በተባባሩት አረብ ኤምሬቶች የእምነት ምስክርነት ቤተ ክርስቲያንን ባለጸጋ እንደሚያደርጋት ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ማርቲኔሊ በንግግራቸው፥ በሙስሊም አገር ውስጥ ቤተ ክርስቲያን የምትሰጠውን የእምነት ምስክርነት፣ የሰማዕታቱ የኢዮቤልዩ በዓል፣ በሂደት ላይ የሚገኘውን ሲኖዶሳዊ ጉዞን፣ የአቡዳቢ ስምምነት ጥንካሬን እና በየመን ውስጥ ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ በማስመልከት ገለጻ አድርገዋል።
የደቡብ አረቢያ ሐዋርያዊ ተወካይ እና የካፑቺን ፍራንሲስካዊ ማኅበር አባል የሆኑት አቡነ ፓውሎ ማርቲኔሊ በአቡ ዳቢ ከተማ በሚገኝ የቅዱስ ዮሴፍ ካቴድራል አገልጋይ ከሆኑት የማኅበራቸው አባላት ጋር ንግግር አድርገዋል። ይህ ቦታ ከባንግላዴሽ በስደት የመጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን የሚገኙበት እና በቁጥር በርካታ ሰዎች ወደ ሉርድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎት ለማቅረብ እና ሻማ ለማብራት የሚሰበሰቡበት ቦታ እንደሆነ ታውቋል።
ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ማርቲኔሊ በጣሊያን ሚላን ለስምንት ዓመታት በረዳት ጳጳስነት ያገለገሉ እና እንደ ጎርጎርሳውያኑ ከግንቦት ወር 2022 ዓ. ም. ጀምሮ ለተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፣ ለኦማን እና ለመን ሐዋርያዊ ተወካይ ሆነው ያገለገሉ፣ ከ43 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ባሉባቸው በእነዚህ አካባቢዎች ወደ አንድ ሚሊዮን ለሚጠጉ ምዕመናን ሐዋርያዊ መሪ በመሆን በማገልገል ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።
በካቴድራሉ ግቢ ውስጥ ብዙ የተለያዩ ቋንቋዎች እና ወጎች አሉ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የካቲት 5/2019 ዓ. ም. የተባበሩ አረብ ኤምሬቶች ጉብኝታቸው ወቅት በካቴድራሉ በጎበኙበት የመጨረሻ ቀን የፊሊፒንስ ቋንቋን ጨምሮ የአፍሪካ እና የአውሮፓ ቋንቋዎች እንዲሁም በአረብኛ፣ በእንግሊዘኛ፣ በፈረንሳይኛ፣ ከሕንድ ቋንቋዎች በታጋሎግ፣ በማላያላም፣ በሲንሃላ፣ በኡርዱ እና በታሚል ቋንቋዎች መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት መፈጸሙ ይታወሳል።
በጥምቀት አንድ ከሆኑ ልዩነቱ ሃብት ይሆናል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ አቡ ዳቢ ባደረጉት ታሪካዊ ሐዋርያዊ ጉዟቸው ወቅት ከአል አዝሃር መስጊድ ታላቁ ኢማም አል ታይብ ጋር የሰብዓዊ ወንድማማችነት ሠነድ ሲፈርሙ ያደረጉትን ቃለ ምልልስ በማስታወስ ንግግራቸውን የጀመሩት ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ማርቲኔሊ፥ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የሙስሊም ባሕል የሚገኝበት ቦታ እንደ ሆነ ገልጸው፥ በአካባቢው የሚደረግ የወንጌል ስርጭት የመልካም ሕይወት ምስክርነት እንደሆነ ተናግረዋል። ምእመናኖችም በሚያጋጥሟቸው ሁሉ፣ በቤተሰባቸው፣ በሥራ መስክ፣ በትምህርት ቤት፣ በስብሰባዎች እና ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚያደርጉት ግንኙነቶች ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የተገናኘ መልካም የሕይወት ምስክር እንደሆኑ አስረድተዋል።
ቅዱስ ወንጌል በተግባር የሚኖሩትን እና የሚመሰክሩትን ለሌሎችም በቅንነት እና በትህትና የሚያስተላልፉበት መሠረታዊ መንገድ እንደሆነ ገልጸው፥ የወንጌል ምስክርነት እውነትን ለሌሎች የሚያስተላልፉበት ትሁት መንገድ እንደሆነ አስረድተዋል። በሙስሊም አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ባህሪ በመላው አረብ ባሕረ ሰላጤ አገሮች ውስጥ ያለ ባህርይ ስለሆነ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን አማኞቿ ከወንጌላዊው ሕይወት ጋር እንዲጣጣሙ እና ከኢየሱስ ጋር ያለውን ግንኙነት በዕለት ተዕለት ሕይወት ማለትም ከወንጌል የሚወለደውን መልካም ሕይወት እንዲመሰክሩ ታስተምራለች ብለዋል።
የቅዱስ አርጣስ 1500 ዓመት እና የባልደረቦች ሰማዕትነት መታሰቢያ የቅዱሳን ሰማዕታት ታላቅ ኢዮቤልዩ ቢያንስ ሁለት መሠረታዊ ትርጉሞች አሉት ያሉት ብጹዕ አቡነ ፓውሎ ማርቲኔሊ የመጀመሪያው ለኢየሱስ ክርስቶስ እስከ መጨረሻው ታማኝ የመሆን የክርስቲያኖች ምስክርነት እንደሆነ ገልጸው፥ ምንም እንኳን የክርስትና እምነታቸውን እንዲክዱ ግፊት ቢደረግም ሰማዕታት ከእምነታቸው ጋር የሚስማሙ እና ክርስቶስን ከመካድ ሞትን የሚመርጡ እንደ ነበር አስረድተዋል። ስለዚህ ከዚህ አንፃር ሰማዕታቱ መላዋ ቤተ ክርስቲያን በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ምስክር እንድትሆን ሁልጊዜ ያሳስባሉ ብለዋል። ለኛ ያለው ሌላው ትልቅ ዋጋ ከባልደረቦቹ ጋር በነዚህ ሀገራት የክርስትና እምነት መመሥረት እንደሆነ ገልጸው፥ ነገር ግን በዚህ አካባቢ ለመኖር ለሚመጡት ክርስቲያኖች በሙሉ፣ በቀላሉ ስደተኞች እንዳልሆንን እና በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ በተወሰነ መልኩ ታግተን መቆየታችንን ማወቅ አስፈላጊ ነው ብለዋል።