THAILAND PHOTO SET RELIGIONS CATHOLICS

እኛ ካቶሊኮች በአማላጅነት ያለን እምነታችን

የእምነት ዐምድ የሆነችሁ ቅድስት ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያናችን በማርያምና በቅዱሳን አማላጅነት እንድናምን ታስተምረናለች፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አንድን ቅዱስ ወደ መንበረ ታቦት ከፍ የምታደርገው እግዚአብሔር ያን ቅዱስ ተጠቅሞ ለሰው ልጆች ያደረገውን ድንቅ ሥራውንና መለኮታዊ ቸርነቱን ለማወጅ ነው፡፡ የቅድስና ሕይወቱን ከእኛ ከፍጥረታቱ ጋር የሚካፈለውን እግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ልታወድስ ትፈልጋለች። እግዚአብሔር ሲናገር «እኔ አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ» (ዘሌ.19፡2) ይለናል፡፡

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ቅድስና ባሕርይ የእግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ይህም ማለት ቅድስናው ከእርሱ የማይለይ፣ ቅድስናውን ከማንም ያልተዋሰው ወይንም ያልተቀበለው፣ ማንም ሊወስድበት የማይችል የራሱ ሀብት የሆነ ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር በባሕርዩ ቅዱስ ስለሆነ ቅድስና ከእርሱ እርሱም ከቅድስና ተለይተው የማይታሰቡ ናቸው፡፡ በእርሱ ዘንድ ከቅድስና በስተቀር ሌላ ነገር የማይታሰብበት፤ በቅድስናው እንከን፣ ከሁሉ ልዩ በመሆኑ ሐሰት የሌለበት አምላክ ነው፡፡ ስለሆነም “ቅዱስ እግዚአብሔር” ይባላል፡፡

ሰዎች ቅዱሳን የሚባሉት በፊታቸው ከተዘረጉላቸው ሁለት አቅጣጫዎች እውነተኛውንና ቀጥተኛውን የመረጡ፤ ከተከፈቱላቸው ሁለት በሮች በጠባቧ ለመግባት የወደዱ፣ የተጣራ የሕይወት አቋም የነበራቸው የእግዚአብሔር ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ብዙ ጊዜ ሳይታዩና ዓለም ሳይቀበላቸው፣ የዓለም ታላላቅ ሰዎች ሳያውቀአቸው፣ ነገር ግን በአብ ዘንድ ተወዳጅ ሆነው በጌታችን እርሻ ሳይደክሙና ሳይታክቱ የሠሩ ናቸው፡፡ ለራሳችን ብቻ ስንሠራ በመንፈስ ከመሻገት ይልቅ ለክርስቶስ እየሠራን በሥጋ ብንደክምና ብንሞት ይሻላል ብሎ የክርስቶስን የመረጡ የእምነት አርበኞች ናቸው፡፡ ቅድስና ለክርስቶስ ተከታዮች የተሰጠ «የክብር ማስረጃ» ነው፡፡ እነዚህን ታላቁን መከራ ያለፉትን እናታችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሕያው የሆነ አብነታቸውን እንድንከተል፤ እነርሱ የደረሱበትን ለመድረስና አማላጅነታቸውን እንድንጠይቅ ለእኛ ታቀርብልናለች፡፡ አብነታቸውም እኛ ራሳችን ወደ ቅድስና በሚናደርገው ጉዞአችን ጀግንነትን፣ ትዕግሥትን፣ ቆራጥነትን . . . ወዘተ የሚጠይቁ የአገልግሎት ተግባራትን እንድከናውን ይቀሰቀቅሱናል፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን እምነት ድንግል ማርያምና ቅዱሳን ከሰማይ ሆነው ያማልዱልናል፡፡ በዛሬው ዓለማችን ስለ እመቤታችን ድንግል ማርያም እና ስለ ቅዱሳን አማላጅነት ስንናገር ደስ የማይላቸው ልኖሩ ይችላሉ፡፡

በእርግጥ አመላጅ ማለት ምን ማለት ነው? ምልጃ ማለት፤ አንዱ ስለሌላው የሚያደርገው ልመናና ጸሎት ነው፡፡ የሚለመነው እግዚአብሔር ሲሆን የሚያማልዱት ደግሞ ቅዱሳን ናቸው፡፡ ምልጃ የታዘዘውና ያስፈለገው እግዚአብሔር ከኃጢአተኞች ይልቅ የጻድቃንን ጸሎት የበለጠ ስለሚሰማ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ንጉሥ ዳዊት “የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮዎቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸው” (መዝ.34፡15) ይላል፡፡ ቅዱስ ያዕቆብም “የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች፤ ግዳጅም ትፈጽማለች” (ያዕ.5፡16)፡ በመጻሐፈ ምሳሌም “እግዚአብሔር ከኃጢአተኞች ይርቃል፤ የጻድቃንን ጸሎት ግን ይሰማል” (መ.ምሳሌ 15፡29) ይላል፡፡  

አመላጅነት የሚንጠይቃቸው ቅዱሳን ሰዎች ከእግዚአብሔር የበለጠ ለሰዎች ርኅሩሆችና ደጎች ስለሆኑ አይደለም፡፡ ከእግዚአብሔር የበለጠ ለሰው ልጆች አዛኝና መሐሪ የለም፡፡ ምልጃ በእግዚአብሔር ሥልጣን ጣልቃ መግባትም አይደለም፡፡ እግዚአብሔር እንደ አምባገነን መሪዎችም አይደለም፡፡ ራሱ አንዱ ስለሌላው እንዲጸልይና እንዲለምን ያሳሰበ፤ ሳይለምኑት ሲቀሩ ሳይሆን ሲለምኑት ደስ የሚለው ቸር አምላክ ነው፡፡ ሲለምኑት ደስ የሚለው ብቻ ሳይሆን እኛ ስለ ራሳችንም ሆነ ስለ ሌሎች ወገኖቻችን ስንለምነው ለእኛው ለራሳችን ዋጋ የሚሰጥም ፍጹም ደግ አባት ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ የሕይወት ውሀ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል” (ዮሐ.7፡38) ብሏል ፡፡ እንዲሁም “እኔ የምሰጠው ውሀ በእርሱ ውስጥ ለዘለዓለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል” በማለት እርሱን ያመኑና በጸጋ ላይ ጸጋ እስኪሰጣቸው ደረሰው የከበሩ ወዳጆቹ እግዚአብሔር የሚሰጠው ጸጋና በረከት እንዲሁም ሕይወት በእነርሱ አማካይነት ሲሰጥ የሚኖር መሆኑን ይገልጻል (ዮሐ.4፡14)፡፡ ስለዚህ ቅዱሳን የሕይወት ውሀ ወንዝ መፍለቂያዎች ናቸው፡፡

በሌላው አንድም ፍጡር መቼም ቢሆን ሥጋን ከለበሰው ከእግዚአብሔር ቃልና መድኃኒት፤ ቤዛ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እኩል ሊሆን አይችልም፡፡ ማወዳደር ራሱ የተሳሳተ አሳብ ነው፡፡

የአዳኙ ልዩ አስታራቂነት ከዚህ ከአንድ ምንጭ የመጋራትን ዘርፈ ብዙ ትብብር ይፈጥራል እንጂ አያግድም:: እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ በፍቅር የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል፡፡ እኛ እርስ በርስ ከተፈቀርን የእግዚአብሔር ፍቅር አንቀንስም፡፡ ይልቁንም በሥራችን ጎልቶ እንዲታይ እናደርጋለን፡፡ አማላጅነትም እንደዚያው ነው፡፡ ከሰው ልጅ ከጥልቅ ማንነቱ ለሚነሡት መሠረታዊ ለሆኑት ለሕይወት ጥያቄዎች ከእግዚአብሔር የተሰጠው ብቸኛ መልስ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ መሆኑንም የሌሎች የአማላጅነት ሚና በምንም መልኩ በጥያቄ ውስጥ ሊያስገባ አይችልም፡፡ ኢየሱስ አስራቂያችን ብቻ ሳይሆን እርሱ ራሱ እርቅ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰውና በእግዚአብሔር፣ በሰውና በሰው፣ በሰውና በፍጥረታት መካከል ከኃጢአት የተነሣ የተፈጠረውን የጠላትነትን ግድግዳ በማፍረስ ሰላምን የሚያመጣ ብቻ ሳይሆን እርሱ ራሱ ሰላማችን ነው፡፡ ስለሆነም እግዚአብሔር ለሰዎች ምሕረቱን፣ ፍቅሩን፣ ይቅርታውን፣ ቸርነቱን የሚገልጸው በሰዎችና በሰዎች አማካይነት ነው፡፡ በእግዚአብሔር የተመረጡ ጻድቃን ሰዎች ሊያማልዱልን እንደሚችሉ እናምናለን፤ ይሁንና እግዚአብሔር አማላጅነትን በሙላት የገለጸው አንድ ልጁ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ነው፡፡ እርሱ የአማላጆች ሁሉ አማላጅ ነው፡፡ የሌሎች የአማላጅነት ሚና ትክክለኛ ትርጉምንና ዋጋን የሚያገኘው ከእርሱ ነው፡፡

 

25 January 2024, 16:09