የአሜሪካ ብጹዓን ጳጳሳት በዘረኝነት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ በድጋሚ ጥሪ አቀረቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
አሜሪካ የማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር ቀን ሰኞ ጥር 6/2016 ዓ. ም. ባከበረችበት ዕለት፥ የአገሪቱ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ይፋ ባደርጉት መግለጫ ካቶሊክ ምዕመናን እና ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋችነትን፣ የማይሻረውን የሰብዓዊ ወንድማማችነትን እና የፍቅር ውርስን እንዲያከብሩ ጠይቀዋል።
የማርቲን ሉተር ኪንግ "የማይጠፋ ቅርስ"
የሟቹ ማርቲን ሉተር ኪንግ የልደት ቀን ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ጥር 15/1929 ዓ. ም. በሚዘከርበት ቀን በሰሜን አሜሪካ እና በዓለም ዙሪያ ለማኅበራዊ እና ለብሔር ፍትህ የሚደረገውን የማያቋርጥ ትግል ለማስታወስ በሀገር አቀፍ ደረጃ በጥር ወር ሦስተኛ ሳምንት በሚውለው ሰኞ እንደሚከበር ይታወሳል።
በዓሉን ምክንያት በማድረግ የሰሜን አሜሪካ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት እና የሠራዊቱ ሐዋርያዊ አገልግሎት መምሪያ ተጠሪ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጢሞቴዎስ ብሮሊዮ፥ የሟቹን የማርቲን ሉተር ኪንግ ጥሪን መሠረት በማድረግ ዘርን፣ ጎሣን፣ ሃይማኖትን እና ማንኛውንም ልዩነት እንዲታገሉት በማለት አሳስበዋል።
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጢሞቴዎስ በመግለጫቸው “ማርቲን ሉተር ኪንግ እንዳስተማረን፥ ዘረኝነትን እና ጭፍን ጥላቻን በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር መጋፈጥ አለብን” ብለው፥ “ማርቲን ሉተር ኪንግ የሰዎችን ልብ እና አእምሮ ለመለወጥ የእግዚአብሔርን ቃል ተጠቅሟል” ብለዋል።
"እያንዳንዳችን ለፍትህ እና ለሰላም መሥራት እንችላለን ወይም መሥራት አለብን” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጢሞቴዎስ፥ የማርቲን ሉተር ኪንግን እርምጃ ጥሪ በማስታወስ፥ በሕይወት ውስጥ የማያቋርጥ እና አንገብጋቢው ጥያቄ፥ 'ለሌሎች ምን ታደርጋለህ?' የሚለው ነው ብለዋል።
ለዘር እኩልነት ቤተ ክርስቲያን ያላት ቁርጠኝነት
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጢሞቴዎስ እንደተናገሩት፥ በሰሜን አሜሪካ ማኅበረሰብ ውስጥ እየታዩ ባሉት በማያቋርጥ ስደት እና ፀረ-ሴማዊነት፣ በዘር እና በሃይማኖታዊ መድሎዎች፣ በሰዎች የጋራ እውቅና እና ትብብር ላይ ፈጽሞ እንዳልተሠራ አስታውሰው፥ “በእርግጥም በእነዚህ ዘርፎች የተከናወኑ መልካም ነገሮችን የሚያፈርሱ ኃይሎች አሁንም አሉ” በማለት ገልጸዋል።
በመሆኑም የሰሜን አሜሪካ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጢሞቴዎስ፥ የአገራቸው ካቶሊክ ምዕመናን በወንጌል ምስክርነት ጥረቶች እና በሰዎች ግንኙነት ውስጥ ያለውን ቀጣይ የዜጎች መሻሻል አዎንታዊ ምልክቶችን ለመጠቀም ነቅተው እንዲጠብቁ ጋብዘዋል።
“እነዚህ ነገሮች ከተለያዩ ጎሳዎች፣ ብሔረሰቦች እና ባሕላዊ ዳራዎቻች በኩል የሚመጡ አወንታዊ ውጤቶችን የሚገልጹ ማኅበረሰቦችን ለመቅረጽ ያግዛሉ” ብለዋል። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጢሞቴዎስ፥ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለዚህ ሥራ ያላትን የማያወላውል ቁርጠኝነት በማረጋገጥ፥ አእምሮ፣ እምነት እና ተስፋ ካላቸው ሰዎች ሁሉ ጋር በመተባበር እና ቁርጠኝነትን በማረጋገጥ የጉባኤውን መግለጫ ደምድመዋል።
የ 2024 የማርቲን ሉተር ኪንግ ቀን ጭብጥ
የማርቲን ሉተር ኪንግ ቀን በሰሜን አሜሪካ ግዛቶች እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1986 ዓ. ም. ጀምሮ እንደ ፌዴራል በዓል ሆኖ የሚከበር ሲሆን በተለምዶ በሰልፍ፣ የሲቪል መብቶች ተሟጋቾች እና የፖለቲካ ሰዎች በሚሰጡት ንግግሮች እንዲሁም በመላ ሀገሪቱ ያሉ ሰዎች የማኅበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክቶችን በመቀላቀል የሚከበር መሆኑ ይታወቃል።
ለ 2024 ዓ. ም. የተመረጠው የበዓሉ ጭብጥ፥ ተስፋን፣ ድፍረትን እና አንድነትን በማስፋፋት፥ ህልምን በተጨባጭ መኖር ከእኔ ይጀምራል” የሚል እንደሆነ ተመልክቷል።