በፖርት-ኦፕሪንስ ውስጥ የሚገኘው የሴንት-አኔ እህቶች መኖሪያ በፖርት-ኦፕሪንስ ውስጥ የሚገኘው የሴንት-አኔ እህቶች መኖሪያ  

የሄይቲ ጳጳሳት የታገቱት ስድስት መነኮሳት እንዲፈቱ ጥሪያቸውን አቀረቡ

ባለፈው አርብ በሄይቲ ዋና ከተማ ከአውቶብስ ላይ ታግተው የተወሰዱት 6 መነኮሳት እንዲፈቱ የፖርት ኦ ፕሪንስ ሊቀ ጳጳሳት ጥሪ ማቅረባቸው ተገልጿል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የሄይቲ ጳጳሳት ጉባኤ እና የፖርት ኦ-ፕሪንስ ሊቀ ጳጳስ ሃይቲያውያን “ይህ በወንበዴዎች የተፈፀመ የሽብር ተግባር” ብለው በሚጠሩት ነገር ተሰላችተዋል ይላሉ።

የሀገሪቱ ጳጳሳት የሄይቲ መንግስት ዜጎቹን እንዲጠብቅ በማሳሰብ፥ “ብዙ ጊዜ፣ ቤተክርስቲያን የሰዎችን ስቃይ በተመለከተ የንቀት አመለካከት የሆነውን ዝምታቸውን አውግዛለች” ብለዋል።

በተጨማሪም ጳጳሳቱ ከሁለት ዓመታት በላይ እያስቆጠረ ላለው ሰዎችን አግቶ የመውሰድ ችግር ግልጽ የሆነ ምላሽ አለመስጠቱ እንዳሳዘናቸውም ተናግረዋል።

ጳጳሳቱ አክለውም “ይህ ሁኔታ ሄይቲን ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ አስከፊ ቀውስ ውስጥ ያስገባታል” ካሉ በኋላ ስድስቱ ገዳማዊያን እህቶች በሰላም እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

መነኮሳቱ ለሰማንያ ዓመታት በሄይቲ ህጻናትን እና ድሆችን በመርዳት በተለይም በትምህርት እና በማህበራዊ ልማት ዘርፍ የተሰማሩ የቅዱስ አኔ ጉባኤ አባላት ናቸው።

መነኮሳቱ አርብ ዕለት ፖርት ኦ-ፕሪንስ ከተማ ውስጥ በአውቶብስ እየተጓዙ ከሌሎች ሁለት ሰዎች ጋር በታጠቁ ሰዎች ታፍነው ተወስደዋል። ሆኖም ግን እስካሁን ድረስ ኃላፊነቱን የወሰደ ቡድን ወይም ታጣቂ ቡድን የለም ተብሏል።

አፀያፊ ወንጀል

በሄይቲ የፖርት ኦ-ፕሪንስ ከተማ ረዳት ጳጳስ የሆኑት ጳጳስ ፒየር አንድሬ ዱማስ አፈናውን አውግዘው፥ “ይህ አፀያፊ ወንጀል” እንዲቆም ጠይቀዋል።

“ይህ አጸያፊ እና አረመኔያዊ ድርጊት ወጣቶችን፣ ድሆችን እና በጣም ተጋላጭ የሆኑትን የማህበረሰባችን አባላትን ለማስተማር እና ለማቋቋም በሙሉ ልብ የሚሰሩ እና ለአምላክ የተሰጡ ገዳማዊያን ሴቶች ክብር ምንም አይነት ክብር ዬለውም” በማለትም ድርጊቱን አውግዘዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ባለፈው እሁድ ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ መነኮሳቱ እንዲፈቱ በመማፀን፥ የመታፈናቸውን ዜና ሲሰሙ ታላቅ ሀዘን እንደተሰማቸው ከገለፁ በኋላ፥ ይህ ‘ብዙ መከራን ያስከተለው’ በሃገሪቱ የተከሰተው ብጥብጥ እንዲቆም ጠይቀዋል።

ተጠናክሮ የቀጠለው የጠለፋ ጉዳይ

ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ በሄይቲ ውስጥ ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎች እንደታገቱ የተነገረ ሲሆን፥ ይህ ካለፉት አስራ ሁለት ወራት የሰማኒያ በመቶ ጭማሪ ማሳየቱም ተገልጿል።

ሄይቲ በምዕራቡ ንፍቀ ክበብ ካሉት ሃገራት ውስጥ እጅግ በጣም ድሃ አገር እንደሆነች እና ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የገንዘብ ድጋፍ እንዲሁም የመረጋጋት፣ የህግ እና የስርዓት ከለላ የሚያስፈልጋት ሃገር እንደሆነችም ዘገባዎች ያሳያሉ።
 

25 January 2024, 16:20