚገባ ግን እርሱ የበጎቹ እረኛ ነው፤ በር ጠባቂው በሩን ይከፍትለታል፤ በጎቹም ድምፁን ይሰማሉ። የራሱንም በጎች በየስማቸው እየጠራ ያወጣቸዋል። የራሱ የሆኑትንም ሁሉ ካወጣ በኋላ ፊት ፊታቸው ይሄዳል፤ በጎቹም ድምፁን ስለሚያውቁ ይከተሉታል። እንግዳ የሆነውን ግን ድምፁን ስለማያውቁ ከእርሱ ይሸሻሉ እንጂ ፈጽሞ አይከተሉትም።” ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፤ እነርሱ ግን ምን እንደ ነገራቸው አላስተዋሉም።

ስለዚህ ኢየሱስ ዳግም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ የበጎች በር እኔ ነኝ። ከእኔ በፊት የመጡት ሁሉ ሌቦችና ቀማኞች ነበሩ፤ በጎቹ ግን አልሰሟቸውም። በሩ እኔ ነኝ፤ በእኔ በኩል የሚገባ ሁሉ ይድናል፤ ይገባል፤ ይወጣልም፤ መሰማሪያም ያገኛል። ሌባው ሊሰርቅ፣ ሊገድልና ሊያጠፋ ብቻ ይመጣል፤ እኔ ግን ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲትረፈረፍላቸው መጥቻለሁ።”

“መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ መልካም እረኛ ሕይወቱን ስለ በጎቹ አሳልፎ ይሰጣል፤ ተቀጣሪው እረኛ ግን በጎቹ የእርሱ ስላልሆኑ፣ ተኵላ ሲመጣ ጥሎአቸው ይሸሻል፤ ተኵላውም በጎቹን ይነጥቃል፤ ይበትናቸዋልም። የሚሸሸውም ተቀጣሪ ስለ ሆነና ለበጎቹ ደንታ ስለሌለው ነው።

“መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ በጎቼን ዐውቃለሁ፤ እነርሱም ያውቁኛል፤ ይህም አብ እኔን እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው ነው። ሕይወቴንም ስለ በጎቼ አሳልፌ እሰጣለሁ። ከዚህ ጒረኖ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነርሱንም ማምጣት አለብኝ። እነርሱም ድምፄን ይሰማሉ፤ አንድ መንጋም ይሆናሉ፤ እረኛውም አንድ። መልሼ ለማንሣት ሕይወቴን አሳልፌ ስለምሰጥ አባቴ ይወደኛል። ሕይወቴን በራሴ ፈቃድ አሳልፌ እሰጣለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤ አሳልፌ ለመስጠትም ሆነ ለማንሣት ሥልጣን አለኝ፤ ይህን ትእዛዝ የተቀበልሁትም ከአባቴ ነው።”

ከዚህም ቃል የተነሣ በአይሁድ መካከል እንደ ገና መለያየት ተፈጠረ። ብዙዎቹም፣ “ጋኔን ያደረበት እብድ ነው፤ ለምን ትሰሙ ታለችሁ?” አሉ። ሌሎች ግን፣ “ይህ ጋኔን ያደረበት ሰው ንግግር አይደለም፤ ጋኔን የዐይነ ስውርን ዐይን መክፈት ይችላልን?” አሉ።

 

የእለቱ አስተንትኖ

በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦችና በጎፍቃድ ያላችሁ ሁሉ ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ዘኖላዊ ወይንም ዘስብከት 3ኛ ሰንበትን እናከብራለን ፡፡ በዚህ ስብከተ ገና ወቅት ይህ ሦስተኛው ሳምንት ዘኖላዊ ማለትም የእረኛው ኢየሱስ ሰንበት ተብሎ ሲጠራ እግዚአብሔር ምን ያህል እያንዳንዳችንን ፈልጎ ለማግኘትና ለመንከባከብ እንዲሁም የእርሱና ለእርሱ ከእርሱ እንዲሁም በእርሱ መሆናችንን እንገነዘብ ዘንድ በዚህ የእርሱ ልደት ዝግጅት ተጋብዘናል። በዚህም መሠረት ገና ማለትም የእርሱ ልደት ቀድሞ እርሱ እኛን እንዳገኘን የሚያሳስበን ሲሆን እኛም እናገኘው ዘንድ ራሳችንን እንድንመረምርና እንድናዘጋጅ ያግዘናል።

በዕብራውያን መልእክት እግዚአብሔርን ደስ ስለሚያሰኘው መስዋዕት ይናገራል፡፡  ይህንንም “ወንድሞቼ ሆይ  የፃፍሁላችሁ መልዕክት አጭር እንደመሆኑ  የምክር ቃሌን በትዕግሥተ እንድትቀበሉ አደራ እላችኋለው” ይላል (ዕብ. 16.22)።

የዛሬው የዕብራውያን መልዕክት በመጀመሪያ ደረጃ የዘለዓለምን ሕይወት ለመውረስ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ ብቻ መጓዝ እንዳለባቸው በ2ኛ ደረጃ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ መጓዝ የማያልቅ በረከት በሕይወታቸው እንደሚሰጣቸው በ3ኛ ደረጃ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ መጓዝ  በውስጡ ወይንም በጉዞው ላይ ብዙ መስቀል መኖሩን እንዲገነዘቡና  ይህንንም መስቀል በትዕግሥትና በጥበብ መሸከም እንዳለባቸው ለማሳሰብ  በመጨረሻም  እግዚአብሔር ለእነሱ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሰጣቸውን አዲስ የሕይወት ጉዞ አዲስ የክርስትና ጉዞ በመተው  ወደ ቀድሞው ኃጢአትና ክፉ ሥራ ከተመለሱ ብርቱ ቅጣት ወደ ፊት እንደሚጠብቃቸው ያሳስባቸዋል፡፡

ይህ ማሳሰቢያ በእርግጥ ለእነርሱ ብቻ ሳይሆንም ዛሬ በቀጥታ እኛን እያንዳንዳችንን ይመለከታል፡፡

ሁላችንም በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኘውን ደህንነት ብቻ በማሰብ በእርሱ ብቻ በመታመንና ለቃሉ በመገዛት መኖር እንዲሁም እርሱን ስንከተል እርሱ ራሱ ያለፈባቸውን የመስቀል መንገዶች ሁሉ በፅናት በመከተል እንድንጓዝ ያስፈልጋል፡፡ ማቴ 24:13 እስከ መጨረሻ የሚፀና እርሱ ይድናል ይላል፡፡

እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው በቃላችን የምናቀርበውን ጸሎት ብቻ ሳይሆን ዘወትር ይህንንም ቃል በተግባራችን እንድናውለው የፈልጋል፡፡

ልክ በኦሪት ዘመን እንደነበረው የእንስሳትን ደም በማፍሰሰ ብቻ የምናቀርበውን መሥዋዕት ሳይሆን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በመርዳት ጥል ባለበት ቦታ ሁሉ ፍቅርን በማውረድ ምሕረትንና ይቅርታን ለበደሉን ሁሉ በማድረግ የእርሱ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት በመሆን የክርስትና ጥሪያችንን በተገቢ መልኩ እንድንኖር ያስፈልጋል። በእግዚአብሔር አብ ፊት ንጹህና ነውር የሌለበት ሃይማኖት ይህ ነው ሰውን ሁሉ በችግሩ መርዳትና ከዓለም እርኩሰት ሁሉ ራስን መጠበቅ ነው ይላል ቅዱስ ሐዋርያው ያዕቆብ (ያዕቆብ 1፡27)።

ለእግዚአብሔር መስዋዕት አድረገን እንድናቀርብለት የሚያስፈልገው ንጹህ ልባችንን ነው ከኃጢአት በመራቅ የተቀደሰውን የእኛን ሰውነት ነው።  ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ይላል “እንግዲህ ወንድሞች ሆይ ሰውነታችሁን ቅዱስና  እግዚአብሔርን ደስ የሚያኝ ሕያው መስዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኀራኄ እለምናችኋለው” ይላል (ሮሜ. 12፡1)፡፡ ይህም ማለት ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አብረን የቀበርነውን አሮጌ ሰውነታችንን በመተው በእርሱ ትንሳኤ ያገኘነውን አዲስ ሕይወት ይዘን በቅድስና ጎዳና ላይ እንመላለስ ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔርም ከእኛ የሚፈልገውና የሚጠብቀው ይህንን ብቻ ነው፡፡

በሁለተኛው መልእክት ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ በመጀመሪያ መልዕክቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ሁሉ መከራና ስቃይ የተቀበለው ለእኛ ምሳሌ ለመሆን እንደሆነ ይናገራል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህንን ሁሉ የመስቀል ጉዞ የተጓዘው እኛን የተጋድሎ ሕይወት ምን እንደሚመስል ለማስተማር እንደሆነ ይናገራል ፡፡

የክርስትና ጉዞ ይሄ ነው ልክ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረንና ምሳሌ እንደሆነን በሕይወታችን የሚገጥመንን የትኛውንም ዓይነት ክፉ ነገር  በመልካም መመለስ እንድንችል ነው ፡፡ ለዚህም ሁሉ እሱ ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  አይነተኛ ምሳሌያችን ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳያስ እንዲህ ይላል “ተጨነቀ ተሰቃየም ነገር ግን አፉን አልከፈተም እንደ ጠቦትም ለእርድ ተነዳ በሸላቾች ፊት ዝም እደሚል በግ አፉን አልከፈተም” (በትንቢተ ኢሳያስ 53፡7)።

የክርስቶስን መንገድ ለመከተል ጉዞ ከጀመርን እኛም በሚደርስብን መከራና ሥቃይ የእርሱን ፈለግ መከተል የግድ ነው፡፡ ምክንያቱም ያለ ስቃይና ያለ ችግር ያለ ብዙ ፈተና ወደ ዘለዓለማዊ ክብር ለመድረስ አንችልም። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ይላል “በሞቱ ከእርሱ ጋር እንዲህ ከተግባርን በትንሣኤውም በእርግጥ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን” ይላል (ሮሜ. 6፡5) ።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ስንከተል በሚደርሰስብን መከራና እንግልት ተስፋ ልንቆርጥ አይገባንም ምክንያቱም እኛም የዘለዓለምን ሕይወት ያገኘነው ፣ ከኃጢአት ሠንሠለት የተፈታነውና የተፈወስነው በእርሱ ቁስል ነውና፡፡ ትንቢተ ኢሳያስ 53፡5 ላይ እንዲህ ይለል “ነገር ግን እሱ ስለመተላለፋችን ተወጋ ስለ በደላችንም ተደበደበ በእርሱ ላይ የወደቀው ቅጣት ለእኛ ሰላም አመጣልን በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን” ይላል፡፡

ዘወትር ጠባቂያችንና እረኛችን የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ሁሉ መከራው እኛን በጸጋውና በኃይሉ አበርትቶናልና በዚሁ ኃይል በምናገኘው እርዳታ የሰይጣንን ፈተናና የዓለምን ማብረቅረቅ በማሸነፍ ከእርሱ የወረስነውን መልካም አብነት በሕይወታችን በዕለት ተዕለት ጉዟችን ተግባራዊ እንድናደርግ ያስፈልጋል፡፡

በዮሐንስ ወንጌል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ መልካም እረኝነት ያስተምረናል፡፡

በብሎይ ኪዳን እግዚአብሔር የእስራኤላውያን እረኛ እንደነበር በመዝ. 23፡1 እንደሁም በትንቢተ ሕዝቅኤል 34፡11-12 ላይ ይናገራል “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው እንዳች አይጐድልብበኝም” ይላል (መዝ. 23፡1) “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ የለናል እኔ ራሴ በጐቼን እፈልጋቸዋለው -- እጠብቃቸዋለሁም እረኛ ከመንጋው ጋር ሳለ የተበተኑትን በጐች እንደሚፈልግ ሁሉ እኔም በጐቼን እፈልጋቸዋለው” ይላል፡፡

በአዲስ ኪዳን ውስጥ ደግሞ እግዚአብሔር ይህንን የእረኝነትን ሥራ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አውርሶታል። ለዚህ ነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐ. 10፡11 ላይ “መልካም እረኛ እኔ ነኝ መልካም እረኛ ሕይወቱን ስለ በጐቹ አሳልፎ ይሰጣል” ብሎ የተናገረው፡፡

የእግዚአብሔርን ልጅና እረኛችን የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  በዚያች የድሆች ከተማ በሆነችው ቤተልሔም ውስጥ መምጣት አስደናቂ እውነታ ለጥቂት ጊዜ ቆም ብለን በአትኩሮት ስናስብ ከራሳችን ማንነትና ዙሪያችንን ከከበቡን ጉዳዮቻችን ሁሉ ለመውጣት እንገደዳለን፡፡ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና ለእግዚአብሔር አብ አዳኝ ፍቅርና መለኮታዊ ጥበቃ ምስጋና ወደ ማቅረብ አዲስ አድናቆት ወደ መቸር ከፍ ከፍ እንላለን፡፡

የስብከተ ገና ወራት የመታደሻ፣ አዲስ እምነት የመቀበያና የመለወጫ ጊዜ ነው፡፡ ይህ ወቅት ለመንፈሳዊ እድገት እንቅፋት የሚሆኑትን በርካታ የችግር ሰንሰለቶች የመበጠሻ ጊዜ ነው፡፡ ወቅቱ ከእግዚአብሔር መለኮታዊ ኃይሉና ጥበቃው በሕይወታችን ላይ ካስቀመጣቸው ከወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋርም የአንድነት መተሳሰሪያ ገመዳችንን የምናጠብቅበት ጊዜ ነው፡፡ አንዱ የመጠቀሚያ ዘዴያችንም የእርቅና የፍቅር የሆነው የንስሐ ቅዱስ ሚስጥር ነው፣ ይህ ሚስጢር ኃጢአትን ይቅር ለማለት የሚደርስልንና እውነተኛውን ውስጣዊ መለወጥ ለማግኘት የሚያስችለንን ፀጋ የያዘ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡

ጌታ በኛ ተፈልጐ መገኘት ያለበት ነው በርሱ በኩል የሚቻለውን ያህል ቀርቧልና፡፡ እርሱ እኛ ዘወትር ልንፈልገው የሚገባና እንደ ተገናኘንም ወዲያውኑ ሕይወታችንን ሊለውጠው ዘወተር ተዘጋጅቶ የሚጠብቀን ነው፡፡ እረኛችንን ፍለጋ እንድንሄድና ብሎም እንድንከተለው ልባችንና ነፍሳችን አጥብቀው የሚሹትን አምላክ ፍለጋችንን ቀጥለን እስክናገኘው ድረስ በጽኑ እምነት መጓዝ አለብን።

በዚህ ምድር ላይ የምናሳልፈው ሕይወታችን እውነተኛ እረኛችን የሆነውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የማያቋርጥ ፍለጋ ያለበት ፣ እርሱን እስከምናገኘው ድረስ መሻታችንን የምንቀጥልበት ፣ ካገኘነውም በኋላ ለሁል ጊዜውም ካጠገባችን ሳይለይ እንዲኖር የምናደርግበት ጊዜ ሊሆን ይገባል፡፡ በእርግጥ ከልብ የምንወደውና የምንፈልገው ከሆነ እግዚአብሔርን ማግኘት ማለት ዘወተር አጥብቀን ይዘነው መቆየት ማለት ነውና፡፡

እርሱን ፍለጋ በምንሔድበት ጊዜ፤ ፍለጋህ በሙሉ ልብህና ነፍስህ ከሆነ በእርግጥም ጌታን ታገኘዋለህ፡፡ እርሱን ለመፈለግ ታዲያ እንዴት ነው ልባችንንና ነፍሳችን የምናዘጋጀው? የርሱን ትእዛዛት ለመጠበቅ ለራሳችን ውሳኔ ባሳለፍንበት ቀን ፣ የራሳችንን ማንነትና ውስጣችንን መርምረን ንስሐ ለመግባት ቁርጥ ውሳኔ ባደረግንበት ቀን የዚያን ጊዜ ስለርሱ መረዳት እንጀምራለን ፣ ልናገኘው ተስፋ አድርገን ፍለጋውን የጀመርንለትን እርሱን ለማየት እንችል ዘንድ ዓይኖቻችን ይከፈታሉ፡፡ ምክንያቱም ልበ ንፁሃን እስካልሆንን ድረስ እርሱን ለማየትና ለማግኘትም አንችልምና ነው።

የሕይወታችን መሪና እረኛችንን ለመፈለግና ለማግኘት መንገድ ከመጀመራችን በፊት ራሳችንን በጥንቃቄ መመርመርና በልባችን አዳራሽ ውስጥ የተቀመጠው ማን እንደሆነ ተገቢነት ለርሱ ለጌታችን መቀመጫ በሆነው የልባችን አዳራሽ ውስጥ ምን በመካሔድ ላይ እንደሆነ ማየትና ማወቅ አለብን፡፡ በሌላ አነጋገር እርሱን እንግዳችንን  የምናስገባበት ክፍል ማጽዳት አለብን ማለት ነው፡፡ ጌታን ማግኘት ማለት እርሱን መያዝና በልባችን ውስጥ እንዲቀመጥ ወደ ውስጣችን ማስገባት ማለት ነውና ጌታም ወደ እኛ ለመምጣትና ከኛ ጋር ለመኖር ይፈልጋል፡፡

እርሱን መፈለግ የሚገባን ያህል የማንፈልገው ከሆነ ምክንያቱ በንስሐ አገባባችን ላይ የሚጐድል ነገር መኖሩና እኛም ከኃጢአታችን ክብደት ለማዳን የተፈለገውን የሕማምና የሥቃይ መስዋዕትነት ልክ አለመገንዘባችን ነው፡፡ የኃጢአት ይቅርታን ማግኘት አስፈላጊነት ስናውቅና ልምዱም ሲኖረን ብቻ እኛን ይቅር ለማለት ዘወትር ዝግጁ ሆኖ ወደ የሚጠብቀን ጌታ ከልብ ተፀፅተን ፊታችንን ለማዞር የምንችለው ያኔ ብቻ ነው ከልብ በመነጨ ፍቅር እሱን መፈለግና መከተልም የምንጀምረው ፣ ምክንያቱም ብዙ ኃጢአት ይቅር የተባለለት በፋንታው ደግሞ ብዙ ይወዳልና፡፡ "ስለዚህ ተስፋ የቆረጠውን ሁሉ በርታ አይዞህ አትፍራ እግዚአብሔር ሊታደግህ ይመጣል" ት. ኢሳይያስ 35፡4

እግዚአብሔር ሁሉንም ነገሮች የሠራቸው ለራሱ ሲል ሳይሆን ነገር ግን ለታላቁ ፍጥረት ለሰው ልጆች ነው፡፡ ሁሉ ነገር ከተዘጋጀ በኋላ የዚህን ታላቅና ሰፊ ዓለም ንጉሥና ገዢ ሠራ ሰውን ፈጠረ፡፡ መለኮታዊ አስትንፋሱን በሰው ላይ ተነፈሰ፣ ልጁም አደረገው ከዚያም ገደብና ድንበር በሌለው በዘላለማዊ ደስታ ሰውን ተካፋይ እንዲሆንለት እጅግ ከፍተኛ ጉጉት አደረበት፡፡

ሆኖም ግን የሰው ልጅ ታዛዥ ባለመሆኑ የተነሣ የእግዚአብሔርን እቅድ አበላሸ፡፡ ያም ሆኖ ግን እግዚአብሔር የመልካም እረኝነት ተግባሩን ጨርሶ አልተወውም ፣ አልራቀውም፡፡ ስለዚህ አዲስና እጅግ አስደናቂ የሆነ እቅድ አዘጋጀ በህልማችን እንኳን ጨርሶ ይሆናል ብለን ያላሰብነውን ዓይነት የሰውን ልጅ እርሱ ወዳዘጋጀለት ታላቅ ደስታ ለማምጣት ነው አዲሱን ዕቅድ የነደፈው፡፡ የሰው ልጅ ዘላለማዊ ደስታን ይጐናጸፍ ዘንድ እግዚአብሔር ያለውን ታላቅ ጉጉት ለማሳየት በመለኮታዊ ጥበብ ፣ ሃይልና ፍቅር እስከ መናገር ደረጃ ደረሰ፡፡ አንድያና ብቸኛውን ልጁን የምስጢረ ሥላሴ ሁለተኛውን አካል የሆነውን ልጁን እጅግ አሳፋሪና አሰቃቂ የሆነውን የመስቀል ሞት እንዲሞትና በዚህም ሳቢያ የሰው ልጅ ፈጣሪው ለርሱ ያለውን ፍቅርና የዘላለምንም ደስታ እንዲያገኝ ያለውን ጉጉት እንዲገነዘብ ሁሉም ሰብዓዊ ፈጡር ደግሞ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለስ ያንን ተወዳጅ ልጁን የሰው ልጆች ቤተሰብ አባል አድርጐ ወደ ምድር ላከው፡፡እርሱ መለኮታዊ ሕይወት መልሶ ሰጥቶናል፣ በድጋሚ ልጆቹ አድርጐናል ፣ የርሱ የሆነችው ቤተክርስቲያን አባል አድርጐናል በርሷ አማካይነትም እንደ እግዚአብሔር ልጅነታችን ይህንን ወደ ምድር የተላከውን አዳኝ ለነፍሳችን መጠበቂያ የምንወስደው ምግብና መጠጥ አድርጐ ሰጥቶናል፡፡ በሁሉም የሕይወት መከራዎችና ፈተናዎች ውስጥ ይጠብቀናል፣ ይመራናል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ በኩል እንድናልፍ የሚፈልገው የተትረፈረፈ ሕይወት እንዲኖረንና እንድናገኝ ነው። ስለዚህ ሁላችንም በእርሱ በኩል በማለፍ የተቀደሰና በእርሱ ጸጋ የተሞላ አዲስ ሕይወት ይዘን ወደ ቅድስና ጉዞአችንን እንድናጠናክር ያስፈልጋል ለዚህም የደካሞች እናት የክርስቲያኖችና የሃዘነተኞች አፅናኝ የሆነች እናታችን ቅድስት ድንገል ማርያም ትርዳን ጸጋና በረከቱን ከልጇ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ታሰጠን ፤ የሰማነውን በልባችን ያኑርልን።

የሰማነውን ቃል በሕይወት መኖር እንድንችል ጸጋና በረከቱን ያብዛልን !

ምንጭ፡ ሬዲዮ ቫቲካን የአማርኛ የስርጭት ክፍል

30 December 2023, 21:04