ር.ሊ.ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እና የካንተርበሪ ሊቀ ጳጳስ ጀስቲን ዌልቢ ጥር 16 ቀን 2016 ዓ.ም. የምሽት የጸሎት ሥነ ስርዓት ሲያካሂዱ ር.ሊ.ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እና የካንተርበሪ ሊቀ ጳጳስ ጀስቲን ዌልቢ ጥር 16 ቀን 2016 ዓ.ም. የምሽት የጸሎት ሥነ ስርዓት ሲያካሂዱ   (ANSA)

የአንግሊካንና የካቶሊክ ጳጳሳት ለአንድነት እና ለተልዕኮ ለተደረገው ጥሪ ህብረት መፍጠራቸው ተነገረ

በዓለም አቀፉ የአንግሊካን-ሮማን ካቶሊክ የአንድነት እና ተልእኮ ኮሚሽን (IARCCUM) የመሪዎች ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ ጳጳሳቱ ወደ ዕርቅ የሚያመራውን ፍሬያማ ጉዞ ላይ አጽንኦት ሰጥተው የተነጋገሩ ሲሆን፥ ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶችን በመቅረፍ ወደ ክርስቲያናዊ አንድነት ለመምጣት ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

“የእኛ የጋራ ምስክርነት፣ ጥሪ እና ቁርጠኝነት” በሚል ርዕስ፥ ጥር 23 ቀን 2016 ዓ.ም. የአንግሊካን እና የካቶሊክ ጳጳሳት፥ “በአንድ ላይ ማደግ” በተሰኘው የክርስቲያናዊ ህብረት ጉባኤ ላይ ከተሳተፉ በኋላ በጋራ ሆነው ጋዜጣዊ መግለጫ አውጥተዋል።

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና በእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን መካከል ያለው ዋና ልዩነት አንግሊካውያኑ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱን የክርስትና እምነት መሪ አድርገው የማይቀበሉ ሲሆን፥ ይልቁንም የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን መሪ የእንግሊዝ ንጉሠ ነገሥት ነው ይላሉ። በእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከፍተኛው ደረጃ የሚይዙት የካንተርበሪ ሊቀ ጳጳስ ናቸው።

በመግለጫው ውስጥ ጳጳሳቱ ለአንድነት እና ለጋራ ተልእኮ ያላቸውን ቆራጥነት ያሳዩ ሲሆን፥ መግለጫው የወጣው ጳጳሳቱ በጋራ ተልእኮ እና ምስክርነት ላይ ለመምከር ከጥር 13 እስከ 20/2016 ዓ.ም. ድረስ ለአንድ ሳምንት በሮም እና በካንተርበሪ ከተሞች ውስጥ ሲያካሂዱት የነበረውን ስብሰባ ተከትሎ እንደሆነም ተገልጿል።

ጉባኤው

በዓለም አቀፉ የአንግሊካን-ሮማን ካቶሊክ የአንድነት እና ተልእኮ ኮሚሽን (IARCCUM) የተዘጋጀው ይህ ጉባኤ በሮም ከሚገኘው የክርስቲያን አንድነትን ለማበረታታት ከተቋቋመው ጽ/ቤት እና ከአንግሊካን ህብረት ጽ/ቤት ከፍተኛ ድጋፍ እንደተደረገለትም ለማወቅ ተችሏል።

ለክርስቲያናዊ አንድነት የጸሎት ሳምንት ላይ የተገኙት ጳጳሳቱ፥ በዓለም አቀፍ ደረጃ 27 ሃገራትን የወከሉ ሲሆን፥ አልፎም በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እና በካንተርበሪው ሊቀ ጳጳስ በቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ በሚካሄደው የምሽት የጸሎት ሥነ ስርዓት ላይ ውክልና ተሰጥቷቸው ምክክር እንዲያደርጉ የተወከሉ ናቸው።

አብሮ መራመድ

“ከአራት መቶ ዓመታት ግጭትና መለያየት በኋላ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና የአንግሊካን ኅብረት፥ ከባለፉት ስድስት አስርት ዓመታት ጀምሮ ወደ እርቅ ጉዞ የጀመርን ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜ የዕርቅ መንገዱ ውጣ ውረድ የበዛበት እንደነበር፥ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ እንደሚያግዘን እና ቤተክርስቲያናችንም ዕርቁ በምክክር እንዲደረግ በትጋት እየሠራች እንደሆነ፥ ይህም ድንቅ ፍሬ እያፈራ እንደሆነ ለመግለጽ እንወዳለን” ሲል ይነበባል መግለጫው።

ጳጳሳቱ በመሃላቸው ያለውን በክርስቶስ ኅብረት ውስጥ የሚገኘውን ደስታ እና ሕይወት እንደሚገነዘቡት በማጉላት፥ ይህም በተፈጥሮው ጥልቅ እና ደማቅ ነው ይላሉ።

የዓለም አቀፉ የአንግሊካን-ሮማን ካቶሊክ የአንድነት እና ተልእኮ ኮሚሽን ጳጳሳት ፍሬያማ ውይይትን በማበረታታት እና በሁለቱም በኩል ያሉትን ተመሳሳይ የሆኑ ሃይማኖታዊ እይታዎችን ለማቀራረብ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮን ጥሪ ማስጠጋባት

ጳጳሳቱ በአራቱም ማለትም የምሥክርነት፣ የወዳጅነት፣ የተልእኮ እና የሲኖዶሳዊነት ዘርፎች ውስጥ ቤተክርስቲያን ተቀራርቦ ለመስራት ቅድሚያ እንድትሰጥ ያሳስባሉ። ይህንንም ለማጠናከር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ “በመጀመሪያ ለወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ቅድሚያ እንስጥ፥ ከዚያም መዋቅሮቻችን እናስከትል” ብለው ያቀረቡትን ጥሪ ደግመው አስተጋብተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በሮም በሚገኘው ቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ ለጳጳሳቱ ተልእኮ በሰጡበት ወቅት የተናገሩትን በማጣቀስ “ሲኖዶሳዊነት የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ብቻ ሳይሆን ግንኙነቶችን በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ማዕከል ላይ ማድረግ ነው፥ መጀመሪያ ለወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ቅድሚያ እንስጥ፥ በማስከተልም ለመዋቅሮቻችን” በማለት መግለጫው ያስረዳል።

ጳጳሳቱ በመግለጫቸው አስቸኳይ የአየር ንብረት ችግርን አስመልክቶ የጋራ መኖሪያችንን የመንከባከብን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥተው በመግለጽ፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ‘ኢንሳይክሊካል ኦን ዘ ኢንቫይሮንመንት’ (ላውዳቶ ሲ) እና የአንግሊካን ጳጳሳት በ2022 በላምቤዝ ኮንፈረንስ ያወጡትን ‘የላምቤዝ የአካባቢና የዘላቂ ልማት’ ጥሪን አስተጋብተዋል።

ጳጳሳቱ መግለጫቸውን ያጠቃለሉት በመካሄድ ላይ ባሉ ጦርነቶች ምክንያት በተጎዱ አካባቢዎች የሰላምን መልካም ዜና ለማወጅ ቃል በመግባት ሲሆን፥ ወደ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያኖቻቸው ሲመለሱም፥ እንደ ካቶሊኮችና አንግሊካውያን በአገልግሎቶቻቸው እርስ በርስ እና ሁሉም ክርስቲያኖች አንዲት እና ብቸኛ በሆነችው የክርስቶስ ቤተክርስቲያን አንድነት እንዲዋሃዱ ለማስታረቅ እንድንችል እንጸልያለን ብለዋል።
 

05 February 2024, 15:23