በፖርት-አው-ፕሪንስ ውስጥ በስቅለተ ዓርብ ወቅት ክርስቲያኖች የስቅለት መንገድን ሥነ ስርዓት ሲያካሂዱ - የፋይል ፎቶ በፖርት-አው-ፕሪንስ ውስጥ በስቅለተ ዓርብ ወቅት ክርስቲያኖች የስቅለት መንገድን ሥነ ስርዓት ሲያካሂዱ - የፋይል ፎቶ 

በሄይቲ ፖርት ኦ-ፕሪንስ ከተማ ውስጥ ታግተው የተወሰዱት ስድስት መነኮሳት ተለቀቁ

የፖርት ኦ-ፕሪንስ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ማክስ ሌሮይ ሜሲዶር እንደተናገሩት ጥር 10 ቀን 2016 ዓ.ም. በታጣቂዎች ታግተው የነበሩ 6 የቅዱስ አኔ ጉባኤ መነኮሳት እና ከነሱ ጋር የነበሩ ሁለት ሰዎች መለቀቃቸውን ተናግረዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ጥር 10 በሄይቲ ዋና ከተማ በሆነችው በፖርት-አው-ፕሪንስ መሳሪያ ባነገቱ ታጣቂዎች ታግተው የነበሩ ስድስት የቅድስት አኔ ጉባኤ ገዳማዊያን እህቶች እንደተለቀቁ ተገልጿል።

ከመነኮሳቱ ጋር አብረው ታግተው የነበሩት ማለትም ሲጓዙበት የነበረውን አውቶቡስ ይነዳ የነበረው ሹፌራቸው እና አንዲት የመንኩሴ እህት እንዲሁ መለቀቃቸው ተነግሯል።

እነዚህ ማንነታቸው ያልታወቁት ታጣቂዎች ገዳማዊያኑ ሲጓዙበት የነበረውን አውቶብስ አስቁመው ካገቷቸው በኋላ የታገቱትን ለመልቀቅ 3.5 ሚሊዮን ዶላር ጠይቀው እንደነበር የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የሄይቲ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ማክስ ሌሮይ ሜሲዶር ታጋቾቹ መለቀቃቸውን ለቫቲካን ሚዲያ አረጋግጠዋል።

ሊቀ ጳጳስ ሜሲዶር በዜናው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው በዚህ ሁኔታ ትኩረት ሰጥተው ድጋፍ ያደረጉትን ሁሉ በማመስገን፥ “በመጀመሪያ እግዚአብሔርን እናመሰግናለን! ከጎናችን ለነበራችሁ ሁሉ ስላደረጋችሁልን ድጋፍ እናመሰግናለን” ብለዋል።

የር.ሊ.ጳጳሳቱ ጥሪ እና የአከባቢው ቤተ ክርስቲያናት ጸሎቶች

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እሁድ ዕለት ባቀረቡት የመልአከ እግዚያብሄር ጸሎት ላይ ስድስቱ መነኮሳት እንዲፈቱ ከልባቸው ተማጽነው እንደነበር ይታወሳል።

በዕለቱም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የእገታውን ዜና ሲሰሙ ልባቸው በሃዘን እንደተሰበረም ተናግረው ነበር። ብጹዕነታቸው እንዳሉት “ታጋቾቹ እንዲፈቱ ባቀረብኩት ልባዊ ተማጽኖ ላይም በሀገሪቱ ውስጥ ማህበራዊ ስምምነት እንዲመጣ ጸልያለሁ፥ እናም በዚህ የተከበረ ህዝብ ላይ ከፍተኛ ስቃይ እየፈጠረ ያለውን ሁከት እንዲያቆም ለሚመለከታቸው ሁሉ ጥሪዬን አቀርባለሁ” ብለዋል።

ረቡዕ ዕለት በሄይቲ የምትገኘው የካቶሊክ ቤተክርስትያን ለገዳማዊያኑ እህቶች እና ታግተው ለሚገኙ ሰዎች ሁሉ የጸሎት፣ የጥሞና እና የቅዱስ ቁርባን ቀን አዘጋጅታ እንደነበርም ተገልጿል።

ሊቀ ጳጳስ ዱማስ፡ 'ወደ እግዚአብሔር ጮኽን'

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የሄይቲ ጳጳሳት ጉባኤ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የአንሴ-አ-ቬው ሚራጎን ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ፒየር አንድሬ ዱማስ ታግተው የነበሩ ስምንቱም ሰዎች በመፈታታቸው ምስጋና አቅርበዋል።

ጳጳሱ ምስጋናቸውን ለመግለጽ በፃፉት ጽሁፍ “ይህ አፀያፊ ክስተት እምነታችንን በድጋሚ ፈትኖታል፥ ነገር ግን የማይናወጥ ሆኖ ይኖራል” በማለት ገልፀዋል። በማከልም “ወደ እግዚአብሔር ጮኽን፥ በመከራችን ጊዜ እንድንበረታ አድርጎናል፥ የታሰሩትንም ወደ ነፃነት መልሶልናል” ብለዋል።

ብጹእ አቡነ ዱማስ መነኮሳቱ በታገቱ ጊዜ ከቫቲካን ረዲዮ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት መነኮሳቱን በመተካት ራሳቸውን ለእገታ ለማቅረብ እንደሚፈልጉ ተናግረው ነበር።

በመጨረሻም “ድሆችን እና ወጣቶችን ለማዳን ሕይወታቸውን የሰጡ ሴቶችን ማገት የእግዚአብሔርን ፍርድ የሚጠይቅ ተግባር ነው” ብለዋል።
 

26 January 2024, 14:07